ጊዜው የዲጂታል ዘመን ነው:: ‹‹ዓለም በእጃችን ላይ ናት፣ አንድ መንደር ሆናለች›› አይነት አባባሎች እየተለመዱ መጥተዋል:: በዚህ ዘመን ሰዎች ኑሯቸውን የሚያቀሉበት፤ የሚፈልጓቸውን መረጃዎች በቀላሉ የሚያገኙበት፤ ለትምህርት እና ለሥራም ጭምር ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙበት ሆኗል:: ወቅቱም አዳዲስ ፈጠራዎችን የምንተዋወቅበት እየሆነ በመምጣቱ አንዳንድ በቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራት በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ራሳቸውን አበልጽገው የኑሯቸው አንድ አካል አድርገውታል::
ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ በሥራ ቦታችን የምንጠቀማቸው ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች፣ ታብሌቶች፣ በየቤታችን ውስጥ የምንጋራው ቴሌቪዥን በእለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የምንጠቀማቸው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው:: ታዲያ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሕይወታችንን ተቆጣጥረውታል ማለት በሚቻል መልኩ ረጅም ሰዓትን በስክሪን ላይ እናሳልፋለን::
ይህ ልማድ ከጠቃሚነቱ ባሻገር ሰዎች ረጅም ሰዓት ስልካቸው ላይ በማሳለፍ ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠሩና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ከመጉዳት ባለፈም ጤናቸውን ሲጎዳ ይስተዋላል:: ስክሪን ላይ ረጅም ጊዜ በማሳለፍ ሱስ የተጠመዱ ወላጆችም ሆኑ ልጆቻቸው ለምደውት እና በዚሁ ሱስ ተጠምደው ቀላል የማይባል ጊዜን ስክሪን ላይ ያሳልፋሉ:: የሰው ልጅ የአዕምሮ እድገትና አቀባበል እንደየእድሜው የሚለያይ ሲሆን፣ ሕጻናት ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ከአዋቂዎች በላቀ መልኩ የሚኖራቸው የአዕምሮ እድገት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊም፣ አሉታዊም ተፅዕኖ አለው:: በዛሬው የማኅደረ ጤና ዓምዳችን ሕጻናት ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ጤናቸው ላይ ስለሚያመጣው ጉዳት እና ወላጆች ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ጠቅላላ ሐኪምና ሁለንተናዊ የሕጻናት እድገት ባለሙያ ከሆኑት ዶክተር ቱሚም ጌታቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል::
ዶክተር ቱሚም ሕጻናት ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዱ ልጆች በቴሌቪዥን፣ በታብሌት፣ በስልክ አልያም ዘመን አመጣሽ የስክሪን ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያጠፉት ጊዜ ልንለው እንችላለን ይላሉ::
ጤናማ የሕጻናት የስክሪን ጊዜ
ያለንበት ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ ልጆች ከስክሪን እንዲርቁ ማድረግ አይቻልም የሚሉት ዶክተር ቱሚም፤ የወደፊት የሥራ ሁኔታቸው በዚህ የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ የተመረኮዘ ሊሆን ይችላል:: ስለሆነም ከስክሪን፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ መራቅ አለባቸው ማለት አንችልም:: ነገር ግን አጠቃቀማቸው እንዴት መሆን አለበት የሚለውን ጉዳይ ወላጆች ለይተው ማወቅ እና አፅዕኖት መስጠት ይኖርባቸዋል ይላሉ::
ዶክተር ቱሚም እንደሚያስረዱት ከሆነ ሕጻናት ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጤናማ የሚባል የስክሪን ጊዜ እንደየዕድሜያቸው ይለያያል:: እድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ምንም አይነት ስክሪን ባይመለከቱ ይመረጣል:: ከሁለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ላሉ ሕጻናት ግን ስክሪን ላይ የሚቆዩበት ጊዜ ከአንድ ሰዓት ያልበለጠ እንዲሆን ይመከራል:: ከአምስት አመት በላይ ለሆኑ ሕጻናት ደግሞ ከሁለት ሰዓት ያልበለጠ እና የቤተሰብ ክትትል ሳይዘነጋ ማየት ይችላሉ:: ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን የሰዓት መጠን ከመቆጣጠር ባለፈ ወላጆች እንዲሁም የቤተሰብ አካላት ሕጻናቱ የሚመለከቱትን ርዕሰ ጉዳይ መምረጥ ይኖርባቸዋል:: እድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ሕጻናት በስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ሰዓት በበዛ ቁጥር የሚኖረው ጉዳት ከፍ እያለ ይመጣል::
ያለነው የዲጂታል ዘመን ላይ በመሆኑ ሕጻናቱ ሲያድጉም በዚህ መንገድ ካሉ የኤሌክትሮኒክስ ሲስተሞች ጋር የተላመዱ እንዲሆኑ ይጠበቃል:: በመሆኑም ከልጅነታቸው ጀምሮ ስክሪን እንዲለምዱና እንዲያውቁ ሁኔታዎች ግድ ይላሉ:: ለትምህርታቸው የሚያግዛቸው መሆኑም የግድ የማለቱ አካል ነው::
አንዳንድ ሕጻናት ከቴክኖሎጂ ፈጠራ ጋር የተገናኙ ፍላጎቶች ስለሚኖራቸው ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት በመረዳት ከቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁና እንዲላመዱ ማድረግ እና ቴክኖሎጂው የሚሰጠውን መልካም እድል ተጠቅመው ልጆቻቸውን ከዘመኑ ጋር ከሚያራምዱ እውቀቶች ጋር ማስተዋወቅ ይችላሉ::
ስክሪን ላይ ረጅም ወይንም ያልተገደበ ሰዓት ማሳለፍ በአዕምሮ እድገት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ ብዙም ጥናት የተደረገበት ባይሆንም፤ ባደጉ ሀገራት በሕጻናት የስክሪን ቆይታ ላይ በተደረጉ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው፣ ማኅበራዊ፣ ሥነልቦናዊ እና የጤና ጉዳትን ያስከትላሉ::
ወላጆች ልጆችን ወደ ሕይወታቸው በሚያመጡበት ጊዜ ልጆቻቸው ሊመለከቷቸው የሚችሏቸውን ልጆች ተኮር የሆኑ ይዘቶች ያላቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ድረ-ገጾች አስቀድመው ይመለከታሉ የሚሉት ዶክተር ቱሚም፤ ልጆቻቸውም አካባቢያቸውን ማስተዋል ከሚጀምሩበት የጨቅላነት ጊዜያቸው ጀምረው እነዚህን ድረ-ገጾች ያስተዋውቋቸዋል:: ለሕጻናት ተብለው የሚዘጋጁ ይዘቶች ደግሞ ሳቢ እንዲሆኑ ተደርገው የሚዘጋጁ በመሆናቸው ሕጻናት ከስክሪን ጋር የሚኖራቸው ቅርርብ በእነዚህ ይዘቶች አማካኝነት ይገነባል ይላሉ ጠቅላላ ሐኪሟ::
ሕፃናት በተደጋጋሚ ስክሪን ላይ ጊዜያቸውን ባሳለፉ ቁጥር ስክሪን በራሱ ሱስ የመሆን እድሉ ሰፊ በመሆኑ ሰዓታቸው ያልተገደበ እየሆነ እና እየተላመዱ በሚሄዱበት ወቅት ከዛ መላቀቅ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል:: ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ሕጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ በጣም በመላመዳቸው ምክንያት በሚከለከሉበት ወቅት ትልቅ ነገር እንደተከለከሉ ሆነው ያለቅሳሉ፤ በጠዋት ተነስተው ስልክ ይፈልጋሉ፤ ሲበሉ እጃቸው ላይ ስልክ አብሯቸው ይሆናል:: ወላጆችም ከማስለመዳቸው የተነሳ ሕጻናት በሌላ ጉዳይም ቢሆን በሚያለቅሱበት ወቅት እንደማባበያም ይጠቀሙበታል። ይህ ልክ እንዳልሆነ ነው ዶክተር ቱሚም የሚያስረዱት::
እንደ ዶክተር ቱሚም ሙያዊ ገለፃ፤ ሕጻናት በስክሪን ላይ የሚኖራቸው ቆይታ እና በተደጋጋሚ የሚመለከቱት ይዘት ባሕሪያቸውንም በእጅጉ ይቀይረዋል:: አብዝተው ስክሪን የሚጠቀሙ ሕጻናት ነጭናጫና ስሜታዊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: የባሕሪያቸው መቀያየር ደግሞ ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ይጎዳዋል::
ዶክተሯ ሕጻናት እንደየእድሜያቸው አዕምሯቸው የዳበረ እና ማመዛዘን የሚችሉበት እድሜ ይለያያል:: በመሆኑም በስክሪኑ ላይ የሚያዩዋቸው ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች ላይ የሚመለከቱትን ነገር ለመምሰልና ለመሆን ይጥራሉ:: ከስክሪን ጋር በተላመዱ ቁጥርም በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር የማያወሩ፣ ከሰው መቀላቀል የማይፈልጉ እና የሚኖራቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ደካማ ይሆናል በማለት ነው የሕፃናትን የስክሪን ላይ የረጅም ሰዓት ቆይታ ጉዳት የሚገልፁት::
ሕጻናት ምግብ መመገብ የሚገባቸው አልያም የሚችሉበት እድሜ ላይ ሲደርሱ ወላጆች የሚቸግራቸው በቂ ምግብ እንዲመገቡ ማድረግ ነው:: ታዲያ ወላጆች ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምግብ በሚመገቡበት ወቅት ስክሪን እየተመለከቱ መብላት እንዲለምዱ ያደርጋሉ:: ይህንን የለመዱ ሕጻናት ስክሪን እየተመለከቱ ካልሆነ መመገብ እንዳይችሉ ይሆናሉ:: ይህ በሚሆንበት ወቅት ሕጻናት የሚመገቡትን ምግብ ምንነቱንና ጣዕሙን ሳያውቁትና ሳይለዩት ይመገባሉ:: በሚመገቡበት ሰዓትም ትኩረታቸው ወደ ስክሪኑ ስለሚሆን የሚበቃቸውን መጠን ባለማወቅ በቃኝ አይሉም፤ አልያም ስክሪኑ ላይ የሚመለከቱት ነገር ላይ ለማተኮር ሲሉ በበቂ ሁኔታ ሳይመገቡ በቃኝ ይላሉ::
ከስክሪን ጋር በእጅጉ የተላመዱ ሕጻናት ስልካቸውን ይዘው በአንድ ቦታ ይቀመጣሉ፤ እንደሌሎች ልጆችም እንቅስቃሴ አያደርጉም። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የሰውነታቸው ክብደት እንዲጨምር እና ጥንካሬ እንዳይኖራቸው እንደሚያደርጋቸውም ዶክተር ቱሚምን ይናገራሉ።
“በተጨማሪም″ ነው የሚሉት ዶክተር ቱሚም፣ በተጨማሪም ስክሪን ላይ ረጅም ሰዓት በሚያሳልፉበት ወቅት በሚጠቀሙት ኤሌክትሮኒክስ ላይ የሚኖረው ብሉ ላይት (blue light) “ሰማያዊ ጨረር” ለምንለው የጨረር አይነት ስለሚጋለጡ አብዛኛውን ጊዜ ኮምፒውተር ላይ በማሳለፍ የሚመጣውን “Computer Vision Syndrome” የሚሰኝ ረጅም ሰዓት በኮምፒውተር ላይ በማሳለፍ የሚመጣ የዓይን ድርቀት፣ የአንገትና ማጅራት አካባቢ ሕመም፣ አይንን ማሳከክ፣ የእይታ መደብዘዝ፣ ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ የዓይን ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል::
እንደ ዶክተር ቱሚም አስተያየት፣ ልጆች ባሉበት የእድሜ ክልል ያሉበትን ሁኔታም ሆነ ትክክል እና ትክክል ያልሆነውን የሚያመዛዝኑበት እድሜ ላይ አልደረሱም:: በሀገራችን የሚገኙ ሕጻናት በስክሪን ላይ የሚመለከቷቸው መማሪያም ሆኑ መዝናኛ ላይ ያተኮሩ ይዘቶች ሀገር በቀል ሳይሆኑ በሌላው ዓለም ለሚገኙ ሕጻናት የተዘጋጁ ናቸው:: በመሆኑም ለሕጻናት ተብለው የሚዘጋጁ የሌላ ሀገራት ርዕሰ ጉዳዮች ከኛ ባሕል፣ አስተሳሰብ እና ሃይማኖት ጋር የሚቃረኑ እና የማይገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ:: አንዳንድ መልዕክቶችንም በሕጻናት አዕምሮ ውስጥ ለማስረጽ ሆን ተብለው ስለሚዘጋጁ ወጣ ያሉ አስተሳሰቦችን እና በኛ ባሕል የተወገዙ፤ የሚቃረኑ አመለካከቶችን ትክክል አድርገው ሊቆጥሯቸው ይችላሉ:: በመሆኑም በስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ሰዓት ብቻ ሳይሆን የሚመለከቱት ይዘት በራሱ አዕምሯቸው ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል::
ሕጻናት የልጅነት እድሜያቸው ላይ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የአዕምሯቸው እድገት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው የሚናገሩት ዶክተር ቱሚም፤ ከዚህም ባሻገር የቋንቋ ክሂሎታቸውን ለማሳደግና ለማዳበር ትልቅ አስተዋፅዖ አለው:: ነገር ግን በዚህ እድሜያቸው ላይ ሰፊ ጊዜያቸውን በስክሪን ላይ በሚያሳልፉበት ሰዓት በቅርባቸው ካለ ሰው ጋር በመግባባት ሊያዳብሩት የሚችሉበትን እድል ያጣሉ፤ የቋንቋ እድገታቸውም ዝቅ ይላል:: ምክንያቱም ስክሪን ማየትን ብቻ የሚያካትት በመሆኑና መስማት ባለመሆኑ ነው:: አንዳንድ ወላጆችም ይህንን ባለማስተዋል ልጆቻቸው ቶሎ አፍ ባለመፍታታቸው ምክንያት በሌላ በሽታ የተጠቁ እስኪመስላቸው ድረስ ወደ ጤና ተቋማት ልጆቻቸውን ይዘው እንደሚመጡ ዶክተር ቱሚም ገለፃ ያስረዳል::
እንደ ዶክተር ቱሚም ማብራሪያ፣ ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ በ2021 ባጠናው ጥናት ታዳጊ የምንላቸው ሕፃናት በሚጠቀሟቸው የማኅበራዊ ድረ-ገጾች አማካኝነት በሠራው ጥናት እድሜያቸው ከ12 ዓመት እስከ 17 ዓመት ያሉ ሴት ታዳጊዎች በሚጠቀሟቸው የማኅበራዊ ድረ-ገጾች እና በሚፈሯቸው፤ ነገር ግን፣ በአካል በማያውቋቸው ሰዎች አማካኝነት ዲጂታል ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቅሷል::
ያለንበት ዘመን ከጥቃቅን እስከ ትልቅ የሚባሉ እንቅስቃሴዎቻችን ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፤ ልጆች ደግሞ በጣም ፍላጎት ስላላቸው ለዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን የቀረቡ ከቴክኖሎጂው እና ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ጋር ተላምደው ከወላጆቻቸው እጅግ በልጠው ይገኛሉ:: ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸው በስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቆጣጠርም ሆነ ከልጆቻቸው ጋር ለመግባባት ራሳቸውን ከጊዜው ቴክኖሎጂ ጋር በተቻለ መልኩ ማራመድ ይኖርባቸዋል የሚለውም የዶክተሯ አስተያየት ነው::
በተጨማሪም ወላጆች ራሳቸው ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት እና የሚያዩትን ጉዳይ በተመለከተ ለልጆቻቸው አርዓያ መሆን ይገባቸዋል:: ምክንያቱም ልጆች ወላጆች የሚናገሩትን ሳይሆን ድርጊታቸውን የመከተል ባሕሪ አላቸው:: በመሆኑም ወላጆች በስክሪን አጠቃቀማቸው ላይ ራሳቸውን ማረቅ፣ መገደብ፣ ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜን ማሳለፍና ማውራት እንደሚገባቸውም ዶክተር ቱሚም ያሳስባሉ::
ሕጻናትን ሙሉ ለሙሉ ከስክሪን እንዲለዩ ማድረግ የማይቻል በመሆኑም ስክሪን የሚመለከቱበትን፣ የሚያጠኑበትን እና የሚዝናኑበትን ሰዓት በተመለከተ የቤት ውስጥ ሕግ ማውጣት ይኖርባቸዋል:: ሕጉም በሚወጣበት ጊዜ ልጆችን ያማከለ እና የተስማሙበት ቢሆን ይመረጣል:: ሕጉን አክብረው እና ተከትለው ካልተገኙ የሚጠብቃቸውን ቅጣትም አያይዘው ማስቀመጥ ይገባቸዋል:: ጊዜው የትምህርት ወቅት በመሆኑም ይህ የቤት ውስጥ ሕግም የጥናት ሰዓታቸውን እና ስክሪን ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ በመለየት ወደ ትምህርት ቤት የገቡ ልጆች ትምህርታቸው ላይ የሚኖራቸውን ትኩረት እንዲለዩ ያደርጋቸዋል ሲሉም ነው የሚመክሩት::
ዶክተር ቱሚም እንደሚናገሩት ከሆነ ልጆች የሚኖራቸውን የስክሪን ጊዜ ከመቆጣጠር ባለፈም የሚመለከቷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወላጆች ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል:: ሥነ-ምግባራቸውን የሚያርቅ ከቴክኖሎጂ ጋር ከመላመድ አንጻር እንዲሁ ወላጆች ልጆች ወደ ፊት መሆን የሚፈልጓቸውን ነገሮች በመረዳት ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮችን ሊያዳብሩ የሚችሏቸውን ሀሳቦች መርጠው በማሳየት ሊያበረታቷቸው ይችላሉ:: ቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ ፍላጎት ያላቸው ልጆች አጠቃቀሙን ማወቅ ስለሚገባቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ቢያውቁት የተሻለ ይሆናል::
አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ስክሪን ላይ የምናሳልፍ በመሆናችን ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ፣ ከጥናት ሰዓታቸው በኋላ ለመዝናናት ሲሉ ስክሪን ላይ ብቻ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ:: ወላጆች ልጆች ከስክሪን የተሻለ አዕምሯቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን መፍጠር ይገባል:: የተለያዩ ጨዋታዎችን በቤት ውስጥ በመፍጠር ልጆች እንዲጫወቱ ማድረግ፣ ከቤት ውጪ አብረው ወክ (ሽርሽር) በማድረግ ልጆች እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው ዶክተር ቱሚም የሚያስረዱት::
በተጨማሪም፣ እንደ ሥዕል፣ እጃቸውን እንዲያፍታቱ የሚያደርጉ ጨዋታዎችን መፍጠር፣ ከልጆች ፍላጎት ጋር አብረው የሚሄዱ ጨዋታ መሰል፤ ነገር ግን አዕምሯዊም አካላዊም እንቅስቃሴያቸውን እና ችሎታቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል፤ ከወላጆችም ይጠበቃል:: ለልጆች ተብለው የተዘጋጁ ማዘውተሪያዎች መውሰድ ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ መቀነስም ሆነ መገደብ የሚቻል በመሆኑ እነዚህ እና መሰል ሥራዎች ከወላጆች የሚጠበቁ ስራዎች ናቸው:: ልጆች የሚያዩትን ነገር የመሆን ፍላጎት ስለሚያድርባቸው የሚያዩትን ብቻ ሳይሆን ወላጆች ራሳቸው በቤት ውስጥ ልጆች ባሉበት የሚከፍቱትን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክተውም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል:: ይህም ልጆች አድገው ነገ ለሚኖራቸው ባሕሪ እና ስብዕና ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ሲሉም ሐኪሟ ያጠቃልላሉ::
ሰሚራ በርሀ እና በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም