የ35 ዓመቱ ጎልማሳ ፋዋዝ ፋራ ከባለቤቱና ከስድስት ልጆቹ ጋር ሆኖ በሰንዓ ከተማ በሚገኝ የልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ገብቶ ዋጋ ይጠይቃል። ፋራ ከብዙ ተከታታይ የዋጋ ጥያቄዎች በኋላ የተጠየቀውን ዋጋ መክፈል እንደማይችል ለሱቁ ባለቤት ነግሮት ቤተሰቦቹን ይዞ ከሱቁ ወጣ፡፡
“አንዷ ልጄ አሻንጉሊት እንድገዛላት ትነግረኛለች፡፡ ሌላኛዋ ደግሞ ልብስም ሆነ ሌላ እቃ ለምን መግዛት እንዳልቻልኩ እያለቀሰች ትጠይቀኛለች፡፡ እንኳን አሻንጉሊት ልብስ ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ እንኳ እንደሌለኝ ነገርኳቸው” ይላል። ፋራ በሃዘን ስሜት ተውጦ፤ ዘንድሮ ለኢድ አልፈጥር በዓል ለልጆቹ አዲስ ልብስ ሳይገዛላቸው የቀረበት የመጀመሪያው ዓመት እንደሆነ ፋራ ይናገራል፡፡
ፋራ እንደሚለው፤ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጥሮ ጥሩ ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ የመን ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦቹም በቂ ገንዘብ ይልክላቸው ስለነበር ጥሩ የሚባል ደስተኛ ሕይወት ሲመሩ ቆይተዋል። ባለቤቱ አማም ለኢድ አልፈጥር በዓል ለልጆቻቸው ውድ ልብሶችን ትገዛላቸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ፤ ያ ደስተኛ ሕይወት በነበረበት ሊቀጥል አልቻለም፡፡ የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት የፋራን ቤተሰብ ደስታ ነጠቀው፡፡ ፋራ በመካ ከተማ ውስጥ ስለየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲያወራ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
“የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ልክ እንደ ኢራን ለሐውቲ ታጣቂዎች ድጋፍ ያደርጋል” ብሎ፤ የተናገረው ነገር ከባድ መዘዝ ያመጣብኛል ብሎ አላሰበም ነበር፡፡ ግን በዚህ ንግግሩ የተቆጡት የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ቪዛውን ቀምተው ወደ የመን መለሱት፡፡
አሁን ፋራ ከስድስት ልጆቹና የዘጠኝ ወር እርጉዝ ከሆነችው ባለቤቱ ጋር ሰንዓ ከተማ ውስጥ በኪራይ ቤት ይኖራል፡፡ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን ስራ አጥ የየመን ሕዝብም ተቀላቅሏል። ፋራ ተስፋ አልቆረጠም።
ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ልብሶችን በቅናሽ ዋጋ አገኛለሁ በማለት ፍለጋውን ቀጥሏል፡፡ ፍለጋው ሰምሮለትም ለሁለቱ ልጆቹ የሚሆኑ ልብስ ገዛ። በዚህ የተበረታታው ፋዋዝ፤ ለሌሎቹም የሚሆን ልብስ ለመግዛት ፍለጋውን እንደሚቀጥልና ስጦታ እንደሚሰጣቸውም ቃል ገባላቸው፡፡
ባኪል ሳላም ለሰባት ልጆቹና ወንድሙ ከሞተ በኋላ ለሚንከባከባቸው አራት ወንድሞቹ የሚሆን ነገር ለመግዛት ጫት ይሸጣል፡፡ ጎረቤቶቻቸው አዲስ ልብስ ተገዝቶላቸው ያዩት የሳላም ልጆችም ልብስና ጫማ እንዲገዛላቸው አባታቸውን ጠይቀውት ስለነበር በዋጋ ንረት ወደሚናጡት የሰንዓ ገበያዎች ሄዱ፡፡
ለበዓሉ በቅናሽ ዋጋ እንደሚሸጥ በሩ ላይ ማስታወቂያ ወደለጠፈ አንድ የጫማ መደብር ገቡ፡፡ ይሁን እንጂ፤ ነገሩ እንዳሰበው ስላልሆነ ምንም ዕቃ ሳይገዛ በሁኔታው እየተገረመና እያዘነ መደብሩ ውስጥ እንደቆየ በአካባቢው ለነበሩት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ነግሯቸዋል፡፡
ዘንድሮ በሰንዓ ገበያዎች የሚታየው የኢድ አልፈጥር በዓል ሰሞን ድባብ ባለፉት ዓመታት ከነበረው ፍጹም የተለየ ነው፡፡ ለወትሮው የደስታና የሳቅ አየር የማይለያቸው የሰንዓ ገበያዎች ዘንድሮ በሕፃናት ለቅሶና በገንዘብ እጥረት ምክንያት የልጆቻቸውን ለቅሶ መስማት በተገደዱ ቤተሰቦች ያዘነ ፊት ተሞልተዋል፡፡
የ23 ዓመቱ አብዱል ማሌክ አል-ራሚ ሰንዓ ውስጥ በሚገኘው ታዋቂው አል ሃሳባ ገበያ ውስጥ ልብስ ይሸጣል፡፡ ልጆች ሲያለቅሱና ቤተሰቦች ተከፍተው ሲመለከት እንደሚያዝን ይናገራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትርፍ ለማግኘት መስራቱን ወደጎን በመተው በቅናሽ ዋጋ እንደሚሸጥም ይገልፃል። “ነጋዴዎች አላህን መፍራት አለባቸው። ሕዝቡ ገንዘብ ስለሌለው ዋጋውን ቀንሰው መሸጥ ይገባቸዋል” ይላል፡፡
ኦሳማ ሳዲቅ የተባለ ባለሱቅ በበኩሉ፤ ለድሃ ቤተሰቦች ዋጋ ለመቀነስ እንደማያመነታ ተናግሯል። አንድ ልብስ ሊገዛ ወደሳዲቅ ሱቅ የመጣ ግለሰብ ከተጠየቀው ዋጋ ሁለት ሺ ሪያል (አራት ዶላር) እንደጎደለው ሲናገር ሳዲቅ ግን ሰውየው ያለውን ብቻ ከፍሎ እንዲወስድ ስለማድረጉ የአልጀዚራ ዘጋቢዎች ጽፈዋል፡፡
አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ከባለስልጣናትም ሆነ ከሀብታም ግለሰቦች መደበኛ የሚባል እገዛ ሳይደረግላቸው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እገዛ እያደረጉ ነው፡፡ “ቮለንተርሊ ስማይል ግሩፕ” (Voluntarily Smile Group) የተባለው ቡድን ዳይሬክተር አክራም አል-ታይሪ እንደሚለው፤ ቡድኑ ለኢድ አልፈጥር በዓል ልብስ መግዛት ለማይችሉ ቤተሰቦች ልብስ ለመስጠት አቅዶ ይሰራል፡፡ ባለፈው ዓመት ለ220 ቤተሰቦች ልብስ ለመስጠት አቅዶ ተንቀሳቅሷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 300 ቤተሰቦችን ለመድረስ እቅድ አለው፡፡
አስራ ስድስት ሰራተኞችንና ሃምሳ በጎ ፈቃደኞችን በማካተት የሚንቀሳቀሰው ቡድኑ፤ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚሰበስባቸውን አልባሳትና ስጦታዎች ለድሃ ቤተሰቦች ያከፋፍላል። የቡድኑ ዳይሬክተር አክራም አል-ታይሪ “ቤት ድረስ በመሄድ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በልጆቹ ቁጥር ካርድ እንሰጣለን፡፡
አንድ ካርድ ከአምስት እስከ ስድስት የሚሆኑ ስጦታዎችን የያዘ ነው። አንድ ስጦታ ለአንድ ልጅ የሚሆን ቲሸርትና ሱሪ ይይዛል። እያንዳንዱ ቤተሰብም ልብሱ ወደሚሰጥበት ቦታ በመሄድ ለልጆቹ የሚሆን ልብስ መርጦ ይወስዳል። ጉዳዩ በይፋ ከተነገረ መጨናነቅ ስለሚፈጠር ይህን የምናደርገው በምስጢር ነው፤ ይህ ግን በቂ አይደለም” ይላል፡፡
የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ታማኞች ከሐውቲ ታጣቂዎች ጋር አብረው በፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ መንሱር አል-ሃዲ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከጀመሩበት ከ2015 ጀምሮ የመን በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ትገኛለች። በተለይ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ ወዲህ የመናውያን ሁሉም ነገር ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖባቸዋል፡፡
ሁለቱ አገራት በየመን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ ወዲህ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች እንደተገደሉና (ከነዚህም መካከል ከ60 በመቶ የሚበልጡት ሰላማዊ ዜጎች እንደሆኑ) ከዚህ የሚበልጡ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
በየመን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጀርባ የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካ በበላይነት ለመቆጣጠር የሚሽቀዳደሙት የሳዑዲ አረቢያና የኢራን፤ እንዲሁም ወሳኝ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውን ይህን ቀጣና በእጅ አዙር ለመቆጣጠር ምንጊዜም ቢሆን የማይተኙት የምዕራባውያን ሀገራት እጅ እንዳለበት ተደጋግሞ ይገለፃል፡፡
በእርግጥ ሳዑዲ አረቢያ ሀገር ጥለው የተሰደዱትን የመንሱር አል-ሃዲን ታማኞች ደግፋ በጦርነቱ መሳተፏና ሐውቲዎች የሺኣ እስልምና ተከታይ ናቸው መባሉ ሺአዋ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ በየመኑ ጦርነት እጃቸውን ስለማስገባታቸው እንደዋነኛ ምክንያቶች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡
ኢራን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አብደላ ሳሌህን ታማኞችንና የሐውቲ ታጣቂዎችን እንደምትረዳ ተደጋግሞ ቢነገርም ሀገሪቱ ግን ይህን መረጃ በተደጋጋሚ ስታጣጥለውና “የሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ ውንጀላ ነው” በማለት ስትደመጥ ተስተውላለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ ከፍተኛ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናን ለመቆጣጠር ለአፍታ ያህል የማይዘናጉት ምዕራባውያን በበኩላቸው በሳዑዲ አረቢያ ለሚመራው ጥምር ጦር የሎጂስቲክና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በተለይ አሜሪካ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ ያላት ፍላጎት በየመን በየዕለቱ የሚቀጠፈውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ችላ እንዲባል አድርጎታል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት እየተሳተፈ ለሚገኘው የሳዑዲ-ኤምሬቶች ጥምር ኃይል የምታደርገውን እገዛ እንድታቋርጥ ኮንግረሱ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡
በየመን ለበርካታ ዓመታት ስር ሰድደው የቆዩ ችግሮች የሀገሪቱን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ አድርገውታል፡፡ በየመን ሰፊ ይዞታ እንዳለው የሚነገርለት ዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ የየመናውያንን ሰቆቃ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ካደረገው ቆይቷል፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድንም፤ በአካባቢው ያለውን ይዞታውን ለማስፋት እንደመሸጋገሪያና መቆያ ከሚጠቀምባቸው የአካባቢው ሀገራት መካከል የመን አንዷ ናት።
የንፁሃንን አንገት መቅላት የየዕለት ተግባሩ የሆነው ይህ ቡድን የአየር ጥቃት ለሚያሰቃያቸው የመናውያን ሌላ የሕልውና አደጋ ሆኖባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም፤ ሀገሪቱ በነዚህ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች፤ በሐውቲዎች እና በመንሱር አል-ሃዲ ታማኞች ቁጥጥር ስር ተከፋፍላ ትገኛለች፡፡
በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰውና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል በድህነት የሚወዳደራት የለም በምትባለው የመን እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ያስከተለው ረሀብና በሽታ የሀገሪቱን ዜጎች ስቃይና መከራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባቸዋል፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው፤ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በየመን ያለውን አስከፊ ቀውስ ችላ ብሎ።” በማለት ወቀሳቸውን በተደጋጋሚ አሰምተዋል። ለዚህም ነው የመገናኛ ብዙኃኑና የፖለቲካ ተንታኞቹ የየመኑን ፖለቲካዊ ቀውስ “የተረሳው/የተዘነጋው ጦርነት” (The Forgotten War) የሚል ስያሜ የሰጡት፤
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
አንተነህ ቸሬ