ለኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የቦክስ ውድድር

ከንክኪ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው ቦክስ የተመልካችን ቀልብ በመሳብ ቦክስን የሚስተካከለው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዚያም ነው ውድድሩ በሚካሄድበት ስፍራ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥርና ድጋፍ የሚታየው፡፡ በዚህ ስፖርት በተለይ በከባድ ሚዛን በሚደረጉ ውድድሮች አጓጊ በመሆናቸው ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው የሚካሄዱ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ቦክስ ረብጣ ገንዘብ ከሚንቀሳቀስባቸው 10 ስፖርቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

ይህ ስፖርት በኢትዮጵያ ደግሞ እንደሚገባቸው አላደጉም ከሚባሉት መካከል ይመደባል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ለበርካታ ጊዜ ከተሳተፈችባቸው አትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርቶችን ተከትሎ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይሁንና በተሳትፎ የተወሰነና ከቦክሰኞች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ የተከሰተ መጥፎ ገጠመኝ በማህደሩ መዝግቧል፡፡ በአህጉር ደረጃም ቢሆን ከጥቂት መልካም ውጤቶች ባለፈ እምብዛም የሚነሳ ስኬት አልተገኘም።ነገር ግን በቅርቡ ጭላንጭል የታየባቸውን ተሳትፎዎች እንዲሁም አህጉር አቀፉ የቦክስ ማህበር በኢትዮጵያዊ ፕሬዚዳንት የሚመራ መሆኑን ተከትሎ ተስፋ እየታየበት ነው፡፡

አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ይህን ዓይነት ውድድር በሌላው ዓለም የተለመደ ሲሆን፤ ጎረቤት ሀገራት ሳይቀሩ ፕሮፌሽናል ውድድሮችን በማካሄድ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን። ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ቦክሰኞቿን የማነቃቃት እንዲሁም ታዳጊዎቿ በስፖርቱ እንዲሳቡ የሚያደርግ ተስፋ የጣለችበትን ውድድር ለማከናወን አዲስ አበባ ላይ ቀጠሮ ይዛለች፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የተባለውን ውድድር ያዘጋጁት የአፍሪካ ካናዳ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማህበር (ACISA) ከዓለም አሊያንስ ቦክስ ማህበር (WABA) እና ከሶሎ ኢንተርናሽናል ስፖርት ጋር በመሆን ነው። በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ አሊያም ክልሎች አዘጋጅነት ከሚካሄዱ የቦክስ ቻምፒዮናዎች ባለፈ መሰል ውድድሮች የተለመዱ ባለመሆናቸው በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተወዳዳሪነት አነስተኛ ሊባል የሚችል ነው። በመሆኑም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ያገኘው ማህበሩ ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ጋር ግንኙነት በመፍጠርም ነው መድረኩን ያዘጋጀው፡፡

ውድድሩ በአምስት ዘርፎች የሚደረግ ሲሆን፤ ይኸውም በ71 ኪሎ ግራም(ፕሮፌሽናል)፣ በ57 ኪሎ ግራም፣ 63 ኪሎ ግራም፣ በከፊል ፕሮፌሽናል እንዲሁም ወደፊት በሚገለጽ የሴቶች ተሳትፎ ነው፡፡ ውድድሩ በመጪው ወር መጋቢት 15/2016ዓም የሚደረግ ሲሆን፤ ‹‹ሰላም በአፍሪካ›› የሚል መሪ ሃሳብም አለው።

 የአፍሪካ ካናዳ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንስትራክተር ዮሴፍ ነጋሽ፤ በውድድሩ ላይ ከኢትዮጵያዊያን ቦክሰኞች ባለፈ የእንግሊዝ፣ የኬንያ፣ የኡጋንዳ እና የኮትዲቯር ቦክሰኞች የሚሳተፋ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ በዚህም ታዋቂ ቦክሰኞች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በአፍሪካ የከባድና የቀላል ሚዛን ቻምፒዮን የሆኑት ኮፊል ሚካኤል እና ዱኩ ሮናልድ በከባድ ሚዛን ዘርፍ በ71 ኪሎ ይወዳደራሉ፡፡ በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ቦክሰኞችም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሀገርን ለመወከል የቻሉ እንዲሁም መስፈርቱን የሚያሟሉ አማተሮች ናቸው፡፡

በትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ይህ ማህበር፤ ከውድድሩ ጎን ለጎን ኢትዮጵያዊያን ዳኞችን ወደ ፕሮፌሽናልነት ለማብቃት የሚያስችል ስልጠናም የሚሰጥ መሆኑንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያብራራሉ። ማህበሩ በቀጣይም ታዳጊዎች ላይ እንዲሁም የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች ላይ ለመስራት እቅድ ያለው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይም ተመሳሳይ ውድድሮችንም ያዘጋጃል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ውድድሩ ስፖርቱን ሊያነቃቃ እንደሚችልም ይታመናል፡፡ የአፍሪካ ካናዳ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማህበር ምክትል ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ መላከ ተሰማ፤ ኢትዮጵያዊያን ቦክሰኞችን ለማበረታታት እንዲሁም ወደ ፕሮፌሽናልነት የማሳደግ ዕድል እንዲያገኙ ያለመ ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ የሚደረገው ውድድሩ፤ የሀገርን መልካም ገጽታ ከመገንባት አኳያም ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውድድሩ ላይ የዓለምና የአፍሪካ ቦክስ ማህበራት አመራሮች፣ ዳያስፖራዎች፣ የስፖርቱ አፍቃሪያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ፡፡ አሸናፊ የሚሆኑ ቦክሰኞችም የገንዘብ እና የቤልት ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል፡፡

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You