ባለክራሯ ድውር

ፒያሳ ጊዮርጊስ አፍ ቢኖረው፣ ዶሮ ማነቂያ ቢናገር፣ ደጃች ውቤም ቢመሰክር፣ ምናልባት ስለ ሜሪ አርምዴ ሳይሆን ሜሪ አርምዴን ዛሬም መልኳን ባሳዩን ነበር። እሷ እኮ የፒያሳ ድምቀት፤ የፒያሳ ጊዮርጊስ ጌጥ፤ የአዲስ አበባ ፈርጥ ነበረች። ክንፍ ባይኖራትም በሰማዩ ላይ ሳይቀር የምትበር፤ ባለክራር፤ የማትደክም ንስር አሞራ…የሕይወቷም ድውር ልክ እንደ ክራሯ ያለ ነበር። እያንዳንዱን አውታር በነኩት ቁጥር እንደሚሰጠው ልዩ ልዩ ዜማ። በአንድ ሕይወት ብዙ ድውር፤ በአንድ ክራር ብዙ ሙዚቃ አምባሰል፣ ባቲ፣ አንቺሆዬ እና ትዝታ የሕይወቷ መልክ ናቸው። ባለ ቅኔው በግጥም፤ ሌሎችም በቀለም በስዕል ይናገሩላታል። እንደ ቴዲ አፍሮ ያለው ደግሞ በሙዚቃው እንዲህ ይቀኝላታል፤

«ጸጉሯን ተተኩሳ እንደ አርምዴ ሜሪ፤

ዘመናይ ናት እሷ በክራር ነጋሪ»

ሲል ስላዜመላት ስለዚህች ምትሀተኛ እንስት ብዙ ሰምተን ይሆናል። በዛሬው የዝነኞች አምድ፤ የዝና ቅኝታችን ካሳለፈቻቸው የሕይወት ገጠመኞቿ ላይ ያደላ ይሆናል። ሜሪ የ40ዎቹና 50ዎቹ ምትሀት ነበረች። ከአንዲት መንደር ብቅ ብላ ሙሉ ትውልዱን ያንቀሳቀሰች ያነቃነቀች፣ ደግሞም ያስከተለች የዘመን አብዮተኛ ናት። ዛሬ ላይ ሆነን ይህቺን ምትሀተኛ ሴት ለማወቅ ወደ ኋላ መለስ ብንል፤ ሜሪ አርምዴ በብዙኃኑ ዘንድ፤ ስሟ እንጂ ሕይወቷ ተረስቶ ስለመኖሩ እንገነዘባለን። ዛሬ ላይ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በብዕር ጠብታዎች፤ የሚወሳላት የሕይወት ታሪክና ገጠመኞቿ ከአንድ ቃለምልልስ ላይ የተገኙ ናቸው። ይህ የታሪክ ባለውለታም «መነን» መጽሔት ነበር። 1965ዓ.ም በጊዜው የዚህ መጽሔት አዘጋጅ ደግሞ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ነበር። እኔም፤ ብዕሬን እንዳነሳ አደረገኝ።

ልጅነት በሜሪ ሕይወት ውስጥ ከአብዛኛዎቹ የመንደሯ ልጆች የተለየ ነበር። እግሯ እሺ ብሎ ከአንድ ስፍራ የማይረግጥ፤ ሲልኳት እንደ በረሮ ቱር! ብላ ሄዳ የምትቀር እንደ ቁራ መልዕክተኛ ጭልጥ ባይ። ብዙ ወላጆች እንደሚሉትም «ቂጧ አርፎ የማይቀመጥ» ቅብጥብጥ ቀዥቃዣ፤ አንዳንዴም አይናፋር ቢጤ ነበረች። ሌላ አይደለም፤ እንዲህ የሚያደርጋት የሙዚቃው ውቃቢ ነው። ያክለፈልፋታል የሚለው ቃል እስከማይገልጻት ድረስ ቤተሰቦቿን ሳይቀር ፍዳቸውን ታበላቸው ነበር። ሜሪ መጥፎ አመል ኖሮባት አልነበረም፤ አመሏ ይኸው ሙዚቃ እና የሙዚቃ ፍቅር ነው። የሀገራችን የባህል ቁጥብነት ከሴትነቷ ጋር ተዳምሮ በማኅበረሰቡም ዘንድ ስክነትን የነፈጋት ልብ አውልቅ ተደርጋ እንድትታይ አደረጋት። ላይዋን እንጂ፤ እንዲህ ያገነፈላትን የውስጧን ወላፈን ያየ የተመለከተ አልነበረም። ጨዋታና ፍቅር ገበያ የወጡ ያህል በሚደራበት በዚያ የአራዳ መንደር ውስጥ፤ ጠጅ ቤቶች መደዳውን ይዘው ተገጥግጠዋል። የሜሪ ልብም ከቤቷ ይልቅ በመንደሯ ጠጅ ቤቶች አብዝቶ ይደሰታል። እግሮቿም የሚናፍቁት ወደዚያ ማምራትን ብቻ ነው። መላላክና መታዘዝንም የምትጠባበቀው በጉጉት ነው፤ ተልካ ስትወጣ ግን በስተመጨረሻ መገኛዋ እነዚሁ ጠጅ ቤቶች ናቸው። ይህቺ ታዳጊ ጠጅ አሊያም የሚንቆረቆር የጠጅ አንቡላ ናፍቋት አነበረም። ይልቅስ ጊዜዋን የምታጠፋው ከጠጅ ቤቶቹ መጋረጃ እያጮለቀች ሙዚቃ በመስማትና የአዝማሪዎቹን ክራር በማየት ነበር። ከጠጅ ቤቶቹ ውስጥ የሚታየው ሙዚቃዊ ትርኢት፤ ላይመልሰው ልቧን አሸፍቶት ነበርና በበርበሬና በአርጩሜም የምትመለስ አልሆነችም።

የሜሪ ቤተሰቦች የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ትለወጣለች በማለት ከሚሲዮን ትምህርት ቤት አስገቧት። የያዛት መች በትምህርት የሚለቅ ሆነና፤ ይባስ ትምህርት ቤቱንም ማናወጥ ጀመረች። በቅጥር ግቢና ክፍል ውስጥ ሁሉ ማንጎራጎር ሥራዋ ሆነ። ይሄን የተመለከቱ መምህራኖቿም «ይች ልጅ ዘፈን እንጂ ትምህርት የሚሆናት አይደለችምና ሌሎች ልጆችንም እንዳታበላሽብን በሉ ተረከቡን» ሲሉ መልሰው አስረከቧት። ቤተሰቦቿም «ከእዚሁ ሆና ጫጩትም ቢሆን ትጠብቅ እንጂ ከቤት ውላ ልትለወጥ አትችልም» በማለት ዳግም ወሰዷት። በብዙ ልመናም ተመልሳ ገባች። ግን አሁንም ያው እራሷ ናት። ጓደኞቿ ከመጽሐፍትና ፊደላት ጋር ሲታገሉ፤ እርሷ ግን ከአንዱ ጥግ ሆና ይሄን ሙዚቃዋን ታንቆረቁረዋለች። በስተመጨረሻም፤ መነኩሴው የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ «ከእንግዲህስ ዓይኗን እንዳላይ!» ሲሉ በቁጣ ሸኟት። እሷም «ግልግል!» ስትል ትምህርትን ዳግም ዞራ ላታየው ተሰናብታው ሄደች። ከዚህ በኋላ ሙሉ ጊዜዋን የምታሳልፈው ከጠጅ ቤቶቹ ጓዳና ሳሎን ሆነ። ተፈላጊና ተወዳጅ እየሆነች ከዚያው በክራር መዝፈኗን ቀጠለች። በዚህ መሀል ከአንዲት የፈረንሳይ ዜግነት ካላት ልጅ ጋር ተዋወቀች። ወዳጅነትና ፍቅራቸው ጠንቶ ከጓደኝነትም እንደ እህትማማች ሆኑ። ሜሪ የዘመኑን ብርቅዬና ተወዳጅ የሆኑትን ዘመናዊ ዳንሶችን ተማረች። በድሮዋ ሜሪ ላይ የዳንሱ ነገር ሲጨመርበት፤ ሀገር ምድሩ «ጉድ!» አለ። «ያን ጊዜ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ፥ በባዶ እግር ነበር የሚደነሰው። ታዲያ ይህ ጉዳይ ኅብረተሰቡን አስቆጥቶት ነበር» ስትል ትገልጻለች። በዚህ መሀልም ፈረንሳዊቷ ጓደኛዋ ወደ ሀገሯ ስትመለስ የነበሯትን ንብረት በሙሉ ለሜሪ አስረክባ ሄደች። እዚህ ጋር፤ የሜሪ አርምዴ የአንድ ከፍታ ሁለተኛው የጉዞ ምዕራፍ መጀመሪያ ሆነ።

«ከዚያም አሁን የሞዳኖቫ ሱቅ ከተሠራበት የራስ ኃይሉ ንብረት ላይ ይገኝ የነበረ ቤት በከፍተኛ ገንዘብ ተከራየሁ። ችግሬ ግን የሠለጠኑ ሴቶች ማግኘቱ ነበር። እንዳሁኑ ሴቶች እኔው መርጬ አሠለጠንኳቸው። የፀጉር አሠራሩንም፥ ዳንሱንም አሠለጠንኳቸው። በዚያን ጊዜ ዳንሱም አለባበሱም ብርቅ ስለነበረ ገበያው ደራ» ትላለች። ሜሪ ሴቶችን የምታገኛቸው ወደ ጣሳ ቤቶች መንደር ጎራ በማለት ነበር። ቆነጃጅቱ ባላገር መሳይ ክራራቸውን ይዘው ከቺንኮ ተራ ከተፍ ይላሉ። ይህን መንደር ጣሊያኖቹ «ቺንኮ» እያሉ ሲጠሩት የአዲስ አበባው ሕዝብ ደግሞ «ከሰል ተራ» እያለ ይጠራዋል። የጣሳና ብርሌ፤ የጠጅና ጠላው፤ የክራር ሙዚቃው ኳኳታ የበዛበት መንደር መሆኑ ነው። እዚህ ሠፈር የሚረግጡት በብዛትም ኪሳቸው የነጣ፤ ኑሮ በዘዴዎቹ ናቸው። ሜሪ ከዚሁ ሠፈር ብቅ እያለች እኚያን ጉብል ኮረዳዎች ትጎበኛቸዋለች። ሴቶቹን ስመለከታቸው በጣም ነበር የሚያሳዝኑኝ የምትለዋ ሜሪም «ኑ እኔ ጋ ዳንሱን ተማሩ። እኔ ቤት ስንቱ እንግሊዝ፥ ስንቱ አሜሪካ፥ ስንቱ መኳንንት ይመጣል። እኔ ልውሰዳችሁ ስላቸው፤ እኛ ልብስ የለንም። አንቺ ጋ መጥተን ምን እንፈጥራለን? ሲሉኝ፤ ግድ የለም፤ የኔ ጌጥ የኔ ልብስ አለ፤ እያልኩኝ እወስዳቸው ነበር» በማለት በሁለት መንታ ስሜት ትገልጸዋለች። የወሰደቻቸውንም ሴቶች ጸጉራቸውን እየተኮሰች፤ ኩልን እየኳለቻቸው፤ ሁሉንም ነገር ከሀ እስከ ፐ አስተማርኳቸው የምትለው ሜሪ «ይኸውላችሁ እነሱኑ ለማሠልጠን ስል የፀጉር የመተኮሻውን ካስክ (ቆብ) እራሴ ላይ እያደረግሁ በሽተኛ ሆንኩ» ስትል ስለ መናገሯ ከመጽሔቱ ላይ ሰፍሯል።

በጊዜው የሜሪ አርምዴን ቡና ቤት የማይረግጥ ባለሀብት፤ ብቅ የማይል የውጭ ዜጋም ሆነ የሀገር ውስጥ አርቲስት አነበረም። የሚገርመው ደግሞ ከቡና ቤቱ የሚመጡትን እነዚህን ታላላቆች ለማየትና ለመገናኘት ሲል የሚመጣው ሰው ብዛት ደግሞ ጉድ የሚያስብል ነው። ጨለም ከማለቱ ገና «አልጀመረም? አርቲስቶቹስ ስንት ሰዓት ላይ ነው የሚመጡት?» እያለ በስልክ የሚያጨናንቃት ባለ ምጥ ብዙ ነው። ሦስት ሰዓት ላይ ለሚጀመረው የሜሪ ቡና ቤት የምሽት ዳንስ፤ ሁለት ሰዓት ከመሆኑ በፊት ቤቱ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ ይፈሳል። የመቀመጫ ወንበር የማግኘቱ ነገር ከኪስ በላይ የሚያሳስብ ነው። ከቤቱ ጥግ ጥጉን ያቆመቻቸው የሰባቱ ወጠምሻ ጎረምሳ ግልምጫ ደግሞ ይባስ ለመቁነጥነጥም የማይሆን ነው። በመጠጥ ኃይል ተነሳስቶም ሆነ ተሳስቶ ለመደንፋት ያለውን አንጠልጥለው ያወጡታል። ሜሪ እንደሆን ዝናዋ ከአዲስ አበባ አልፎ፤ የበረራ ቲኬትም ሳይቆርጥ ሀገር አቋርጦ ያልደረሰበት አነበረምና ከውጭም መጣ ከውስጥ «ይህቺ ሜሪ የሚሏት የትኛዋ ናት?» እያለ በስም እየጠራ በዓይን የማይፈልግ፤ የማይጠይቅ አነበረም። እሷም በግልጽ ወጥታ ለመታየትም ሆነ በአካል ለመታወቅ አትፈልግም ነበር፤ ለምን? ስትባል «ምክንያቱም እኔን ለማየት ሲሉ ብቻ ገንዘባቸውን አውጥተው ቡና ቤቴን ስለሚጎበኙት ነዋ» ነበር ያለችው። አይ ሜሪ! ብቻ ሥራዋ ብዙ ነው።

ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን በከተማው ብቸኛ የሆነው የሜሪ ቡና ቤት፤ በቀይ መብራት አሸብርቆ ቦግ እልም እያለ ጣሪያ ግርግዳውን ያሸበርቀዋል። ከወዲህና ወዲያ ብርጭቆውን እያነሳ «ቺርስ!» ይባባላል። ለሁሉም አዲስ በሆነው ባለቀለም መብራት፤ ከሜሪ ሴቶች ውበትና አርቲስቶቹ ጋር ተደማምሮ ከቤቱ የሚተነው እንፋሎት ሌላ ነው። እዚህ ጋር አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በ«ትኩሳት» መጽሐፉ ውስጥ ውቤ በረሃ እያለ የሚገልጸው ያ ስፍራ ምናልባትም ከሜሪ አርምዴ ቡና ቤት ውስጥ ሳይሆን እንዳልቀረ ጠረጠርኩ። ሜሪ በአዲስ አበባ ምድር ቡና ቤት ለመክፈትም ሆነ ባለቀለም መብራት ለመጠቀም የመጀመሪያዋ ናት። በኋላ ላይ ሜሪን የተመለከቱ ባለሀብቶች አንድ ሁለት እያሉ ቡና ቤት መክፈት ጀመሩ። እየተበራከቱም መጡ። በዚሁ መጠን ረብሻና ሁካታው በዛ። የማታ ማታ የከተማዋ አዳር፤ የውሻ መንጋ ሲናተፍ እንደሚያድርበት የቄራ መንደር መሰለ። በዚህ ጊዜ ሕጉም ጠበቅ አለና ክልከላው በዛ። ሴቶቹ ለብሰው የሚወጡት፤ በብዛት በውስጥ ልብሶች ብቻ ነበርና ይህ እንዳይሆን ክልከላ ተደረገ። በግለት የነበረው የሜሪ ቡና ቤት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዝቀዝ ማለት ጀመረ። ብዙዎችም «ሜሪ ጥዩፍ ናት … ሰው ትንቃለች፣ ትኮራለች…» እና መሰል የጎረምሶች ንዝንዝም፤ ዛቻና ማስፈራሪያ እየበዛበት መጣ። ሜሪም ከሁሉም ለመገላገል ስትል ቡና ቤቷን ዘግታ ቁጭ አለች። ያ ሁሉ ያጅባትና ሲጋፋላት የነበረ ሁሉ ጥሎ ጠፋ። ያሠለጠነቻቸው ቆነጃጅትም የራሳቸውን ቡና ቤት ከፍተው ባለሀብት ሆኑ። እርሷ ግን፤ ከስኬት ማማ ላይ ቁልቁል እየወረደች፤ ከአቧራው መሬት ላይ አረፈች። ዘውድና ጎፈር በአንድ የሕይወት ጀንበር። ገቢ ለማግኘት ስትል ጸጉር ቤት ከፈተች። በዚህም የመጀመሪያዋ በሆነችበት፤ በዘመናዊ የጸጉር ሙያዋ የአዲስ አበባን ሴት በሞላ አበባ ብታስመስልም፤ የእርሷ ሕይወት ግን ቁልቁል መምዘግዘጉን ሊያቆም አልቻለም።

በአንድ ወቅት የደቡብ አፍሪካዋ ማሪያም ማኬባ ለስብሰባ አዲስ አበባ በመጣችበት ጊዜ ‹‹ያቺን በዝና የሚወራላትን ሜሪ አርምዴን ሳላይ ወደ ሀገሬ አልመለስም›› በማለት ካለችበት ካላሳያችሁኝ አለች። ጋዜጠኞችም መርተው ቤቷ ድረስ ይዘዋት መጡ። ሜሪ የነበረችው፤ ድር ባደራበትና አቧራው ለአፍንጫ በሚሰነፍጥ ጉስቁልቁል ባለ ቤት ውስጥ ከአንዲት አልጋ ጋር ነበር። «እዚህ ቤት ውስጥ ነው የምትኖሪው?» አለቻት ማሪያ ማኬባ። «አይ፤ ይሄ የገረዴ ቤት ነው። ስለታመመችብኝ ልጠይቃት መጥቼ ነው» በማለት ትመልሳለች። ጉደኛዋ ሜሪ፤ ለካስ ሠራተኛዋን እንድተውንላት ለምና በማሳመን በብርድ ልብስ ጀቡና አስተኝታት ነበር። ከብርድ ልብሱ ስር ሆና ለጉድ ታቃስታለች። ሜሪም እንዲህ ነበር ያስታወሰችው፤ «እሷም እንዳልኳት ኧኧኧ ስትል ማርያም ማኬባ አዘነችና ሃምሳ የአሜሪካን ብር አንስታ «እንቺ ስጫት» አለችኝ። እኔም ያቺን ብር «የኔ ገንዘብ ነው በኋላ ትሰጭኛለሽ» ብዬ ትራስዋ ሥር አስቀመጥኩ። በኋላም ቤትሽን አሳይኝ ብትለኝ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር አጠገብ ያለውን የበድሉን ሕንፃ የኔ ነው ብዬ ነገርኳት። ‹‹እናትና አባቴ ስለርስት ጉዳይ ንትረክ ይዘዋልና ፀጥታ እንነሳቸዋለን። እሁድ እራት ጋብዤሻለሁና እንዳትቀሪብኝ አልኩና ተሰናበትኳት። ግብዣውን የት አባቴ እንደማዘጋጅ ግራ ገባኝ። ምን ይዋጠኝ? ምነው ያችኑ አነስተኛ ቤት የኔ ነች ባልኩ፤ እያልኩ ስጨነቅ አንድ የማውቃቸውን ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውን ሰው ላስቸግር ወሰንኩ። እቤታቸው ሄጄ እግራቸው ላይ ወድቄ አለቀስኩ። ታሪኩንም ዘርዝሬ ነገርኳቸው። እሳቸውም በነገሩ ተደንቀው፥ ደግሰው፥ ቤቱን በደንብ አድርገው አዘጋጁልኝ። ከዚህም ሌላ ማርያም ማኬባን ከሆቴሏ የሚመጣት መኪናና ሾፌር ሰጡኝ። እኔም የእሳቸውንና የባለቤታቸውን ፎቶግራፍ ከግድግዳው ላይ አንስቼ የኔን ፎቶ አደረግሁ። የራሴ ቤት ለማስመሰል ፒጃማ ለበስኩ። ልክ እንደቤቴ ሽር ጉድ እያልኩ ጋበዝኳት። ሾፌሩንም አስቀድሜ ለምኜው ነበርና ከእራት በኋላ እሷን ለማድረስ ስንወጣ ወርዶ እጅ ነስቶ፥ መኪና ከፍቶ አስገባን። ሆቴሉም ስንደርስ ሮጦ ወጣና ከፈተልን። በመጨረሻም የሀገር ልብስ ጥሩውን በርካሽ ዋጋ ገዝቼ ሸለምኳት። እሷም ቆንጆ የደረት ጌጥ ሸለመችኝ። እባክህ ጌታዬ አታጋልጠኝ ብዬ ለቁልቢው ገብርኤል ጥላና ጧፍ ተስዬ ነበር። ሳልጋለጥ ቀረሁ» ይህን ማድረጓ፤ ይህችን ያህሏ ዝነኛ የምትኖረው በዚህ ቤት ነው ብላ የሀገሯን ስም በድህነት እንዳታጠለሽ ስለፈራች ነበር።

ሜሪ አርምዴ፤ በሁሉ የተሰጠች ናትና ማዘጋጃ ቤት ተቀጥራ ሴቶችን በዘመናዊ ፋሽን ማሰልጠን ጀመረች። ከዚያም ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት አቅንታ በዚያም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ባላት ሙያ ሁሉ ስታገለግል ቆየች። የቴዎድሮስ ቴአትር ሲሠራ ሹሩባውን እንዲያ አሳምራ የሠራችው ሜሪ አርምዴ ነበረች። በሃኒባል ቴአትርም አልባሳቱን ያዘጋጀችው እርሷው ናት። በዚህ ሁሉ ግን አብዛኛውን ሥራዎች የምትሠራው በነፃ ነበር። ነገሮች እየከፉ ቀኑም እየጨለመ መጣ። በጭቃ ወደተመረገው ወደ አፈሩና ጭር ወዳለው ቤቷ ገብታ ቁጭ አለች። መከፋትና ድብርቱ ተጫጫናት። ያላት ብቸኛው ነገር «ባሌም፤ አባቴም ወንድሜም እሱ ነው» የምትለው ያ ክራሯ ብቻ ነበር። በዥንጉርጉር ቀለም አጊጦ ከትራስጌዋ ተሰቅሏል። ሆድ ሲብሳት ከተሰቀለበት እያወረደች ብሶት መከፋቷን ትገልጽበታለች። ከፋኝ ብላ የምትነግረው የምታዋየው እንኳን አልነበራትም። ወዳጆቿ የነበሩትም ሜሪን የሚመለከቷት፤ ክራሯን ይዛ አንዳንዴ ከቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ስትል ነው። ድምጽዋንም የሚሰሙት ከራዲዮን ላይ ስታንጎራጉር እንጂ ቤቷ ጎራ ብሎ የሚጠይቅ አነበረም።

«ዛፍ ያጣ ጉሬዛ አዳኝ ያበረረው የማትሆነኝ እንደሁ ልቤን ተው ልበለው

ጐጃምና ጐንደር ማዶ ለማዶ ነው ፍቅር ያለቦታው አባ ጨጓሬ ነው»

እያለች እንዳንጎራጎረች፤ ክራሯን ስትከረክር እንደኖረች፤ ኖራ ኖራ ከዚያው ደሳሳ ቤቷ አለፈች! ይህቺ ኦና ቤትም፤ ዛሬም ድረስ በፒያሳ ጊዮርጊስ ወገብ ላይ በትዝብት እንደቆመች አለች። እሷ ግን በክራር ጀመራ፤ በክራር ጨረሰች።

 ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You