አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ እና በዓለም ባንክ መካከል የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ማህበረሰብ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የሚውል የ350 ሚሊዮን ዶላር የብድር እና የድጋፍ ስምምነት ትናንት በገንዘብ ሚኒስቴር ተፈርሟል።
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና በዓለም ባንክ በኩል በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ሚስ ካርሎይን ቱርክ ፈርመውታል።
ከተፈረመው የ350 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት 280 ሚሊዮን ዶላሩ በረጅም ጊዜ የሚከፈል እና ቀላል ብድር ሲሆን፣ ቀሪው 70 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በድጋፍ መልክ የተሰጠ መሆኑ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።
ወደ 10 ቢሊዮን የኢትዮዽያ ብር የሚገመተው ይህ ስምምነት በሶማሌ፣ አፋር ፣ በኦሮሚያ ቆላማና አርብቶ አደር አካባቢዎች፣ በደቡብ አርብቶ አደር አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረውን የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ፕሮጀክት የሚተካና ሰፋ ያሉ የልማት ሥራዎችን በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ለማካሄድ የሚያስችል ነው።
ፕሮጀክቱ በግጦሽና መሰረተ ልማት፣ በግብይት እና ተያያዥ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በስፋት በመሥራት አካባቢዎቹ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።
ስምምነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በመጪው ዓመት ወደ ትግበራ እንደሚገባ የገለፁት አቶ አህመድ ሽዴ ለስድስት ዓመታት የሚቆይም ይሆናል ብለዋል።
ከሁለት ሚሊዮን በላይ የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው ፕሮጀክቱ በብድር የተሰጠው ገንዘብ በ 40 ዓመት ውስጥ የሚከፈልና ቀላል ከሚባሉት የሚመደብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ብድሩ በሀገሪቱ ኢኮኖሚና ብድር የመክፈል አቅም ላይ ተፅዕኖ የማያሳድር ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011
በድልነሳ ምንውየለት