የ«ሶዳ አሽን» ፍላጎት -በሀገር ውስጥ ምርት

በኢትዮጵያ ከሚገኙና እንዲለሙ ከተደ ረጉ በርካታ ማዕድናት መካከል ሶዳ አሽ የተሰኘው ማዕድን አንዱ ነው፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የሶዳ አሽ ማዕድን ክምችት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ማዕድኑ በብዛት ይገኝባቸዋል ተብለው በጥናት ከተለዩት ቦታዎች መካከል መንትዮቹ በመባል የሚታወቁት የአብያታ እና የሻላ ሐይቆች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢም እንዲሁ ማዕድኑ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሶዳ አሽ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት ይውላል፤ ለሳሙና፣ ጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ ብርጭቆ እና ወረቀት ፋብሪካዎች በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማዕድን በተፈጥሮ በአፈር መልኩ ተቆልሎ እንዲሁም በሐይቅ ውስጥ ይገኛል።

አሁን ላይ እንደ ሀገር እየለማ ያለው ሶዳ አሽ ማዕድን ግን በሐይቅ ውስጥ የሚገኘው ነው። ማዕድኑ እንዳለበት የተለየው ውሃ በተለያዩ ኩሬዎች እንዲጠራቀም ይደረጋል፤ ውሃው በፀሐይ ብርሃን እንዲተን የማድረግ አሠራርን በመከተል ሶዳ አሹን የመለየት ሥራ ይከናወናል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በአብያታና በሻላ ሕይቅ ከ380 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የሶዳ አሽ ማዕድን ክምችት ይገኛል። በእነዚህ ሐይቆች ላይ ማዕድኑን ለማምረት የሚያስችለውን ፈቃድ ወስዶ እየሠራ ያለው የአብያታ-ሻላ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማኅበር ነው። ማኅበሩ በሜድሮክ ኩባንያና በመንግሥት ሼር የተቋቋመ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ፋብሪካ በመገንባት የሶዳ አሽ ማዕድን የማምረት ሥራውን እያካሄደ ነው፡፡

የአብያታ ሻላ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማኅበር የንግድ ሥራ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ገመቹ ነገራ እንዳስታወቁት፤ ማኅበሩ የሶዳ አሽ ማዕድን ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ በመገንባት ወደ ምርት ከገባ ቆይቷል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በሶዳ አሽ ማዕድን ሥራ ላይ እንዲሰማራ ካስቻሉት ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ በአብያታና ሻላ ሐይቆች ያለው ሰፊና እምቅ የሶዳ አሽ የማዕድን ክምችትና ምርቱ የሚፈልጉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በመኖራቸውም ነው፡፡

አቶ ገመቹ ቀደም ብሎ የተደረገ ጥናትን ዋቢ በማድረግም ስለማዕድኑ ሲያብራሩም እንደ ሀገር በዚህ ማዕድን ልማት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚቻልና የሚመረተው የሶዳ አሽ ማዕድንም ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከማዋል ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ገመቹ ገለጻ፤ ‹ሶዳ አሽ› Soda ash (Na2CO3) ሲባል ማዕድኑ ያለበትን ውሃ ከሐይቅ ስቦ በማውጣት በኩሬ እንዲታቆር ከተደረገ በኋላ በፀሐይ ኃይል ውሃው እንዲተን ሲደረግ የሚቀረው ቶሮኖ ይባላል፡፡ ቶሮኖ በመባል የሚታወቀው ሶዳ አሽ የተሰኘው ማዕድን በውስጡ ባይካርቦኔት፣ ሶዴየም ባይካርቦኔት፣ የተሰኙ ማዕድናትን ይይዛል፡፡ ይህም በላቦራቶሪ እንዲታይ ተደርጎ ትክክለኛው የሶዳ አሽ ማዕድን እንዲመረት ይደረጋል፡፡

ሶዳ አሹ በሽርክት ወይም በደቀቀ መልኩ ተፈጭቶ ለገበያ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቅሰውም፤ ለሳሙና እና ለዲተርጀንት፣ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለቆዳ፣ ለብርጭቆና ለወረቀት ፋብሪካዎች በጥሬ በግብዓትነት የሚውል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይ የሳሙና እና ለዲተርጀንት ፋብሪካዎች ትልቁ ግብዓት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚህ የማዕድን አወጣጥ ሂደት ምንም ዓይነት ኬሚካል ሥራ ላይ እንደማይውል ጠቅሰው፣ አካባቢውን የመበከልም ሆነ ሌላ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያደርስም ይገልጻሉ፡፡

የሶዳ አሽ ማዕድን ለማምረት የታቆረው ውሃ በፀሐይ ኃይል አማካይነት እንዲተን ይደረጋል። ማዕድኑ ጨዋማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሶዳ-አሹ ከጨው በላብራቶሪ ይለያል፤ በመቀጠልም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት እንዲውል በሚፈለገው መጠን እንዲዘጋጅ ይደረጋል። ኢንዱስትሪዎች የሶዳ-አሽ ምርት ሲፈልጉ በሚያቀርቡት ዝርዝር የመጠን መገለጫ የሚፈልጉት ያህል መጠን በላቦራቶሪ ተለይቶና ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብላቸው ነው ያስረዱት፡፡

ፋብሪካው እስካሁን ሶዳ አሽ የማምረት ሥራውን በአብያታ ሐይቅ ላይ እየሠራ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞች እና በርካታ ጊዜያዊ ሠራተኞችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ገመቹ ገለፃ፤ ሶዳ አሽ የማምረቱ ሥራ ዝናብ ካልበዛ በስተቀር በስፋት ይካሄዳል፤ ከዝናብ መብዛት ጋር በተያያዘ ግን የሚስተጓጎልበት ሁኔታ ያጋጥማል። ለአብነትም ዘንድሮ የክረምት ወቅቱ በመረዘሙ ምክንያት ማዕድን ያለውን ውሃ ከሐይቅ በማውጣት በኩሬ እንዲታቀፍ ቢደረግም፣ እስካሁን ውሃው በፀሐይ ኃይል ሊተን ባለመቻሉ የሚፈለውን ያህል ማዕድን ለማግኘት አልተቻለም፡፡ በማዕድን ማውጣቱ እንዲካተት የሚያስፈልገው ቶሮኖ የተባለው ተፈላጊ ነገር ሳይሠራና የፀሐይ ኃይል ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ውሃ በሚሸሽት ወቅትም እንዲሁ ምርቱ እንደማይመረት ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ውሃ የሸሸበት ሁኔታ ተከሰቶ እንደነበርም አቶ ገመቹ አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ድርጅቱን ለተለያዩ ተደራራቢ ወጪዎች እንደሚዳርጉትም ያመለክታሉ፡፡ የክረምቱ ወራት በሚያጥርበት ጊዜ ግን የተሻለ ምርት ማምረት እንደሚቻል ገልጸው፤ በተለይ በባለፈው አመት አስደሳች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

ሶዳ አሽ የማምረቱ ሂደት በተፈጥሮ ላይ መሠረት እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ በመጀመሪያው ስድስት ወራት የተፈለገውን ያህል ምርት ባይመረትም፣ በቀጣይ ስድስት ወራት ያለው የአየር ንብረት እየተስተካከለ ሲሄድ ሶዳ አሽ ለማምረት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ያን ጊዜ ፋብሪካው ወደ ማምረት ሥራው በስፋት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዚህ የማዕድን ልማት ሥራ ያጋጠሙ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሌሉ የሚናገሩት አቶ ገመቹ፤ ለልማት ዋንኛ የሆነው እንደ ሀገር እየታየ ያለው የሰላምና የመረጋጋት ችግር አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በሀገራችን ያለው የሶዳ አሽ ማዕድን ከፍተኛ ክምችት በዘርፉ ለመስማራት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል›› ያሉት አቶ ገመቹ፤ በማዕድን ሥራው ልምድ ያላቸው ሰዎችን ማግኘት መቻሉ በቀላሉ ወደ ሥራው መግባት ማስቻሉንም ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ገመቹ ገለፃ፤ የሶዳ አሽ ማዕድን አስፈላጊና ለተለያዩ ምርቶች በጥሬ ግብዓት ያገለግላል፡፡ ፋብሪካው ደግሞ ሶዳ አሽን በማምረት ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ያቀርባል። ይህም ማዕድኑን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል አቅም ከመፈጠር ባሻገር ምርቱን ከውጭ ለማምጣት ይውል የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል፡፡ ምርቱን ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማግኘትም የሚያስችል አቅምን ይፈጥራል፡፡

‹‹የሶዳ አሽ ከተመረተ በኋላ ፈላጊዎቹ ብዙ ስለሆኑ በቀላሉ ገበያ ማግኘት ችለናል›› ያሉት አቶ ገመቹ፤ ከአምራቹ የሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ከፍ በማድረግ ፋብሪካዎች በሚፈልጉት መጠን ማምረት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በአፍሪካ ቀንድ እንደኬንያ ያሉ ሀገራት ሶዳ አሽን በማምረት የሚታወቁ ሲሆን፤ ቻይናም በእዚህ ምርት ትጠቀሳለች፡፡ ቀደም ሲል ሶዳ አሽ በጥሬ ግብዓትነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ይህን ግብዓት ከቻይናና ከኬንያ እያስመጡ ይጠቀሙ እንደነበር አቶ ገመቹ አስታውሰው፤ የአብያታ-ሻላ የሶዳ አሽ ፋብሪካ ከተቋቋመ ጊዜ ወዲህ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች የሚፈለጉትን የሶዳ አሽ መጠን በዝርዝር አቅርበው ምርቱን የሚወሰዱበት አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ገመቹ ማብራሪያ፤ የሶዳ አሽ ማዕድን ምርት እጅግ ተፈላጊና የበርካታ ፋብሪካ ግብዓት ሲሆን፣ ፋብሪካውም ይህንን ምርት የሚያመርተው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ከውጭ የሚመጣውን የሚስተካከል ምርት ያመርታል። ሀገር ውስጥ ላሉ ፋብሪካዎች በሚፈለጉት መጠንና ጥራት ምርቱን ለማቅረብ በላቦራቶሪ ተፈትሾ የሚወጣ ስለሆነ እስካሁን በዚህ ዙሪያ ፋብሪካው ችግር አልገጠመውም፡፡ በቀጣይ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት በማምረት በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን፤ ጥራቱ የሚለካበትን የተሻለ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸው የላቦራቶሪ መሣሪያዎች ለማስገባት ታቅዷል፡፡

‹‹ድርጅቱ በማዕድን ልማት ላይ ከመሰማራት ባሻገር በአካባቢው ያለውን ኅብረተሰብ የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ረገድም እየሠራ ነው›› ይላሉ። በዚህም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ የማዕድን ልማቱ በሚሠራበት ቦታ ላይ ያለው ኅብረተሰብ የሚፈለገውን የጤና፣ የውሃ እና የመሳሰሉት መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ሲያቀርብ ድርጅቱ በሚችለው አቅም ልማቱን በማገዝ ከኅብረተሰቡ ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የሶዳ አሽ ማዕድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ አመላካቾች አሉ›› ያሉት አቶ ገመቹ፤ ለአብነት በአፋር ክልል ውሃ ማቆርና ማትነን ሳይጠበቅበት ራሱ በተፈጥሮ ቶሮኖ በመባል የሚታወቀው ተዘጋጅቶ በአፈር መልክ ተቀምጦ እንዳለ መረጃዎች አጣቅሰው ይናገራሉ፡፡ ይህም በሌሎች አካባቢዎችም ጥናት ቢደረግ ማዕድኑ ሊገኝ እንደሚችል እንደሚያመላክት ይገልፃሉ፡፡

ሀገሪቱ ብዙ የማዕድን ሀብት እንዳላት ቢነገርም እየተሠራባቸው ያሉት ወርቅና በመሳሰሉት ላይ ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሀገሪቱ ያላት እምቅ የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ባለሀብቶች፣ ዲያስፖራዎች ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው ቢሠሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በተሰጠን የማዕድን ሀብት ላይ ብንስራና ብንጠቀመበት ጥሩ ለውጦችንና ውጤቶችን ማምጣት እንችላለን›› ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

የማዕድን ሀብቱ ትልቅ ኢንቨስትመንት ቢሠራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችል ዘርፍ ነው ያሉት ገመቹ፤ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡

በቀጣይም ሁለተኛውን የሻለ ሐይቅ ፕሮጀክት ለመጀመር ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ሻለ ሐይቅ ሰፊ ማዕድን ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰፊ ሥራዎች ለመሥራት ያስችላል ብለዋል። ከሶዳ አሽ ምርት ለሀገር ውስጥ ግብዓትነት ከመጠቀም ባሻገር ለውጭ ገበያ የመላክ እቅድ ተያዞ እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ሥራ ሲጀምር ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ሲሉ ነው አቶ ገመቹ ያስገነዘቡት፡፡

ከኃላፊው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፤ ሶዳ አሽ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሲገባ የቆየ ሲሆን፣ ፋብሪካው ይህን ከውጭ ሀገር የሚመጣውን የሶዳ አሽ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን ችሏል፡፡ ከዚህ አልፎም ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ተመላክቷል።

ይህ ፋብሪካው እያከናወነ ያለው ተግባር መንግሥት ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳን ለያዘው አቅጣጫ ትልቅ አቅም በመሆን ያገልግላል፡፡ ፋብሪካው ይህን ሥራውን በሻላ ሐይቅ በማስፋፋት ሀገርን መደገፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በአብያታና በሻላ ሕይቅ ከ380 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የሶዳ አሽ ማዕድን ክምችት ይገኛል፤

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You