በርካታ የህይወት ፈተናዎችን ማለፉን ይናገራል። ከቤተሰብ ተለይቶ በተቀጣሪነት የግብርና ስራ ከመከወን አንስቶ እስከ ባህል ጭፈራ ቤት ከፍቶ እስከመስራት ያደረሰ የህይወት መንገድን ተጉዟል። ከስራ ባልደረቦች ድብደባ እስከ መደብ አዳሪነት የደረሰ የችግር ጊዜንም አሳልፏል። በሌላ በኩል ግን በመንፈሰ ጠንካራነቱ ደግሞ የሚያውቁት ብዙዎች ናቸው።
አሃዱ ብሎ የጀመራት የሻይ ቤት ንግድ አሁን ላይ የባህል ቤት እና የአልባሳት መሸጫ ሱቅን አበርክታለት የተመቻቸ ኑሮን እየኖረ ይገኛል። ሁልጊዜም አላማው ሰርቶ የተሻለ ገቢን ማግኘት እንደሆነና ለዚህም ሁልጊዜም ደፋ ቀና እያለ መሆኑን ይናገራል። ሙሉ ስሙ አቶ ባይሌ ፈንታ ይባላል። በደብረማርቆስ ከተማ የሚገኘው የጎዛምን ባህል ጭፈራ ቤት ባለቤት ነው።
አቶ ባይሌ ተወልዶ ያደገው በጎዛምን ወረዳ ጭንቦርዴ በተባለው አካባቢ ነው። በልጅነቱ ለቤተሰቡ ከብቶች በማገድ እና የተለያዩ ስራዎችን በመከወን እያገለገለ ቢኖርም እድሜው ለአቅመ አዳም ሲደርስ ግን በቤተሰብ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ወላጆቹን መለየት ግድ ሆነበት። ከ25 ዓመታት በፊት ቤተሰቡን በገቢ ለማገዝ የእራሱን ስራ መስራት እንዳለበት ይወስናል። በመጀመሪያ ያመራው ደግሞ በትውልድ አካባቢው ወደሚገኙ የእርሻ ባለቤቶች ዘንድ ነው።
እናም በችግር ምክንያት የሰው እጅ ከማየት ተቀጥሮ በግብርና ስራ በማገልገል የአሰሪዎቹን መሬት ማረስ መርጧልና ውሎው ከቀጣሪዎቹ መሬት ላይ ሆኗል። የሰው ቤት ኑሮ ቢከብደውም ቻል አድርጎት ጥቂት ብትሆንም ገንዘብ መቋጠሩን ተያይዞታል። ከእናት ቤት እንጀራ ናፍቆት እና የቤተሰብ ፍቅር ሆዱን ቢያላውሰውም የአሰሪዎቹን ፀባይ እና ቁጣ ችሎ ለአራት ዓመታት እርሻውን ሳያስታጉል ሰራ።
ከዚህ በኋላ ግን የእርሻ ስራውን ጥሎ ወደ ደብረማርቆስ ከተማ ለመግባት ልቡ ከጅሏል። እናም የነበረችውን ጥቂት ጓዝ ጠቅልሎ የቀን ስራ ለመስራት በሚል እቅድ ወደ ምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ መዳረሻውን አደረገ። ከተማዋ ግን እጇን ዘርግታ አልተቀበለችውም። ይልቁንም ስራ ፍለጋ በሚሯሯጥበት ወቅት የሚላስ የሚቀመስ ባለማግኘቱ ለሁለት ቀናት እህል ሳይቀምስ መቸገሩን ያስታውሳል። ለተወሰኑ ጊዜያት የሚሰራው አጥቶ የመደብ አልጋ ብቻ እየከፈለ ቢኖርም ቀስ በቀስ ግን ወደ ሸክም ስራ ማምራቱ አልቀረም።
በአካባቢው በሚገኙ የእህል ጫኝ እና አውራጅ ስራ ከተሰማሩ ጋርም ጠጋ ብሎ እየሰራ የተወሰኑ ብሮችን ማግኘት ጀምሯል። እናም በተባራሪነት የሚያገኘውን የጫኝና አውራጅነት ስራ ከወጣቶቹ ጋር በማህበር ተደራጅቶ ለማጠናከር ሲፈልግ ግን እርሱን ገለል አደረጉት። በዚህ የተበሳጨው ባይሌ በየጊዜው ከጫኝና አውራጆች ጋር ፀብ ውስጥ መግባቱ አልቀረም። እኔም ማህበሩ ውስጥ መግባት አለብኝ ብሎ በማመጹ ደግሞ ጊዜ ጠብቀው ከበው ደበደቡት።
በድብደባው የተጎዳው የጎዛምኑ ሰው ታድያ በቶሎ ማገገም አልቻለም። በወጣቶቹ እርግጫ እና ዱላ የተጎዳው ሰውነቱ እስኪያገግም ለአንድ ሳምንት ያክል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት በሆስፒታል ውስጥ ነበር እንዲያሳልፍ ያስገደደው። ከህመሙ ሲያገግም ግን ለበቀል በመነሳሳት አንካሴ ገዝቶ አንዱን ጫኝና አውራጅ ወግቶ ሊሸሽ አሰበ። በዚህ ወቅት ታድያ ሽማግሌዎች መሃል ገብተው የተጣሉትን ሁሉ በማስታረቃቸው ሰላም ሊወርድ ቻለ። ከእርቁ በኋላ አቶ ባይሌም በጫኝና አውራጅ ማህበሩ ገብቶ እንዲሰራ ስምምነት ተደረገ።
ለስድስት ወራት ግን ቋሚ አልሆንክም በሚል ከሌሎቹ ወጣቶች በግማሽ ያነሰ ብር ነበር የሚሰጠው። እኩል የሸክም ስራ ቢሰሩም እነርሱ 100 ካገኙ እርሱ 50 ተቀብሎ ወደ ተከራያት ቤት ያመራል። እንዲህ እንዲህ እያለ ታግሶ ለስድስት ወራት እንደሰራ ቋሚ በመሆኑ ከስራ ባልደረቦቹ እኩል ክፍያ ማግኘት ቻለ። በዚህ ወቅት ግን በልጅነቱ ያላገኘውን የትምህርት ዕድል በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ማሳካት እንዳለበት ወስኗልና ወደ አስኳላ ለማምራት ተመዘገበ። ትምህርቱ ደግሞ የማታ ነበርና ጫኝና አውራጅ ማህበሩ አባላት እንዲማር ነገሮችን ከማመቻቸት ይልቅ አከበዱበት።
በጊዜ ከስራ ቦታ እንዳይወጣ የሂሳብ መሰብሰብ ስራውን ደርበውበት ሂሳቡን ሲደማምር የትምህርት ጊዜው ያልፍበት ጀምሯል። ያም ሆነ ይህ ግን ጫናውን ተቋቁሞ በሚመቹት ቀናት እየሄደ አንድ ብሎ የጀመረውን ትምህርት እስከ ስምንተኛ አደረሰ። ሚስት አግብቶ ኑሮውን የተረጋጋ ያደረገውም በዚሁ ስራ ላይ በነበረበት ወቅት ነበር።
አንድ ቀን ግን ከባለቤቱ ጋር ቆይቶ ወደ ስራ ሲገባ የመንደር ዱርዬዎች የከተማዋን ታጣቂ መሳሪያ ነጥቀው ሲሮጡ ይመለከታል። ይህን እያየ ማለፍ ያልፈለገው ፈርጣማው ባይሌ ታዲያ ወጣቶቹን ተጋፍጦ መሳሪያውን አስጥሏቸው ይሄዳሉ። ይህ ተግባሩ በብዙዎች ዘንድ በመወደዱ ከጫኝና አውራጅነቱ በተጨማሪ የሚሊሺያ ስራ እንዲሰራ ተፈቅዶለት ሚሊሻ ሆነ።
በሚሊሻነቱ ለሰድስት ወራት እንደሰራ ባገኛት የቀበሌ ቤት ደግሞ ወደ ንግድ ስራው ለመሰማራት ወስኗል። አነስተኛ ብርጭቆ እና ሻይ ማፍያ ዕቃዎችን በማሰናዳት ከከባለቤቱ ጋር ሆኖ አነስተኛ ሻይ ቤት በመክፈት የንግዱን ዓለም ተቀላቀለ። ትምህርቱንም በተጓዳኝነት እያስኬደ ስምንተኛ ክፍል ቢደርስም ከዚህ በላይ መቀጠል ግን አልቻለም። ይልቁንም የንግድ ህይወቱን ጠበቅ አድርጎ መያዙን ነው የመረጠው።
በሻይ ቤቱም ዳቦ፣ ቦንቦሊኖ እና የተለያዩ የለስላሳ መጠጦችን በማቅረብ ገቢን ማሳደግ ቻለ። በወቅቱ ከሚያገኘው ገቢ እቁብ ይጥል ነበርና ተራው ሲደርሰው ተጨማሪ የንግድ ቤት የሚከፍትበት እድል ተፈጠረለት። በደብረማርቆስ ከተማ 14 መኝታ ክፍሎች ያሉት የንግድ ቤት በ1500 ብር በመከራየት የንግድ ስራውን አጠናከረው። አንዱን አልጋ በ15 ብር በማከራየት የሚያገኘውን ገቢ በሳምንት የሁለት ሺህ ብር እቁብ በመጣል ገንዘቡን ለተሻለ ህይወት ያመቻች ጀምሯል።
ለሶስት ዓመታት ንግዱን እንደሰራ ደግሞ አሁንም በዕቁብ ገንዘብ 40ሺህ ብር አውጥቶ መሬት መግዛቱን ያስታውሳል። ለአቶ ባይሌ እቁብ ወሳኝ የንግድ ስራ ማሳደጊያ መንገድ ነው። ከመደብ አዳሪነት እስከ እህል ተሸካሚነትን ያለፈው ባይሌ አሁን የተደላደለ ቤተሰብ መስርቷል። በተጨማሪም አራት መቶ ሺህ ብር አውጥቶ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመግዛት የትራንስፖርት ንግዱን ተቀላቀለ። ይሁንና የተሽከርካሪዋ ገቢ አትራፊ ባለመሆኑ ሸጦ ንግዱን ማጠናከሩን ተያያዘው። በሻይ ቤቷ ስራ ደግሞ የአልኮል መጠጦችን በመሸጥ ገንዘብ መሰብሰቡን ተያይዞታል።
ከዚህም አልፎ ጎዛምን የተሰኘ የባህል ጭፈራ ቤት ከፍቶ ጎብኚዎችን ብሎም በከተማዋ ለመዝናናት ጎራ የሚሉትን ሁሉ እየሳበ ይገኛል። በባህል ጭፈራ ቤቱ የአዝማሪ ምሽት በማዘጋጀት ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። በዚህም አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት መኖሪያ ቤት እስከመገንባት ያደረሰ ገቢ እንዳገኘ ነው የሚናገረው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ያለፈተና አልነበረም።
በአንድ ወቅት መዝናኛ ቤቱ ውስጥ በተነሳ ረብሻ ምክንያት አንድ ሰው ቢጎዳ ሁል ጊዜ እርሱ ቤት ረብሻ ይነሳል በማለት ንግዱ እንዲዘጋ የሚጥሩ በርካታ ሰዎች ነበሩ። በሌላ በኩል በሚሊሺያ ስራው አማካኝነት የኮንትሮባንድ ቡና እየያዘ እኩል ከአዘዋዋሪዎቹ ጋር በመካፈል ነው ሀብት ያገኘው በሚልም በሚሊሺያ ስራው ላይ ግምገማ የሚያቀርቡ ሰዎች አልጠፉም።
በተለያየ ምክንያት የንግድ ቤቱ ደንበኞች እንዲቀንሱ አንዳንድ ሰዎች ቢጥሩም ባይሌ ግን የሚሸነፍ አልሆነም። ይልቁንም በንግድ ስራው ላይ ተጨማሪ ዘርፎችን እያከለ ብርታቱን ያሳይ ቀጥሏል። የከተማው ገበያ ስፍራ ላይ የተዘጋጁ አልባሳትን ለንግድ የሚያቀርብበት ሱቅ በመክፈት የተለያዩ አይነት አልባሳትን ይሸጥ ጀመረ። ከአዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ እና መርካቶ እየተጓዘ የሚያስመጣቸውን አልባሳት በሱቁ በማቅረብ ዘርፈ ብዙ ንግዱን ማቀላጠፉን ተክኖበታል።
አሁን የባህል ቤቱን እየተቆጣጠረ የማስፋፊያ ህንጻ ግንባታውን በንግድ ቤቱ ጀርባ ያከናውናል። በዋናነት ግን አራት ወለል ያለው ህንጻ ለመገንባት ነው እቅዱ። ህንጻው ስምንት ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ የገመተው አቶ ባይሌ ህንጻው በቀጣይ ዓመታት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት እና በሆቴል ዘርፉም የበለጠ ለመስራት እንደሚያነሳሳው ይገልጻል።
የአቶ ባይሌ የባህል ምሽት፣ የአልባሳት መሸጫ እና ሻይ ቤት በስራቸው ያሉ ሰራተኞችን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛል። እርሱ ስራ አጥቶ ከመንከራተት ባለፈ በቂ ገቢ ሳይኖረው ያሳለፈውን የመከራ ህይወት መቀየር በመቻሉ ደስተኛ ነው። አሁን ላይ አጠቃላይ ሀብቱ 13 ሚሊዮን ብር አካባቢ መሆኑን የሚገምተው አቶ ባይሌ ከዚህም በላይ የተሻለ ገቢ እንደሚኖረው በማሰብ በየዕለቱ ያለመታከት እንደሚሰራ ይናገራል።
ማንኛውም ሰው ከትንሽ ተነስቶ የማደግ እድል አለው፣ ዋናው ጉዳይ አላማ እና ላሰቡበት ህይወት መሳካት የሚረዳ ጠንካራ የስራ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን አቶ ባይሌ ያስረዳል። እንደ እርሱ፤ ማንኛውም ሰው ድሃ ሆኖ ቢያድግም ሀብት ማፍራት እና ምቹ ኑሮ ማግኘት የሚችለው ቁጠባን መሰረት ያደገ ህይወት መምራት ሲችል ነው ።
በተለይ እቁብን ተጠቅሞ ለታለመለት አላማ ማዋል ከተቻለ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ህይወት ለተሻለ ስኬት የማብቃት ኃይል አለው። በመሆኑም በየቀኑ የምትገኝን አንድ ብር በማስቀመጥ አጠረቃቅሞ የተሻለ የስራ እድል መፍጠር ስለሚቻልበት መንገድ ማሳብ ለንግድ ህይወት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ምክር ይለግሳል። መልካም ሳምንት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ጌትነት ተስፋማርያም