ልጆችዬ እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ። “እንኳን አብሮ አደረሰን!!!” አላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ:: በዓሉ የሚመለከታችሁ እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? መንፈሳዊ ቦታ በመሄድ፣ ዘመድ በመጠየቅ፣ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ሰብሰብ ብላችሁ እየተጫወታችሁ፣ እየተዝናናችሁ እና እየተደሰታችሁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም::
አንዳንድ የታደሉ ሰዎች ደግሞ ይህንን በዓል የታመሙ ሰዎችን፣ አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣ በመርዳት፣ እና በማዝናናት በደስታ ያሳልፋሉ:: ልጆችዬ የገና በዓል በሀገራችን በደማቁ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው:: ታዲያ ልጆችዬ የገና በዓል በሀገራችን በተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች በድምቀት ይከበራል:: በአብዛኞቹ ቦታዎችም በወጣቶች ጭፈራ፣ ደስታ፣ የገና ጨዋታ በመጫወት እና በመንፈሳዊ ዝማሬ እንደሚከበር ይታወቃል::
በዚህ በዓል ዘመድ ከዘመዱ፤ እንዲሁም ከጎረቤቱ ጋር በጋራ በመብላት፣ በመጠጣት፣ ቡና በማፍላት አቅም ያለው በግ፣ ፍየል፣ ዶሮውን ገዝቶ፣ ቤቱን አጽድቶ እና አስውቦ እንዲሁም ቅርጫ በመቃረጥ እንደሚያከበሩ ተመልክታችኋል ብዬ አስባለሁ:: እናም ልጆች እንደ ገና እና ሌሎች በዓላትን ጨምሮ በጋራ፣ በሰላም እና በፍቅር ሲከበር በባህላችን እንድንኮራ ያደርገናል:: ኧረ እንደውም ሁሌም ዓመት በዓል በሆነ ያስብላል አይደል?
ልጆችዬ ዶ/ር መጋቤ ሃዲስ ሮዳስ ታደሰ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ሥርጭት ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ምን አሉ መሰላችሁ? ከወደ ምሥራቅ ሀገር በኮከብ ብርሃን ተመርተው የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ምክንያት በማድረግ ወደ ቤተልሔም የመጡት የጥበብ ሰዎች ሰብአ ሰገል ይባላሉ:: እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ደስ ብሏቸው ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤም አምጥተው ስጦታ አበረከቱለት::
በርካታ ሰዎች የገና በዓል ሲቃረብ ስጦታዎችን ሲገዙ አይታችኋል አይደል ልጆች? በሌላ በዓላት ላይ የማይስተዋለው የስጦታ መስጠቱ ተግባር፤ በገና በዓል ላይ ጎልቶ መታየቱን ሰበአ ሰገል ለኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ከመስጠታቸው ጋር የሚያያዝ ታሪክ እንዳለው የሃይማኖት አባቶች ይገልፃሉ::
ልጆችዬ ስጦታ መሰጣጣት በሰዎች መካከል ፍቅር፣ መከባበር፣ መተሳሰብ እንዲኖር ያደርጋል:: ታዲያ እናንተስ ምን ሰጣችሁ? ምንስ ተሰጣችሁ? ቸኮሌት፣ ከረሜላ፣ ኮፍያ፣ ጌጣ ጌጥ፣ መጽሐፍ እና የተለያዩ ነገሮች እንደተሰጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ:: ይህ ዓይነቱ ባህል መቀጠል የሚገባው ነው አይደል? ‹‹በሚገባ!!!›› አላችሁ? ጎበዞች።
ልጆችዬ ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ሲባል ሰምታችኋል አይደል? ለምን ይመስላችኋል እንደዚህ የተባለው? የገና በዓል ከሃይማኖታዊ ትርጓሜው ባሻገር በማኅበራዊ ትስስር ላይ ሁሉም ሰው እኩል ሆኖ የሚደሰትበት፤ ጌታ እና ሎሌ እኩል ሆነው የሚያሳልፉት እንደሆነ ለማሳየት ነው::
በርግጥ የገና በዓል በተለያዩ ሀገራት ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበራቸውን ተከትሎ የባህል መኮራረጅ ይስተዋላል:: ልጆችዬ፣ የራስን ሳያውቁ የሌላውን አከባበርም ሆነ ባህል ለመኮረጅ፤ እንዲሁም ለማወቅ መጓጓት ተገቢነት አለው ብላችሁ ታምናላችሁ? ‹‹በፍጹም አናምንም::›› የሚል መልስ እንደምትሰጡኝ አልጠራጠርም:: እናም የገና ዛፍ፣ የገና አባት እና ሌሎችም የእኛ ባህል አይደሉምና እንዴት አድርገን የራሳችንን እንወቅ በሚለው ላይ መነጋገር ያስፈልጋል:: ለምሳሌ፣ በእኛ ሀገር በገጠሩ ክፍል ‹‹የገና ጨዋታ›› የሚባል አለ:: ስለዚህ ጨዋታ ምን ያህሎቻችሁ ታውቃላችሁ? ለምሳሌም በገጠሩ አካባቢ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ እረኞች የገና ጨዋታን ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ይጫወቱት እንደነበር ይነገራል::
አባቶቻችሁና እናቶቻችሁ ሲጨዋወቱ እንደምትሰሙት፣ ሀገራችን የበርካታ ታሪክ እና ባህል ባለቤት ናት:: እናም ወላጆች፣ መምህራን እና ሌሎችን ስለታሪካችን፣ ባህላችን እና የዓውደ ዓመት በዓላት እንዴት መከበር እንዳለበት በመጠየቅ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻላችሁ ሀገራችሁን፣ ባህላችሁን እና ታሪካችሁን በሚገባ ውደዱ እንላለን:: ልጆችዬ፣ ዛሬ ዓውደ ዓመትም አይደል? ደስ ብሏችሁ ዋሉ:: ታዲያ ስትመገቡ፣ ስትጫወቱ፣ ስትጠጡ እና ከቦታ ቦታ ስትንቀሳቀሱ በጥንቃቄ እና በአግባቡ መሆኑን አትርሱ እሺ? ልጆችዬ በድጋሚ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ እና የፍቅር እንዲሆንላችሁ በመመኘት በዚሁ እንሰነባበት::
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም