የአሜሪካው ግዙፍ አውሮፕላን አምራች የቦይንግ ኩባንያ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ኤጄሬ በተባለ ስፍራ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ ጠየቁ።
የቦይንግ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ ከሲቢኤስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ግለሰቦች ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ኃላፊው ከዚህ ቀደም በቪድዮ በሰጡት መግለጫ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ አሁን ላይ በይፋ ለሁለተኛ ጊዜ የሟች ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠይቀዋል።
የቦይንግ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የደረሱት አደጋዎች እጅግ አሳዝነውናል” ያሉ ሲሆን፤ ኃላፊውም “ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ እንጠይቃለን። በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ በደረሱት አደጋዎች ክቡር የሆነው የሰዎች ሕይወት በመጥፋቱም ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኃላፊውም አክለው በአደጋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦችን ይቅርታ በመጠየቅ፤ የተፈጠረው ነገር እንደ ድርጅቱ መሪነቴ በቀጥታ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል” ሲሉም ተደምጠዋል።
የቦይንግ ኃላፊ በሁለቱ የአውሮፕላን አደጋዎች ሕይወታቸውን ካጡ ግለሰቦች ቤተሰቦች በተጨማሪ በአውሮፕላን የሚጓጓዙ ሰዎችን በአጠቃላይ ይቅርታ ጠይቀዋል። እርሳቸውም “እምነት ያጡ ተጓጓዦችን ይቅርታ እንጠይቃለን። ደንበኞቻችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደራችን ይጸጽተናል” ብለዋል።
የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ ከተከሰከሱ በኋላ ኃላፊው ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ የሲቢኤስ ኒውስ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም “ቦይንግ ውስጥ ባሳለፍኩት 34 ዓመታት ከተፈጠሩ ነገሮች እጅግ ከባዱ ይህ ነው። የተፈጠረውን መቀየር ባንችልም በቀጣይ ለደህንነት ጉዳዮች የላቀ ትኩረት እንሰጣለን” ብለዋል።
እንዲሁም ቦይንግ ስለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ከመውሰድ ባሻገር በአውሮፕላኑ ላይ አስፈላጊውን ማሻሻያ እንደሚደርግ ኃላፊው ጠቁመው፤ የቦይንግ ስሪት አውሮፕላኖች ለወደፊቱ ደህንነታቸው አስተማማኝ እንደሚሆን ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ባለፈው መጋቢት ወር ከተከሰከሰ ከሳምንታት በኋላ ኃላፊው በቦይንግ ስም ይቅርታ ቢጠይቁም፤ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ የካፒቴን ያሬድ ጌታቸው አባት ዶክተር ጌታቸው ተሰማ የቦይንግ ይቅርታ “ዘግይቷል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ በደረሰበት አደጋ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። እንዲሁም ይህ አደጋ ከመከሰቱ ከአምስት ወር በፊት ንብረትነቱ የኢንዶኔዥያ የሆነ የቦይንግ ስሪት ላየን ኤር አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉም ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
ሶሎሞን በየነ