ሀገር ወዳዱ ቃለአብ

እንዴት ናችሁ ልጆችዬ? ሁሉ ሠላም ነው? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? መቼም በትምህርት፣ በጥናት፣ ወላጆቻችሁን በማገዝ፣ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ እንዳሳለፋችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ፣ ከትምህርታችሁ ጎን ለጎን ማድረግ የሚያስደስታችሁ ነገር ምንድ ነው? የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት፣ ሥዕል መሳል፣ ሙዚቃ እና የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወት እና ሌሎችንም እንደምትዘረዝሩልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ፣ ዛሬ አንድ ጎበዝ ታዳጊ ገጣሚ ልናስተዋውቃችሁ ነው። በትምህርቱም ደግሞ ጎበዝ ነው። “ማነው?” አላችሁ አይደል? እንግዲያውስ እናስተዋውቃችሁ

ቃለአብ ሸዋፈራው ይባላል። የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የልጅ ልጅ ነው። በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው። ልጆችዬ፣ ቃለአብ በትምህርቱ ጎበዝ ሲሆን፤ ከአንድ እስከ አምስተኛ የሚወጣ የደረጃ ተማሪ ነው። ከትምህርቱ ጎን ለጎን የተለያዩ ግጥሞችን ይጽፋል። መፃፍ ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመጋበዝ ግጥሞቹን ያቀርባል። ለምን አንድ ግጥሙን አናስነብባችሁም? የግጥሙ ርዕስ ‹‹አንቺ›› ይሰኛል።

አንቺ

የሰው ዘር መገኛ፣ የአዳም ፍጥረት ቤቱ

ለበኩር ለቃኤል የእድገት መሠረቱ

ለታናሽ ለአቤል ለመኖር ምክንያቱ

አንቺ የሥልጣኔ ምንጭ ታሪክ የማበርከት

በነዛግዌ መንደር በአክሱም ነገሥታት

የጀብድ ሁሉ አዋጅ የታሪክ መሠረት

በዮሐንስ ዘመን በምኒልክ መንግሥት

አንቺ፣ አንቺ ማለት እኮ፣ የድህነት መስኮት

አንቺ ማለት እኮ የሰው ልጆች አጥንት

አንቺ፣ አንቺ፣ አንቺ፣ አንቺ ማለት እኮ

ለድንበርሽ ክብር ደም የተራጩልሽ

የጀግናን ማንነት ባንቺ ያሳዩብሽ

ለአምላክ ሊነግሩልሽ

ዝቅ ብለው ወደታች መሬት የሳሙልሽ

አንቺ ማለት እኮ የዓለም ንግሥት ነሽ

ታዲያ፣ ታዲያ ለዚህ ክብርሽ

ለአንቺ የሚመጥን ስያሜ ባጣልሽ

በሙሉ አንደበቴ ኢትዮጵያ ልበልሽ።

ልጆችዬ፣ አነበባችሁት? ቃለአብ ጎበዝ ገጣሚ ነው አይደል? ሀገሩንም በጥሩ ግጥም እንደገለፃት ተረድታችኋል ብዬ አምናለሁ። ቃለአብ ለወደፊት የምህንድስና ባለሙያ (አርክቴክት) የመሆን ፍላጎት አለው። እንዲሁም፣ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ትልቅ አሻራ የማሳረፍ ዓላማም አለው። ዓላማውን እንዲያሳካ እና ግጥሞቹን እንዲፅፍ አንጋፋው አርቲስት ጋሽ ደበበ እሸቱ ያበረታቱታል። እርሱም አያቱ ስለሚያበረታቱት ደስ ይለዋል። ሌሎች ግጥሞችን በማንበብ ልምድ መውሰዱንም ይናገራል። እናቱ ወይዘሮ ዮዲት ደበበም ርዕሶችን በማስተካከል፣ ምክር እና ሃሳብ በመስጠት እገዛ ታደርግለታለች፤ ታበረታታዋለችም።

የ14 ዓመቱ ታዳጊ ቃልአብ ግጥም መፃፍ የጀመረው ፈልጎ ወይም አቅዶ አይደለም። እንደ ድንገት ወይም እሱ እንደሚለው እንደ ዕድል መፃፍ የጀመረ ሲሆን፤ ልጆች ዝንባሌያቸውን እና ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ ወላጆች ማገዝ እንዳለባቸው ይገልፃል። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ መሞከር እና እስከ መጨረሻው ድረስ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው፤ እንዲሁም፣ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ይመክራል።

ልጆችዬ፣ በትምህርት ቤታችሁ ብዙ ክበባት እንዳሉ ይታወቃል። ታዲያ እናንተ በየትኛዎቹ ክበባት ትሳተፋላችሁ? የቃለአብ እንንገራችሁ። እሱ በብዙ ክበባት ውስጥ ይሳተፋል። በተለይም በሚኒሚዲያ ክበብ በመሳተፍ ግጥሞቹን ያቀርባል። እናም ልጆችዬ፣ ግጥሞቹን በሚኒሚዲያ ላይ በማቅረቡ ዛሬ ላይ ትልልቅ መድረኮች ላይ ተገኝቶ ግጥሞቹን እንዲያቀርብ ብቻ ሳይሆን በራስ የመተማመን አቅሙንም ጨምሮለታል።

በልጆች ዓይን ሁሉም ነገር ጥሩ፣ መልካም እና ንጽህ እንደሆነ ነው ቃለአብ የሚናገረው። ስለዚህም ይህንን በመረዳ ወላጆች ልጆቻቸውን ኮትኩተው ቢያሳድጉ፣ ድጋፍ ቢያደርጉላቸው እና ራሳቸው (ልጆቻቸው) በሚፈልጉበት መንገድ እንዲሄዱ ቢያግዟቸው የነገ ሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆን ያግዛል። ከድሮ ነገሥታቶች አፄ ምኒልክ፣ አፄ ኃይለሥላሴ፣ አፄ ዮሐንስ እና አፄ ቴዎድሮስን አብዝቶ ይወዳቸዋል። የመውደዱ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ለደረሰችበት ዕድገት የእነርሱ ትልቅ ዐሻራ ማሳረፍ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ልጆች ከቃለአብ ዕድሜ ከፍ ያሉትም ይሁኑ ታናናሾቹ አብዛኞቹ ልጆች ስልክ፣ ታብሌት እና መሰል ነገሮችን አብዝተው ይጠቀማሉ። እርሱ ግን ለአስፈላጊ ነገር ብቻ ነው የሚጠቀመው። የእሱ እናት እና አባት መልካም ወላጆች ናቸውና አልባሌ ነገር ላይ ጊዜውን እንዲያጠፋ አያደርጉትም።

ብዙ ልጆች ስልክ እና የመሳሰሉትን ከመጠቀም ባለፈ ሱሰኛ እንደሆኑ ታዝቧል። ለዚህ ደግሞ የወላጆች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም ይላል። ለእዚህ ልጆች ቃለአብ የሚመክራቸው ነገር አለ። ወላጆች ልጆቻቸውን በጥሩ ይሁን በመጥፎ መንገድ የመቅረጽ አቅም አላቸውና ቤተሰብ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በተጨማሪም፣ ተማሪዎች ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ መሆን አለበትም ይላል።

ታዳጊው ቃለአብ ዛሬ በተለያዩ መድረኮች ላይ ተጋብዞ ግጥም እንዲያቀርብ ላገዙት እና ላበረታቱት ለአያቱ ለአርቲስት ጋሽ ደበበ እሸቱ፣ ለእናቱ፣ ለአባቱ እና ለጓደኞቹ፤ እንዲሁም፣ ድጋፍ ለሚያርጉለት ሁሉ ምስጋውን አቅርቧል። ልጆችዬ፣ ከታዳጊው ልጅ ብዙ ነገር እንደተማራችሁ እተማመናለሁ። በሉ ልጆችዬ፣ ሳምንት በድጋሚ ለመገናኘት ያብቃን።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You