የትናንቱን አዲስ ዘመን አስገራሚና ታሪካዊ ዘገባዎች በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ መለስ ብለን እንመለከተዋለን። አንድ የቆየ የጋዜጣው ዘገባ ሌባይቱን ሌባ ሰረቃት ይለናል፤ የሀገር ባህል አልባሳት እያሉ አጭር ቀሚስ ለምኔ ሲል የሐረር ከተማ ፖሊስ አጫጭር ቀሚስ የሚለብሱትን ወይዛዝርት ከጣቢያው ያቀረበበትን አጋጣሚም የሚያስታውሰን ዘገባ ይዘናል፡፡ በተጨማሪም ዘመዶቼን አላስጠቀምክም በሚል ሰበብ በክራንች አራት ጥርስ ያረገፈው ጥጋበኛ ግለሰብ ለአንድ ጥርስ 2 ዓመት ተሰልቶ በስምንት ዓመት እንዲቀጣ ተበይኖበታል። የመንገደኛውን የትዝብት ደብዳቤንም በማከል ለዛሬው ቀንጭበን እናስታውስ፡፡
ሌባይቱን ሌባ ሰረቃት
(ኢ.ዜ.አ.)፡- በግርድና ተቀጥራ ከምትሠራበት ቤት ፪ ሺህ ብር ሰርቃ ስትኮበልል፤ የሰረቀችውን ገንዘብ በሌላ ሌባ የተሰረቀችው ዘውዲቱ ሞላ ፤ በ፮ ወር እስራት እንድትቀጣ አሰላ ከተማ ያስቻለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ፈረደ፡፡
ተከሳሽ ለእስራት ያበቃት ይህንኑ ገንዘብ የተሰረቀችው በአሰላ ከተማ በግርድና ተቀጥራ ትሠራበት ከነበረው አቶ ግርማ ድፋባቸው ቤት ፤ ባለፈው መጋቢት 5 ቀን 66 ዓ/ም / ሲሆን ፤ እሷ ገንዘቡን ይዛ ወደ ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ግዛት ከኮበለለች በኋላ ፤ ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ስትዘዋወር በጋሻው አጥላው በተባለው ልማደኛ ሌባ መሰረቋ ታውቋል፡፡
ከዚያም ዘውዲቱ ሞላ ሀብቷ በልማደኛ ሌባ መሰረቁን ለክፍሉ ፖሊስ አመልክታ፤ በተደረገው መከታተል በጋሻው አጥላው ተይዞ ምርመራው ከተጣራ በኋላ፤ ደብረ ብርሃን አስቻለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት በመቅረብ ጥፋቱ በማስረጃና በሕግ ምስክሮች በመረጋገጡ፤ አንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ሲፈረድበት፤ የተሰረቀውም ገንዘብ ለባለቤቷ እንዲመለስ ታዘዘ። በዚህም መሠረት ዘውዲቱ ሞላ በፍርዱ መሠረት ገንዘቡን ለመረከብ ስትሰናዳ ዋናው ባለ ገንዘብ አቶ ግርማ ድፋባቸው በክትትል ደርሰውባት ኖሮ ፤ አስቀድሞ ገንዘብ ከሳቸው የተሰረቀ መሆኑን ማስረጃ አቅርበው ዘውዲቱ ከነገንዘቡ እጅ ከፍንጅ ተያዘች፡፡
ከዚያም ተከሳሿ ወደ አሰላ ከተማ ተልካ ወንጀሉን በፈጸመችበት ክፍል ክስ እንዲቀርብባት ተደርጎ፤ አድራጎቷ በማስረጃና በሕግ ምስክሮች በመረጋገጡ በ፮ ወር እስራት እንድትቀጣ የተፈረደባት መሆኑን አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡ በሁለቱ ሌቦች መቀባበል ከተሰረቀው ከዚሁም 2 ሺህ ብር ውስጥ 725 ብር ከ25 ሳንቲም ሲባክን በመጨረሻ የተገኘው ተራፊ ገንዘብ 1 ሺህ 338 ብር ከ75 ሳንቲምና በተሰረቀው ገንዘብ ተገዝተው በኤግዚቢትነት የቀረቡት ልብሶችና ዕቃዎች ለባለገንዘቡ ለአቶ ግርማ ድፋባቸው እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ በዚሁ ጊዜ አብሮ ማዘዙን ቃል አቀባዩ ጨምሮ ገልጧል፡፡
(አዲስ ዘመን መጋቢት 27
ቀን 1966 ዓ.ም )
የአጭር ቀሚስ ቁጥጥር በሐረር
ሐረር፤(ኢ-ዜ-አ-) በሐረር ከተማ ውስጥ አጫጭር ቀሚስ እየለበሱ በሚዘዋወሩት ሴቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሐረር አውራጃ ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ ገለጡ፡፡
በተደረገው ቁጥጥር መሠረት በሐረር ከተማ ውስጥ የሀገርን ባህል የሚያጎድፍ ልብስ ለብሰው የተገኙት 67 ልጃገረዶችና ሴቶች 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየቀረቡ ዳግመኛ ላለመልበስ መፈረማቸውን ሌተናል ኮሎኔል ኃይለ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡ ይኸው አፈጻጸም ለወደፊቱ በየጣቢያው ተላልፎ በሚገባ በሥራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
በዚሁ ይዞታ በከተማው ውስጥ ይታይ ነበረው የአጭር ቀሚስ ለባሾች ቁጥር መቀነሱንና ለወደፊት ጨርሶ እንደሚጠፋ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ እምነታቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 1962ዓ.ም)
ጥርስ ያወለቀ ተከሳሽ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደበት
በሰሜን ጎንደር በበየዳ ወረዳ በርዳታ እህል ክፍፍል በተነሳ ችግር ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ የከሳሹን ጥርስ በማውለቁ በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የወረዳው ማስታወቂያ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
……
ፍርድ ቤቱ በሬ ፈረደ በተባለው ላይ ቅጣቱን የወሰነው ዘመዶቼን ለምን ለርዳታ አልመዘገብክልኝም ብሎ ጥያቄ ያቀረበለትን ጥፍጡ መንግሥቱ የተባለውን ግለሰብ በሚጠቀምበት የእግር ክራንች በመምታት አራት የፊት ጥርሱን በማውለቁ ነው፡፡
(አዲስ ዘመን ታኅሳሳ 14 ቀን 1978ዓ.ም)
በሕጉ ነው ወይንስ በራሱ ፍላጎት?
ነሐሴ 28 ቀን 1979ዓ.ም ከሻሸመኔ ወደ ድሬዳዋ ለሚጓዘው የጎን ቁጥር 215 የሆነ የአውቶብስ ቲኪት ቆራጭ የነበሩትን ደመቁ የተባሉት ግለሰብ፤ ለ12 ዓመት ልጅ ቲኬት ለመቁረጥ በሕጉ መሠረት ሰልፍ ይዤ ተራዬ ሲደርስ ግማሽ ዋጋ ይቁረጡልኝ አልኳቸው። እሳቸውም አይቻልም ግማሽ ዋጋ የለም ይሉኛል፡፡ እሺ ይሁን በሙሉ ዋጋ ስጡኝ እላቸዋለሁ መልሰው የለም ውጣ ብለው ያፈጡብኛል፡፡ እኔም ሁኔታው ስላስፈራኝ ወደሚከተለው ክፍል በመሔድ በዝርዝር አስረዳሁ፡፡ የኔን አቤቱታ የተመለከቱትም ወደ ቦታው በመሔድ ለምን እንዲህ ሠራህ ብለው ከጠየቁ በኋላ ቲኬቱ ይቆረጥላቸው ብለው አዘዙ፡፡ ግለሰቡም መልሰው አይቻልም እስቲ የሚመጣውን አያለሁ፤ ቲኬቱም አልቋል ይሏቸዋል፡፡ አቤቱታ ሰሚውም ጥለውኝ ወደ ቢሯቸው ይመለሳሉ። ተስፋ ሳልቆርጥ አሁንም ወደዚያው ድረስ በመሔድ ሰውየው የሚሠሩት በፍላጎታቸው ወይስ በሕግ ነው ብዬ ከጠየቅሁ በኋላ ቲኬቱን ሸጬ ጨርሻለሁ ማለቱስ ተገቢ ነው? ግማሽ ዋጋስ እስከስንት ዓመት ልጅ ነው የሚቆረጠው ብዬ ጥያቄዬን አቀረብኩ። በዚህን ጊዜ ወደ ቦታው በመሔድ በሕግ ሳይሆን በልመና በሙሉ ሂሳብ ቲኬት እንዲቆርጥልኝ አድርገው ሕጻኑን ልልከው ችያለሁ። ሥነ ሥርዓት የጎደላቸውና በሕዝብ የሚያሾፉ እነዚህን መሰል ሠራተኞች ሊታረሙ ይገባል፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ ኮርፖሬሽንስ ለምንድነው ጅራታቸውን እየያዘ ልክ የማያስገባልን?
(አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4 ቀን 1979ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም