በትግራይ ክልል 32 ወረዳዎች ድርቅና የምግብ እጥረት አጋጥሟል

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል 32 ወረዳዎች ላይ የከፋ ድርቅና የምግብ እጥረት ማጋጠሙን የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ አስተባባሪ አቶ ልጅዓለም ካሕሣይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ 32 ወረዳዎች የከፋ ድርቅ እና የምግብ እጥረት አጋጥሟል፡፡

በትግራይ ክልል ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች የከፋ የድርቅ አደጋ ያጋጠማቸው መሆኑን አቶ ልጅዓለም ተናግረዋል፡፡

አጠቃላይ ክልሉ በጦርነቱ ምክንያት፤ በዝናብ እጥረት በግብርናውም ቢሆን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የድርቅ አደጋ በማጋጠሙ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ እርዳታ ፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት፤ በክልሉ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በዋነኝነት በጦርነቱ እና ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ የድርቅ አደጋ በመከሰቱ ያጋጠመ ነው፡፡

ያጋጠመው የምግብ እጥረት አደጋ ለአንድ ዓመት ያህል በትኩረት ርዳታ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፤ መንግሥት በቅርቡ ርዳታ እንደሚልክ ቃል በገባው መሠረት በፍጥነት ወደ ተረጂው እንዲዳረስ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ክልሉ ላይ ያለውን ሀብት በማጥናት ቀጣይነት ያለው የልማት ሥራዎችና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች በማጠናከር ውጤታማ ወደ ሆነ ሥራ መግባት የግድ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አታለለ አቡሐይ እንዳሉት፤ በመጪዎቹ ሦስት ቀናት ለሦስተኛ ዙር የሚሰራጭ ርዳታ እንዳለ አመላክተዋል፡፡

ርዳታው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በድርቅና በግጭት ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ይከፋፈላል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሁለት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅና በግጭት ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ያነሱት አቶ አታለለ፤ ክልሉ ያጋጠመው አደጋ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ባሳወቀው መሠረት ርዳታው ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ ዋግኽምራ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ሰሜን ሸዋ አካባቢ፣ በምሥራቅ ጎጃም እንዲሁም በአፋር ክልል ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች የምግብ እጥረት ማጋጠሙን አንስተው፤ አስፈላጊው ርዳታ ለነዚህ አካባቢዎችም እንደሚሰራጭ ጠቅሰዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You