አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያካሂደው በምርምርና ስርፀት የሚታተሙ ጥናቶች ከእጥፍ በላይ እየጨመሩ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ። በኢትዮጵያ ለምርምርና ስርጸት የሚመደበው በጀት ከዓለም ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ስምንተኛው የምርምርና ስርፀት ዐውደ ሳምንት ትናንት በዋናው ግቢ ማንዴላ አዳራሽ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት፤ የምርምር ሳምንቱ እንደ ፕሮጀክት ሲጀመር ዩኒቨርሲቲው፣ መንግሥትና በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እያደረጉለት ሲሆን፣ የምርምርና ስርፀት ዐውደ ሳምንት ከተጀመረ እኤአ 2012 ወዲህ በምርምር ላይ ያተኮሩ የህትመት ውጤቶች ከእጥፍ በላይ እየጨመሩ ይገኛል። ሲጀመር 250 የነበረው ህትመት ከስምንት ዓመታት ወዲህ ሁለት ሺ መድረስ ችሏል።
‹‹በአሁኑ ወቅት 49 ሺ ተማሪዎች አሉን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና ለአገራችን ልማትና ዕውቀት ግንባታ የሚበጁ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ምሁራንን መገንባት የሆነው ሚናችንን የበለጠ ለማሻሻል እንሠራለን።›› ሲሉ አስታውቀዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ገለፃ፤ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ምርምሮችን መፃፍና መደርደሪያ ላይ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ ህትመት ዘገባዎች መቀየር ለጉባዔዎች ማቅረብና ማወያየት እንዲሁም በጆር ናሎች እንዲታተሙ ለማድረግ የበለጠ መሥራት ግድ ይላል።
የሰላም ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ በሁሉም መስኮች የሚካሄድ ምርምር በአገሪቱ የሚደርሰውን ሁለንተናዊ ተግዳሮትን ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የምርምር አድማሱ ግን በሥራ ፈጠራና የምጣኔ ሀብት ዘርፉን በማሻሻል ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሥራት በህዝቡ ፍላጎት ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
አክለውም ‹‹በጠባብ ጂኦፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ሳንታጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሰብን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አስፈላጊ ነው።›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በምርምር የተመሠረተና የተጠና ፖሊሲ ማካሄድ ቀጣይነት ላለው ሰላምና ልማት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሙፍሪያት፣ ለአገሪቱ ሰላምና ልማት እንቅፋት በሆኑ አንገብጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ የሰላም ሚኒስቴር ጥልቅ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚታዩ የምርምር ክፍተቶችን ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስና ምርምር በዳይሬክተር ደረጃ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘርፉ የምርምር ፖሊሲ ስርፀት፣ የምርምር ስነ ምግባር፣ የህትመት ግምገማ እና ዕውቅና በተጨማሪም በምርምር ፈንድ ዙሪያ በኃላፊነት እንደሚሠሩ አስረድተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከዓመታዊ ምርቷ አንጻር ለምርምርና ስርፀት የሚመደበው ገንዘብ በዓለም ዝቅተኛ ከሆኑት አገራት ተርታ እንደምትመደብ የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚጠቁም ገልፀዋል።
‹‹ዩኒቨርሲቲዎቻችን የውጪ አገራት ተማሪዎችን በማስተማር የውጪ ምንዛሪ ወደአገራችን እንዲገባ በማድረግ፣ በሀብት ውስጥ ስለሚመነጨው ኢኮኖሚ፣ ስለፈጠሩት የሥራ ዕድል፣ ስላስመዘገቡት የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ፣ ተቀባይነትና ዕውቅና ያገኘ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ብዛት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮች ወደ ኢንዱስትሪ ምርምርና ስርፀት ስንቱ ተሸጋገሩ የሚሉትን ወሳኝ ጉዳዮች እየለካን ከሄድን ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ለማላቅና አገሪቱንም ለማሳደግ ይረዳል።›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ