አዲስ አበባ:- በኢጋድ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል በአካባቢው ከአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስራዎችን እየሠራ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ጉሌድ አርታን አስታወቁ።
52ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተናና ትንበያ ፎረም ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል በተጀመረበት ወቅት የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ጉሌድ አርታን እንደገለፁት፤ፎረሙ የሚቀጥሉትን የአራት ወራት የአየር ለውጥ መተንበይ፣ መተንተንና ወደ ተግባር መለወጥ ላይ ያተኮረ ውይይት ይደረግበታል።
ተመሳሳይ የአየር ንብረት ላላቸው የምስራቅ አፍሪካ አገራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በግብርናው ዘርፍ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማሳካት አኳያ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ተረድተው እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
እ.አ.አ በ2011 በምስራቅ አፍሪካ አገራት የተቋቋመው ይህ ማዕከል ከአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስራዎችን ሲሠራ መቆየቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ፎረምም፤ በተለይ እጅግ ወሳኝ በሆኑት ግብርና፣ ውሀ፣ ጤና እና ማዕድን፤ እንዲሁም በእነዚህና ሌሎች ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን በተመለከተ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ጠቃሚ መረጃ መለዋ ወጥ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ጀነራል ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው እንዳ ሉት፤ የውይይት መድረኩ በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎች፣ የሚያስከትሏቸው ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን በተመለከተ ከፍተኛ የእውቀት ሽግግር የሚደ ረግበት ይሆናል። የአየር ንብረት አገልግሎት፣ ለውጥ፣ ትንበያ እና በመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ ይካሄድበታል።
የውሀ፣ መስኖ እና ማዕድን ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ በመከሰቱ ምክንያት በደቡባዊው የአገራችን ክፍል የተለያዩ ችግሮች መከሰታቸውን ጠቅሰው፣ከእነዚህም አንዱ የውሀ ግድቦች አቅም መቀነስ በዚህም የተነሳ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ማስከተሉን አብራርተዋል።
የአገራት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፤ እንዲሁም ከ100 በላይ የዘርፉ ሳይንቲስቶች የተገኙበት ፎረም ውጤታማ በሆነ መልኩ እንደሚጠናቀቅና በርካታ የመፍትሄ ሀሳቦችም እንደሚፈልቁ ይጠበቃል ብለዋል።
ፎረሙ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል (ICPAC) ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011
ግርማ መንግሥቴ