የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያካሄደው ጥናት ለግሉ ዘርፍ ነጋዴዎች በቂ የመሬት አቅርቦት እንደሌለ ማሳየቱ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ ለንግድ ስራ የመሬት አቅርቦት የፖሊሲ መመሪያዎችና አሰራሮች ማነቆዎችን አስመልክቶ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው በሀገሪቱ ለግሉ ዘርፍ ነጋዴዎች ያለው የመሬት አቅርቦት በቂ አይደለም፤ይህ መሆኑም የግሉ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ዝቅተኛ አድርጎታል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ አዘዘው ጥናቱ ትናንት በቀረበበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ግልፅና ፍትሀዊ የመሬት ፖሊሲ መኖር የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስፋት አስተማማኝ የንግድ ተወዳዳሪነት እንዲኖር ያስችላል። ይህም የግሉ ዘርፍ በትልልቅ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚኖረውን ተሳትፎ በማሳደግና ሰላማዊ የውድድር ምህዳር በመፍጠር የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገት ለመፍጠር ያግዛል።
እንደ ጥናቱ አቅራቢ ገለጻ፤በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ይህንን የሚፈቅድ አይደለም። በተጨማሪም የከተሞችን እድገትና መስፋፋት ተከትሎ የግሉ ዘርፍ ቁጥር መጨመሩ ስለማይቀር የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ከግምት ያስገባ የመሬት ስርዓት ሊኖር ይገባል።በመሆኑም ከህገ መንግሥቱ ጀምሮ የሊዝ አዋጅና ከዚህ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን እስከ ዛሬ የወጡ መመሪያዎች በሙሉ እርስ በእርሳቸው የሚናበቡና ሊተገበሩ የሚችሉ እርስ በእርስ የሚቃረኑ እንዳይሆኑ ማስተካካል ይገባል።
የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአነስተኛ ቦታ በቂ መሰረተ ልማት በማቅረብ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፣ እነዚህን ተሞክሮዎች ወደ ሀገርኛ መተግበር፤ ከገጠር ወደ ከተማ እየተካለሉ ያሉ ቦታዎችን ተከትለው የተፈጠሩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ከመሬት ስሪቱ ጋር አስተሳስሮ መፈተሽ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ጥናቱን ባካሄደው ኢኩማ አማካሪ ደርጅት የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኢያሱ ኩመራ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የሊዝ አዋጁ ዋነኛ ዓለማ እያደገ የመጣውን የመሬት ፍላጎት መመለስና ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚመጡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መቅረፍ ነው። በጥናቱ የተገኘው ውጤት የሚያመለክተው ግን በመሬት አቅርቦት በኩል የተወሰነ ውጤት ቢኖርም መልካም አስተዳደርን በተመለከተ ተገቢው ውጤት እንዳልተገኘ ነው።
በአሁኑ ወቅት መሬት የሚተላለፍባቸው ሁለቱ መንገዶች ለነጋዴው ማህበረሰብ ምቹ አይደሉም ያሉት አቶ ኢያሱ.፣ በአንድ ወገን መሬት በምደባ የሚተላለፈው ለትምህርት ቤት፤ ለኤምባሲ፤ ለመንግሥት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች፤ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶችና ለማኑፋክቸሪንግ በመሆኑ ነጋዴው ሊያገኝ አይችልም ይላሉ። ‹‹በጨረታም ሲሆን በሀገሪቱ አንድ ነጥብ አራት ሚሊየን የሚጠጉ ነጋዴዎች ቢኖሩም ሰማኒያ በመቶ የሚደርሱት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር በታች ካፒታል ያላቸው በመሆናቸውና ጨረታው በገበያ ዋጋ የሚወሰን በመሆኑ ከአቅም ጋር በተያያዘ ለመገለል ይዳረጋሉ።››ሲሉ ያመለክታሉ።
በሊዝ አዋጁ የተቀመጡ በርካታ አንቀፆች ግልፅነት የሚጎድላቸው መሆናቸው፤ የገጠርና የከተማ መሬት ድንበር እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን የተለየ አለመሆን፤ የመሬት አስተዳደር አሠራሮች ጠንካራ ባለመሆናቸው መሰረተ ልማቱ የተሟላ በቂ መሬት ስለማይቀርብ እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራር አለመስፈን፤ ስልጣንን አላግባብ መጠቀምና በአንዳንድ ከተሞች ከሊዝ የሚገኘውን ገቢ ለበጀት ማሟያ ለማድረግ መስራት ዋናዋና ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል። በመሆኑም በየከተማው ጠንካራ ተቋም በማቋቋም የሊዝ አዋጁን መፈተሽና ቁርጠኛ የፖለቲካ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ የጥናቱ ውጤት ማመላከቱን ተናግረዋል።
ጥናቱ በሲውዲን ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ (ሲዳ) ድጋፍ ከሰባት መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በተመረጡ 17 ከተሞች ላይ የተከናወነ ሲሆን ሲጠናቀቅም አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግ ለሚመለከታቸው አካላት የሚቀርብ መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ