አዲስ አበባ:- በአገራችን ሁከትን ለማባባስና የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልል አመራሮች ገለፁ። ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አመራሮች እንደገለፁት በማህበራዊ ሚዲያው፣ በተለይም በፌስቡክ እየተሰራጩ የሚገኙ መረጃዎች መሰረተ-ቢስ ከመሆናቸውም በላይ አላማቸው በህብረተሰቡ መካከል ሁከት መፍጠርና በአገሪቱ ሰላም የሌለ በማስመሰል ገፅታዋን ማበላሸት ላይ ያተኮረ ነው።
በአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በልስቲ በለጠ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት ሰሞኑን እምቦጭን ለማጥፋት ጥንዚዛ ከዩጋንዳ በመምጣቱ ምክንያት ጥንዚዛዎቹ በአካባቢው ሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ተደርጎ ሲናፈስ የነበረው ወሬ ተራ አሉባልታ መሆኑንም ተናረዋል።
“ጥንዚዛዎቹ ከዩጋንዳ ነው የመጡት” የሚለው የማህበራዊ ሚዲያ ወሬ መሰረተ-ቢስና የመንግስትንና የህብረተሰቡን መልካም ስራ ለማጣጣል ሆን ተብሎ የተከፈተ ዘመቻ እንጂ ምንም አይነት እውነትነት የለውም ብለዋል ምክትል ዳይሬክተሩ።
ጥንዚዛዎቹ እንቦጭን በመመገብ ህብረተሰቡ አረሙን ለማጥፋት የሚያደርገውን ርብርብ እንዲያግዙ ከሶስት ዓመት በፊት ከዚሁ ከወንጂ ፋብሪካ ያመጣናቸው ናቸው የሚሉት አቶ በልስቲ ፋብሪካው የተጠቀምባቸውና ውጤት ያገኘባቸው፤ ወደ ባህር ዳር ከመጡም ወዲህ ውጤት እያሳዩ ያሉ ናቸው ብለዋል። አሁን ላለበት 61 በመቶ የማስወገድ አፈፃፀምም የጢንዚዛዎቹ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ጥንዚዛዎቹ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት አስፈላጊው ጥናት እየተደረገባቸውና መጠለያ ተሰርቶላቸው ነው ያሉት የሚሉት ዳይሬክተሩ ከወንጂ እንደመጡም አስፈላጊው ምርምር ሳይደረግ ወደ ስፍራው እንዳልተለቀቁም ተናግረዋል።
ሆኖም ሆን ብለው የተሳሳተ ወሬ በመንዛት ህዝብን ለማሳሳት የሚፈልጉ ሃይሎች አላማቸው ይታወቃል የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በመንግስት በኩል የሚሰሩ ስራዎችን ማጣጣልና ምንም እየተሰራ እንዳልሆነ በመግለፅ መንግስትና ህዝብን ለማጋጨት እየሰሩ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን በሚገባ ተረድቶ ምን ግዜም የሚያገኛቸውን መረጃዎች ከየት፣ በማን፣ እና በምን እንደተለቀቁ በመመርመር እውነተኛ ምንጫቸውን በማገናዘብ መቀበል እንዳለበት አሳስበዋል።
የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በበኩላቸው ሰሞኑን የሀዋሳ ከተማን ሰላምና ፀጥታ አስመልክተው በከተማዋ ለተገኙ እንግዶች እንደተናገሩት በማህበራዊ ሚዲያው “በከተማ ውስጥ በተከሰተ የብሄር ግጭት ምክንያት ከተማዋ ታምሳለች” በሚል የፌስቡክ ዘመቻ ተከፍቶ ህብረተሰቡን ለማሳሳት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ነገር ግን በሃዋሳም ሆነ በአጠቃላይ በክልሉ የተከሰተ ሁከትም ሆነ ችግር አለመኖሩንና እንዲህ አይነት ወሬዎች ዓላማቸው ህዝብን ማተራመስ በመሆኑ በእንዲህ አይነት ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ህብረተሰቡም ቢሆን እንዲህ አይነት የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩና በህዝብ ውስጥ ሽብር የሚነዙ የማህበራዊ ሚዲያዎችን በጥንቃቄ ማየትና ሰላሙን ለማስጠበቅ ዘብ መቆም እዳለበት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ግርማ መንግሥቴ