የማዕድን ሀብትን ለማልማት ወሳኝ ከሆኑት መካከል የዘርፉ ኢንቨስትመንት ይጠቀሳል። የማዕድን ዘርፉን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከሚያስችሉ ሥራዎች መካከል ደግሞ ኤክስፖ አንዱ እንደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያም ይህንን የማዕድን ሀብትንና የማዕድን ዘርፉን ለማልማት የተዘጋጁ ምቹ ሁኔታዎችን የሚያስተዋውቀውን፣ የማዕድን ዘርፉን ተዋንያን በአንድ የሚያገናኘውን፣ የዘርፉን የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚያስችለውን ኤክስፖ በማዘጋጀት ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች ትገኛለች።
ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ማካሄዷ ይታወሳል። ዘንድሮም ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሁለተኛውን ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዳለች። የዘንድሮው ኤክስፖ ከአምናው በብዙ መልኩ የተለየ ነው። ባለፈው ዓመት ለሶስት ቀናት ብቻ የተካሄደ ሲሆን ዘንድሮ ለአምስት ቀናት ነው የተካሄደው። ዘንድሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂደዋል።
ኤክስፖው ለሀገሪቱ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ትልቅ አቅም መፍጠሩ ተጠቁሟል። የሀገሪቱን የማዕድን ሀብት ዜጎች በጋራ ተቀናጅተው አክሲዮን እየመሰረቱ ጭምር እንዲያለሙም ጥሪ ቀርቦበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኤክስፖው በተከፈተበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች ሀገር ናት፤ ይህን የማዕድን ሀብት በሚፈለገው ደረጃ አልምቶ በመጠቀም ለተተኪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይቻላል።
‹‹በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች አስደናቂ የማዕድን ሀብቶች አሉ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹ይህን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ማወቅና መጠቀም ከቻልን ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ መሠረት እንጥላለን። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፍን አድርጎታል።›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት የማዕድን ሀብት አለን የለንም የሚለውን ለማወቅና ለመረዳት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። አሁን ደግሞ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች አውቀን ባንጨርስም ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ሀብት የታደለች ሀገር መሆኗን መረዳት ችለናል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የማዕድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን በማዳንና የተለያዩ ማዕድናትን ወደ ውጭ በመላክ በርካታ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ለኢኮኖሚያዊ እድገት አይተኪ ሚና መጫወት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በማዕድን ሀብቱ ይህን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዩችና የበርካታ ውድ ማዕድናት መገኛ እንደሆነች ኤክስፖውም ማመላከቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ምን እንዳለና ምን እየተሰራ እንደሆነ በመረዳት ኢኮኖሚውን ሊደግፉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ክምችት የሚያሳይ፣ የማዕድን ሀብትን ወደ ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ለሚቀጥለው የብልጽግና ጉዞ መሠረት የሚጥል ዘርፍ መሆኑን መረዳት የሚቻልበት ነው። የማዕድን አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ተጠቃሚዎች፣ የቴክኖሎጂ አምራችና አቅራቢዎች ተገናኝተው ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት እና ትስስር የሚፈጥሩበት ነው።
ስለዚህም የምናስበው የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በግል ማምረትና ኢንቨስት ማድረጉን አቁሞ በጋራ መሥራት የምንችልበትን፣ እውቀት የምናሰባስብበትንና የምንበለጽግበትን መንገድ መፍጠር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከችግር ነጻ የሆነ የመልሚያ መንገድ እንደሌለም ጠቅሰው፣ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ወደ ብልጽግና ከፍታ መገስገስ እና ለተተኪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ይህ ኤክስፖ በርካታ እድሎችን ለሀገሪቱ ዜጎች የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙት የማዕድን ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያስችላል። በተጨማሪም መንግሥት ባለሀብቶች ከባለሀብቶች ጋር እንዲቀራረቡ ከፍተኛ እድል የሚፈጥርበትም ነው።
ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅ ፋይዳው ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል። በዚህ በኩል ባለሀብቶች እና በዘርፉ የተሰማራው የግል ዘርፍም ድርሻቸው የጎላ መሆኑን አመልክተው፣ ባለሀብቶች ያለውን ሀብት ተመልክተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ማዕድኑን በሚፈለገው ደረጃ አልምተን ተጠቃሚ መሆን ካልቻልን የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የሚያግዝ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ የታመነበት ብሔራዊ የማዕድን ካውንስል መቋቋሙንም አስታውቀዋል። ባለድርሻ አካላት በጋራ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከ90 በላይ ኩባንያዎች በተሳተፉበት በዚህ ኤክስፖ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማዕድናት፤ ቴክኖሎጂ፤ ሲሚንቶና ብረት ይዘው የቀረቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ ኤክስፖው ከዚህም ባሻገር በኮንፈረስ የታጀበና ብዙ እውቀትን ያስጨበጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኤክስፖውን በብዙ ነገሩ ልዩ ነው ሲሉ ገልጸውታል። በዘርፉ ልምድና ተሞክሮዎች ያሏቸው ሀገራት ልምዳቸውን ያጋሩበት፣ በተመሳሳይ የሀገሪቱ ማዕድናት ምን እንደሚመስሉ፤ የት እንደሚገኙና በምን መልኩ መልማት እንዳለባቸው ያመላከቱ ጥናቶች የቀረቡበት መሆኑን ልዩ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ለአምራቾች፣ ለባለሀብቶች፣ ለመንግሥትም የቀጣይ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑን ተናግረዋል። ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎችም የዘርፉ እውቀት የት እንዳለ እንዲረዱ ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ጭምር በየትኛው ላይ፣ የት ቦታ ሄደው ማልማት እንደሚችሉ ምልክት የሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከኤክስፖው ጎን ለጎን ሶስት ሲምፖዚየሞች ተካሂደው ውይይቶች ተደርገዋል። በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ታረቀኝ ታደሰ በኤክስፖው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል አንዱ ናቸው። እሳቸውም ከማዕድን ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት አንድ አካልን ብቻ መጠበቅ አይገባም፤ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው ሲሉ ይገልጻሉ።
በማዕድን ጉዳይ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ተባብሮ መሥራት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ። ለዚህም ምክንያቱ ሀብቱ የጋራ መሆኑን፤ ተጠቃሚነቱም ሆነ ጉዳቱ እንደዚያው የጋራ መሆኑን ያመለክታሉ። ‹‹ለሥራ ሁሉ ርብርብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ሀብት ባለቤት እንደሆነች መናገር ብቻ በቂ አይደለም። ከዚያ ተሻግሮ ማልማቱ ላይ ተጋግዞ መሥራት ይገባል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ታረቀኝ እንዳሉት፤ የማዕድን ዘርፍን የማልማት ሥራ በርግጥ ብዙ ሀብት፤ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይልን፣ ቴክኖሎጂዎችን ይጠይቃል። በዚህ በኩል ደግሞ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል።
ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋል። መንግሥት በዚህ በኩል ቁርጠኛ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፤ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይህን እድል መጠቀም ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ እንደነዚህ ዓይነት ኤክስፖዎችን ወደተግባር በመቀየሩ በኩል ትኩረት ከተደረገ መልካም እድል ይዘው ይመጣሉ። ስለዚህም ሁሉም ቃል የተገባውን ወደ ሥራ ይቀይረውና ማዕድኑን ለሀገራችን እድገት እናውለው ሲሉ ይመክራሉ።
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ወርቁ በኤክስፖው ተሳታፊ ከነበሩ መካከል ናቸው። ሮማርብል ኤንድ ግራናይት ትሬዲንግ የተባል ድርጅት አቋቁመው በአምራችነትና አከፋፋይነት ይሰራሉ። ሀገሪቱ በርካታ የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ያላት ብትሆንም ይህንን ሀብት አልምቶ መጠቀም ላይ ብዙ ርቀት አለመጓዟን ከቀረቡት ኮንፍረንሶች መረዳት እንደቻሉ አስታውቀዋል። ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሠረት ሊጥል እንደሚችል ገልጸዋል። ዘርፉ በቀደሙ ጊዜያት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን መታዘባቸውን ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት ምን ዓይነት ለውጦች እየመጡ እንደሆነ የራሳቸውን ድርጅት በአብነት ጠቅሰዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት መለየትና ሀብቱን ማስተዳደር የሚያስችል አቅም በመገንባት በኩል ውስንነቶች አሉባት። ለዚህም ማሳያው በርካታ የማዕድን ዓይነቶች ሀገር ውስጥ ቢኖሩም፣ ከውጭ ሀገር በማስመጣት ጥቅም ላይ ሲውል እየታየ ያለበት ሁኔታ ነው።
ይህ ደግሞ ሀገሪቱንም ሆነ ነጋዴውን ወይም አከፋፋዩን በብዙ መልኩ ይጎዳል። አንዱ የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ሲሆን፤ ኩባንያው እቃውን ለማምጣት ዶላር ሲጠይቅ በበቂ ሁኔታ እንዳያገኝ ያደርገዋል። ከዚያም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ መጠቀም ያለባትን ያህል እንዳታገኝ ያስችላታል። የውጭ ምንዛሬውን መስጠት እንጂ መቀበል ላይ ብዙም ተጠቃሚ አትሆንም። የማዕድን ውጤቶች በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ቢሆንና አከፋፋዮች ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡት ማዕድን ቢኖራቸው ብዙ ነገሮች ይቀላሉ። የውጭ ምንዛሬ ማውጣቱ ይቀርና ማስገባቱ የተለመደ ይሆናል።
በአሁን ወቅት መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ የሰጠው ትኩረት እነዚህንና መሰል ችግሮችን እንደሚፈቱ ያግዛል ያሉት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፣ ድርጅታቸው እምነበረድ፤ ግራናይትና ላይም ስቶንን በሀገር ውስጥ ሲያመርትና ሲያከፋፍል በብዙ መልኩ የውጭ ምንዛሬን አድኗል። በእንደነዚህ ዓይነት ኤክስፖዎች ደግሞ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል ሥነ ምህዳርም መፍጠር ችለናል ሲሉ ይገልጻሉ። ምክንያቱም ኤክስፖው ከአስመጪና ላኪዎች፣ ከውጭ ኩባንያዎች እና በዘርፉ ከሚሰሩ አካላት ጋር አስተዋውቆናል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኤክስፖው ከሌሎች የሥራ ልምዶችን እንድንቀስም አስችሎናል ሲሉ ጠቅሰው፣ እኛ የሌሉንን የእምነበረድ አሠራሮች ከሌሎች እንድንቀስምና ልምድ እንድንለዋወጥ፤ ገዢ ደንበኞችንም እንድናፈራ አስችሎናል። ስለዚህም ኤክስፖው በብዙ መልኩ ለእኛ ልዩ ትርጉም አለው ሲሉም አመላክተዋል።
‹‹ሥራ ለእድገት ኦፓል አምራች ማህበር›› በሚል ድርጅት በኦፓል አምራችነት የተሰማሩት አቶ ማስሬ ሀሰን፣ መንግሥት የብዝሀ ኢኮኖሚ አተያይን ተግባራዊ በማድረጉ የማዕድን ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጓል ይላሉ። ይህ ደግሞ በተለይ በባህላዊ መልኩ የሚያመርተው ተደራጅቶ በዘመናዊው መንገድ ወይም በኢንዱስትሪ የሚያመርትበትን፤ በጥራት አምራች የሚሆንበትን እድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከሀገሪቱ የማዕድን ሀብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ይሰማናል የሚሉት አቶ ማስሬ፣ በማህበር ተደራጅቶ መሥራትን ያወቅነውና ተጠቃሚ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው ሲሉም ይገልጻሉ። የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ እንደሚፈልግ ተናግረው፣ መንግሥት ከዚህ አኳያ ድጋፍ ሲያደርግ በተወሰነ መልኩ እያየን እንገኛለን፤ ድጋፉ እኛንም ቢያካትተን መልካም ነው ሲሉም ጠይቀዋል።
‹‹አሁን ባለንበት ደረጃ ብዙ ጉልበት እያፈሰስን ነው ማዕድኑን የምናወጣው። ከዚያ ይልቅ የምናመርትበትን ቴክኖሎጂ የምናገኝበት እድል ቢመቻች ብዙ ነገሮችን መቀነስ እንችላለን። ለአብነት በብዛትና በጥራት ማምረት፣ ለሀገር ውስጥ አከፋፋዮች በቀላል ዋጋ ማቅረብ እንድንችል ያግዘናል ብለዋል።
የማዕድን ሀብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅና ረጅም ጊዜ የሚፈልግ እንደሆነ በትምህርት ከአገኘነው ልምድ እናውቃለን ያሉት አቶ ማስሬ፣ ይህ ካልተገኘ በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ጠቁመዋል። መንግሥት ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶችም አቅማቸውን በማሰባሰብ በዘርፉ ኢንቨስት ቢያደርጉ፤ እንደ እኛ ዓይነት ማህበራትን ቢያግዙ፣ አልያም በጋራ የምንሰራበትን እድል ቢያመቻቹ መልካም ነው ብለዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016