ገና እየነጋ ነው..ሁለት ዓይነት የብርሃን ቀለም በበሯ ሽንቁር ይታያታል። በመኝታዋ ግርጌ ካለው የግራር ዛፍ ላይ ወፎች ሲንጫጩ ይሰማታል። የጎረቤቷ የእማማ ስህን አውራ ዶሮ በማን አለብኝነት ሲያንቃርር ይሄም ይሰማታል። ማለዳዋ እንዲህ ነው በወፎች ንትርክና በአውራ ዶሮ ድንፋታ የተሞላ። ባልመሸና ባልነጋ ሁለት ዓይነት ዓለም ውስጥ ሆና ስለ ነገ የምትጨነቅ።
ማለዳ ትወዳለች..ማለዳ የነፍሷ ውብ ሥዕል ነው። በትላንት በዛሬዋና በነገዋ ውስጥ የተቀለመ። ራሷን ሙሉ ሆና የምታገኘው በአራስ ጀንበር ፊት ነው። ንጋት የሕይወቷ መጀመሪያና መጨረሻ ነው። ጀንበር ምስራቅ አድማስ ላይ ስታቅላላ፣ ሰማይ በቀይና በጥቁር ሁለት መልክ ብርሃን ሲያሸበርቅ መኖር ደስ ይላታል። ምድር በአራስ ጀንበር ስትረሰርስ፣ ቀዬው የእንቁላል አስኳል ሲመስል ያኔ ሌላ ናት። ራሷን ፈልጋ የምታገኘው በዚህ እውነት ውስጥ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ መኖር የምንጊዜም ምኞቷ ነው።
የነፍሷን ውብ ስዕል ንጋትን ሽታ ከነሌሊት ልብሷ ወደ መስኮቱ ተራመደች። መሬት የሚልስ ረጅም ልብሷን በእጆቿ አንቃ። ጸጉሯ ከሌሊት ልብሱ አፈንግጦ ጀርባዋ ላይ ይቦርቃል..እናቷን በሚያስታውሳት መልኩ ተጎንጉኖ። ጸጉሯ የእናቷ ማስታወሻ ነው…በወር አንድ ጊዜ አብረሃም እንደሚወደው ካልተሰራች በስተቀር ሁሌም ሹሩባ ነው። አብረሃም የልጅነት ፍቅረኛዋ ነው። አሁን የት እንዳለ አታውቅም። ድንገት ነው እንዲህ እንደ አሁኑ ማለዳን ሽታ በቆመችበት ወጥቶ የቀረው። በነፍሷ የሁለት ሰዎች ንብረት ናት.. የእናቷና የአብረሃም። እናቷ የአዕምሮ ህመምተኛ ናቸው አማኑኤል ሆስፒታል ነው የሚገኙት። ሁሌ ጠዋትና ማታ ከሹሩባዋ ጋር እየሄደች እቅፋቸው ውስጥ ትወድቃለች። እስከ አስራ ስምንት ዓመቷ ድረስ ጸጉሯን የሚሰሯት እናቷ ነበሩ። ያንን ሁሉ ዘመን ከሹሩባ ሌላ ሰርተዋት አያውቁም። ከነሹሩባዋ እናቷ ፊት መቆም ደስ ይላታል..እናቷን ከህመም የሚያሽርላት ይመስላታል። ትላንትን የሚመልስላት ይመስላታል። አብረሃም በነፍሷ ላይ ሳይሞት የሚኖር ነፍስ ነው። ጠይም ነው..እንደ መስቀል ደመራ እንጨት ዘለግ ያለ። እንደ እናቷ የሳለችው በሕይወቷ ውስጥ ዳግም እንዲፈጠር የምትሻው አንድ እውነቷ ነው። ንጋትን ያስለመዳት..ማለዳን ያስወደዳት እሱ ነው። ሁሌ እንዲህ እንደ አሁኑ በሚነጋ ሰማይ ፊት እሷን አጠገቡ አድርጎ ‹እኔና አንቺ ጀንበርና ሰማይ አንድ ዓይነቶች ነን። አንዳችን ያላንዳችን ስፍራ የለንም። ሰማይ ለጀንበር መድመቂያዋ ነው። ጀንበር ለሰማይ ውበቱ ናት። እኔና አንቺም እንዲሁ ነን..እንደዚህ ንጋት ይላት ነበር።
ሊነጋ ያለን ሰማይ እንደማየት ደስታ የላትም። ከደመና ለመውጣት የምትተናነቅን ጀንበር እንደማየት ፍሰሀ የላትም። ብርሃን ከጨለማ ውስጥ ሲወጣን የመሰለ ድንቅ ተፈጥሮ አታውቅም። በብርሃን የተሳለን ድንቅ ተፈጥሮ ቆሞ እንደማየት ጥበብ አታውቅም። በጎጆአቸው ውስጥ ሆነው የሚያንሾካሹኩ ወፎችን እንደመስማት፣ በቤታቸው ውስጥ ሆነው ንጋት አብሳሪ አውራ ዶሮዎችን እንደማድመጥ ጥዑም ሙዚቃ አታውቅም። በጋጣቸው ውስጥ ሆነው፣ በጉሬያቸው ውስጥ ተደብቀው የሚቁነጠነጡ ነፍሳትን እንደመስማት ዓለም የላትም። ግን ብዙ ናፍቆት አለባት..ብዙ ትዝታ። በሕይወቷ ውስጥ እንዲመለሱ፣ ዳግም እንዲፈጠሩ የምትፈልጋቸው ትላንትናዎች አሉ። ትኖራቸው ይሆን? አታውቅም።
መስኮቱን ከፈተችው…እንዳሰበችው ሆነላት። ጠይም ምድር፣ ጠይም ሰማይ፣ ጠይም ተፈጥሮ ፊቷ ላይ ተጋረጠ። ብርሃንና ጨለማን የቀላቀለ ጅብማ ዓለም ተቀበላት። ደስ አላት..ሰማያዊ ደስታ። እንዲህ ደስ የሚላት ከእለታት አንድ ቀን ነው እና እንዲህ እንደ አሁኑ ሊነጋ ባለ ሰማይ ስር ስትቆም። እንዲህ ደስ የሚላት በመኝታዋ ግርጌ ካለው የግራር ዛፍ ላይ ያሉ ወፎች ሲንጫጩ..የእማማ ስህን አውራ ዶሮ ሲጮህ..እና እናቷ ፊት ስትቆም..አብረሃም ትዝ ሲላት።
ጎረምሳ ንፋስ አጠናፈራት። ደረቷን አላግቶ፣ የሌሊት ልብሷን አወናጭፎ ወደ ሳሎኗ ሲገባ አላስተዋለችውም ነበር። ወደ ሰማይ አየች..ቀይ ጥቁር፣ ቡናማና አመዳማ የብርሃን ሽርጥ አሸርጧል። ወደ ምሥራቅ ቀና አለች.. ምሥራቅ አድማስ በብርሃን ለሀጭ ተዝረክርኳል። ልጃገረድ ኮረዳ ጀንበር ማርያም..ማርያም በሚሉ ወዳጆች ታጅባ ንጋትን ለመውለድ ስታምጥ ይታያታል። በዙሪያዋ ሽር ጉድ የሚሉ ጠይምና ቀይ ዳማ የብርሃን መልኮች ከበዋታል። የእግዜር እውነት ይገርማታል። በመኝታዋ ግርጌ ዋርካው ላይ የሰፈሩት አእዋፍት ማለዳን ሲያበስሩ ይገርማታል። የጎረቤታቸው የእማማ ስህን አውራ ዶሮ እኩለ ሌሊትን ለመንገር ነፍስ ማወቁ ይሄም ያስደንቃታል። የእግዜር እውነት ይገርማታል። በብርሃን ውስጥ ጨለማ፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማኖሩ፣ በትላንት ውስጥ ዛሬን..በዛሬ ውስጥ ነገን መደበቁ ያስደንቃታል።
ወደ ጀንበር አየች..ምጥ ላይ ናት..ብርሃንን ለመገላገል። እዬዬዋ ይሰማታል..ልጇን ወልዳ ለመሳም ያላት ጉጉትም። የሰው ልጅ ያልደረሰበት የተፈጥሮ እውነት ንጋት ውስጥ ያለ መሰላት። በመኖር ውስጥ ያለው ስውር እውነት መሽቶ መንጋት..ነግቶ መምሸት ነው ስትል አሰበች። በንጋት ስር መቆም፣ በንጋት ስር ተፈጥሮን መቃኘት ደስታዋ ባለፈ የእውነቷ መገኛ ስፍራ ነው። የጠፋባትን እውነት በንጋት ጉያ ውስጥ ነው የምታገኘው። እንዲመለሱ የምትሻቸውን ትላትናዎች በመስኮቱ አሻግራ ሰማዩ እርቃን ላይ ነው የምታያቸው። ከቀይና ከጥቁሩ የብርሃን ጓል እያጠቀሰች ራሷን ሳለችው። እየነጋች..እየፈካች ራሷን አገኘችው።
ኮቴ ሰማች..
በንጋት ትካዜ ውስጥ ናት። የጀንበርን ምጥ እያማጠች..ጭንቀቷን እየተጨነቀች። በትካዜዋ ውስጥ ሳለች አንድ ሰው ውልብ አለባት…ከጨለማው ጋር የተመሳሰለ አንድ ሰው። እንደ መስቀል ደመራ ዘለግ ያለ።
ወደምትናፍቀው እውነት እየቀረበች እንደሆነ አላስተዋለችም። እምነቷን ከጀንበሯ መገላገል በኋላ ወዳለው አዲስ ዓለም አድርጋ ጠበቀች። እንደዛሬ የሆነ ንጋት ያየች አይመስላትም። በጀንበር ጉያ ውስጥ ይሄ ነው የማትለው የሆነ እውነት ይታያታል። ወደ እሷ የተዘረጋ እውነት..
በቆመችባት ምድር ወገገ አለች። ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሰማይ ቀና አለች..ጀንበር ወልዳ..ምሥራቅ አድማስ በብርሃን አቅላልቶ አየች። የምትጠበቀው እውነት ይሄ ነበር። ልትደርስበት የምትሻው ሀቅ ይሄ ነበር…ሳቀች በነፍሷ።
እለተ ማክሰኞ ወገግ ሲል ከመስኮቱ ጋ ፈቀቅ አለች። ወደ እናቷ ጋ ልትሄድ ወደ ኋላዋ ስትዞርና በሩ ሲቆረቆር አንድ ሆነ።
በሩን ከፈተችው..
ያየችውን ማመን አልቻለችም..እንደ መስቀል ደመራ እንጨት ዘለግ ያለ አንድ ሰው በር ላይ ቆሟል። አብረሃም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም