ነገ ልደቱ ነው..ልደቱ ሲቀርብ ደስ አይለውም:: በልደቱ ፊትና ኋላ ውስጥ ሠላም የለውም..ኀዘንተኛ ነው:: የሕይወቱ ውብ ቀለም መደብዘዝ የሚጀምረው በዚህ ሰሞን ነው:: በሕይወቱ ምርጥ የሚለውን ነገር በልደቱ ማግስት ያጣ ነው:: አሁንም የሆነ ነገር የሚሆን ይመስለዋል:: የሆነ ነገሩን የሚያጣ ይመስለዋል:: ምኑን እንደሚያጣ ግን እርግጠኛ አይደለም ምክንያቱም ምንም የለውምና:: በዚህ ሰሞን..በዚህ ስሜት ከቤት መውጣት አይፈልግም ግን አንድ የማይቀርበት ቀጠሮ አለው::
የልጅነት ጓዳኛው ከውጭ ሀገር መጥቶ እሱን ለማግኘት እየሄደ ነው:: ልደት ባይኖረው..እናቱ የተወለደበትን ቀን ባትነግረው ምነኛ ደስተኛ ነበር:: ልደቱ ደርሶ በሠላም ወጥቶ የገባበት ቀን የለም:: ገደቢስነቱ ከልጅነቱ የጀመረ ነው:: ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ወንዝ ወርደው ሲዋኙ ደራሽ ውሃ መጥቶ ሁለቱን ጓደኞቹን የነጠቀው በልደቱ ቀን ነበር:: በልጅነቱ ስም ጠሪያቸውን ፈንክቶ ለአንድ አመት ከትምህርት የታገደው በዚሁ ቀን ነበር::
ዕድለቢስነቱ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም አልተወውም የመጀመሪያ አመት ተማሪ እያለ በጣም የሚወደውን ጓደኛውን በመኪና አደጋ ያጣው ለልደቱ የሚሆን ዕቃዎችን በመገዛት ላይ እያሉ ነበር:: በአመቱ ህያብን አጣት:: ህያብ የሕይወቱ የብዙ ነገር መጀመሪያ ናት:: ዓለም እሷን ተደግፋ የቆመች ይመስለዋል:: በፍቅሯ፣ በውበቷ የቆነጀች ይመስለዋል::
የልክ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ይላታል:: ይገርመዋል ዛሬም ድረስ በእሷ እውነት ነው የሚኖረው:: በሕይወቱ ውስጥ የእሷ አለመኖር ሁሌም ይቆጨዋል:: በታሪኩ ውስጥ ደምቃ የደበዘዘች አንድ እውነቱ ናት:: እንዴት እንደተለያዩ ሲያስብ እሷን ለመጥላት አንድ ምክንያት ያገኘ ይመስለዋል..ግን ጠልቷት አያውቅም:: በሕይወቱ ውስጥ እንዲሆን የሚፈልገው አንድ ተዐምር ቢኖር የእሷ በእሱ ሕይወት ውስጥ ዳግም መብቀል ነው:: ግን መቼም የማይሆን ምኞት ይለዋል…
‹እንዴ ነበር የተለየችው? መቼም አይረሳውም..:: በልደቱ ቀን ላይ ልደቱን እያከበሩ ነበር:: ድንገት ስልኩ አንድ የጽሑፍ መልዕክት መቀበሉን ጮሆ ተናገረ:: ስልኩ ህያብ ጋ ስለነበር..የተላከውን መልዕክት ከፍቶ ለማየት ዕድል ነበራት:: መልዕክቱን አየችው..‹የኔ ፍቅር እንኳን ተወለድክልኝ:: በጣም ነው የማፈቅርህ ያንተው ሳምሪ› ይላል:: ከዛ ቴክስት በኋላ ህያብ ዳግም ወደ ሕይወቱ አልመጣችም:: ስልኩን ብላክ ሊስት ውስጥ እስከጨመረችበት ጊዜ ድረስ እየደወለ ሊያስረዳት ሞክሮ ነበር ግን ስልክ ከመዝጋት ባለፈ የፈየደው አልነበረም:: ጭራሽ እሱን ላለማየት ብላ ዩኒቨርሲቲ መቀየሯን ሰማ::
በዚህ ሁሉ እውነት ልደቱን ይፈራዋል:: በተለይ ሰዎች የሚሞቱበት ቀን ከተወለዱበት ቀን ጋር የተያያዘ ነው የሚል ጽሑፍ ካነበበ በኋላ ስጋቱ በእጥፍ ጨምሯል:: ልደቱ በቀረበ ቁጥር ለሞት የቀረበ ይመስለዋል:: እያጣቸው ያሉት ውድ ነገሮች የሞቱ ዋዜማ ይመስሉታል:: ጭራሽ የልደቱን መምጣት ተከትሎ ሰሞኑን እንቅልፍ የሚባል በዓይኑ አልዞረም:: በተኛበት የሚሞት እየመሰለው ቁጭ ብሎ ማደርን ልማድ አድርጎታል:: በዚህ ጊዜ ከቤት መውጣት አይወድም:: ሥራ በመቅረትም እንደልደቱ ሰሞን ሪከርድ የለውም::
በቃ የሆነ መኪና ድንገት መጥቶ የሚገጨው ይመስለዋል:: የሆነ ሕንፃ ተደርምሶ የሚያጠፋው ይመስለዋል:: በእግረኛ መንገድ ላይ እየሄደ እንኳን ሞቱን ነው የሚያስበው:: አሁን ራሱ ለመሞት የሚሄድ ነው የሚመስለው:: ጓደኛው ሞት ሆኖ የሚጠብቀው ነው የሚመስለው:: ምን ነበር የልደት ቀኑን ባያውቀው..ምን ነበር ጳጉሜ 2ትን ባያውቃት:: ብዙዎች የልደታቸውን መቅረብ ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ሲለዋወጡ፣ ሲደሰቱ፣ ሲጨፍሩ ሲያይ ይገርመዋል:: ብዙዎች ልደታቸውን ለማክበር ቦታ ሲመርጡ፣ እንግዳ ሲጠሩ ሲያይ ያስቀናዋል:: ብዙዎች የወዳጆቻቸውን ልደት በሰርፕራይዝ ሲያደምቁ፣ በኬክና በስጦታ ሲያስቡ ሲያይ በራሱ እንዲህ መሆን ይቆጫል::
በሕይወቱ ሁለት ነገሮችን አብዝቶ ይፈራል አንዱ የልደት ቀኑ ነው..አንዱ ደግሞ የሞቱ ቀን:: መኖር የሚወድ ሰው ነው:: ሕይወትን እስከ መጨረሻው የዕድሜ ጥግ ድረስ መኖር ይሻል:: ሕይወት ብርቁ ናት..መኖር የምንጊዜም ህልሙ ነው:: በሕይወቱ ሁለት ሴቶችን አይረሳም..አንዷ መስህብ ናት አንዷ ደግሞ ህያብ:: መስህብ ከህያብ እንዲለያይ በልደቱ ቀን ላይ የውሸት ቴክስት ጽፋ የላከችለት የዲፓርትመንታቸው የመጨረሻ አመት ተማሪ ናት:: እንደምትወደው ብዙ ጊዜ ነግራው የሚወዳት ፍቅረኛ እንዳለችው ነግሯት ነበር::
ህያብ የብዙ ነገር መጀመሪያው ናት..ምድርን ወደ ገነት የቀየረችለት፣ ሕይወትን እንዲወድ እንዲያፈቅር ያደረገችው የነፍሱ ውብ ቅኔ:: በመስህብ የውሸት ቴክስት አቅም አጥታ የራቀችው፣ እንደዚያ ሲለምናትና ሊያስረዳት ሲሞክር የገፋችው..:: እንደ አባትና እናቱ እኚህ ሁለት ሴቶች ሕይወቱን ሙሉ ያመራምሩታል:: መስህብ ፍቅርን አታውቅም:: ፍቅር ለሚወዱት መኖር እንደሆነ ገና አልደረሰችበትም:: ራሷን በማፍቀር የምትኖር ጭራቅ ናት:: ህያብ ብዙ ፍቅር አላት..ፍቅሯ ግን እውነት የለውም:: ከምታየው ይልቅ በምትሰማው ውስጥ ናት:: እምነቷ መጨረሻ የለውም:: በአእምሮዋ ሳይሆን በአካሏ ውስጥ የበቀለች እንዲህም ናት:: ህያብ እውነት ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ላይ አብረው ነበሩ..ደስ በሚል እንግዳ ዓለም ውስጥ::
ለእሱ ሁሌም ትክክል እናቱ ናት:: የእናቱ ሀቅ አመራምሮት አያውቅም:: በሕይወቱ ውስጥ መቼም የማይረሳቸውን ሁለት እውነቶች አስቀምጣለች:: አንዱ የፍቅር እውነት ነው..ከመስህብና ከህያብ የራቀ የፍቅር እውነት:: ፍቅር ሞት የሌለበት ዓለም ነው:: ‹የሌሎች ጥላቻ የአንተን ህያው ፍቅር እንዳይገልብህ ሁሌም ከላይ ሁን› ስትል አደራ ብለዋለች:: በዚህ እውነት ውስጥ የኖረው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው:: ከእናቱ ህልፈት በኋላ በሕይወት ያለ አባቱ የእናቱን የልጅነት እውነት የሚሽር ሌላ እውነት አስተማሩት ‹ፍቅር ሁሌም እውነት አይደለም::
ፍቅር ሁሌም ጸዐዳ አይደለም:: ፍቅር እውነት ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያ ፍቅረኛዬን ትቼ እናትህን አላገባም ነበር:: ፍቅር ውስጥ እውነት ብቻ ዋጋ የለውም:: ዋጋህ ያለው በእውነትና በማስመሰል መካከል ነው ብለውታል:: አሁን ላይ በየትኛው እውነት እንደሚኖር አያውቀውም:: እናቱ ትሁን አባቱ ልክ ይሄንንም አያውቀውም:: በሕይወቱ ብዙ ቦታ ላይ እናቱን ልክ ሆና አግኝቷታል:: በሕይወቱ እጅግ ብዙ ቦታ ላይ የአባቱ እውነት ሲከተለው ደርሶበታል:: ህያብ የማን እውነት ናት? የእናቱ ናት? የአባቱ? አያውቀውም::
በሁለቱም እውነት ውስጥ ያለች ሌላ እውነት ትመስለዋለች:: እሱን ማፍቀሯ..በነፍሷ ውስጥ ነፍሱን ማስቀመጧ የእናቱ እውነት ይመስለዋል:: በውሸትና በማስመሰል ትልቅ ፍቅሩን መሻሯ..ትልቅ እውነቱን መግፋቷ፣ ሊያስረዳት ሲሞክር አለማድመጧ ደግሞ የአባቱ እውነት ይመስለዋል:: በየቱ ይኑር? ዓለም የማን ናት? እውነቷ ምንድነው? ብዙ ጥያቄዎች አንድ ላይ ግር ብለው በልደቱ ዋዜማ ወደተጨናነቀው አእምሮው ገቡ:: በዚህ ጊዜ ከቀጠሮው ቦታ ደርሶ ነበር::
በእናቱና በአባቱ እውነት እየዋለለ፣ ሞቱን እያሰበ ወደ አንድ ሕንፃ ሊገባ ሲንደረደር..አንድ መኪና ክላክስ አደረገለት::
ለእሱ ስላልመሰለው ወደ ኋላ አልዞረም..::
ከመኪና ጡሩንባ ጋር የተቀላቀለ ‹ፍትህ..የሚል አንድ ቀጭን የሴት ድምጽ ጆሮ ግንዱ ላይ አንባረቀ::
ቆመ..:: በቆመበት ይሄ ነው የማይለው በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለ ስሜት ዋጠው:: እንዲህ የሚጠሩት ሁለት ሴቶችን ያውቃል:: አንዱ እናቱ ናት..አንዷ ደግሞ ህያብ:: ሁለቱም አጠገቡ የሉም..ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? የልደቱ ማግስት አይደል..እየሞተ መሰለው እና ደግሞ ለዘላለም ህያው እየኖረ:: የቱን ይመን? በእናቱና በአባቱ እውነት መካከል ቆሞ ወደ ኋላው ዞረ::
በተከፈተ መስኮት ያጮለቀ ቀይ እግዚአብሔራዊ ፊት ዓለም ላይ ምርጡን ፈገግታ ይዞ ይታየዋል..
‹እየሞትኩ ይሆን? ራሱን ጠየቀ:: አብዛኞቹ መከራዎቹ ከዚህ ቀጥለው የመጡ ናቸው:: አብዛኞቹ ስቃዮቹ ሳቁን ተከትለው የተከሰቱ ናቸው::
ወደ ፊቱ ሁለት ርምጃ ተራመደ:: ዓይኖቹ በመስኮቱ አልፈው ቀይዋ ሴት ላይ ይንቀዋለላሉ:: መላአካዊ መልክ ወደ እሱ ፈገግ ብሎ ይታየዋል::
‹ይሄስ ምንድነው? የእናቱ ነው የአባቱ እውነት? ወይስ ያልደረሰበት ሌላ ሰማያዊ እውነት? ሳያስበው ሳቀ..የምንም ነገር መጀመሪያ በሆነ ቀን ላይ የቆመ መሰለው:: እግሮቹ ተራምደው ከፈገግተኛዋ ሴት አጠገብ አደረሱት:: ወደ እናቱ እውነት እየቀረበ ይመስለዋል:: ዓለም በእናት እውነት ውስጥ ያለች መሰለው:: በአባቱ እውነት ያጣውን ፍቅር በእናቱ እውነት አገኘው:: እናት እውነት..አባት እምነት::
ቀይዋ ሴት ህያብ ነበረች::
እንደዚያን ቀን መጥፎ ፊት አያቶ አያውቅም:: ሴት ልጅ መሆንም እንደምትችል ያኔ ነው ያወቀው:: ያጣት በዚሁ ቀን ነበር:: ህያብ የሕይወቱ ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያየ አሁንም ወደ ሞት እየሄደ ይመስለዋል::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016