‹‹ሀገራዊ ምክክሩ የትኛውንም ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት የምንጠቀምበት ሂደት ነው››የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር

በኢትዮጵያ ልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ እንዲሁም በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል። በዚህም ምክንያት እንደሀገር ለዓመታት የተከማቸውን የፖለቲካ ችግር በውይይት እና በብሔራዊ መግባባት እንዲፈታ ብዙዎች ሲወተውቱ ቆይተዋል።

በሀገሪቱ የተለያየ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ግጭቶችም፤ ለዓመታት እልባት ባላገኙ ታሪካዊ ክስተቶች እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች የመጡ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች እና ልዩነቶች በየጊዜው አፋጣኝ እርምጃ እየተወሰደባቸው ባለመሆኑ፤ አሁን እዚህ ደረጃ ላይ መደረሱን ብዙዎች ይጠቁማሉ።

እንደ ሀገር የሚታዩ ፅንፍ የወጡ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶችን ለመፍታት እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚስማማበት ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር መካሄድ እንዳለበት ከመስማማት አልፎ ፍሬያማ ተግባራትን የሚጠበቅበት ጉዳይም ነው።

ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ልዩነት በምርጫ ብቻ የማይፈታ በመሆኑ፤ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል የተባለውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ አቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው ከመሆኑም በላይ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ በአዋጅ በግልጽ ሰፍሯል። በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት ይሠራል ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮቹን በየካቲት 2014 ዓ.ም ከተሾሙለት በኋላ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከእነዚህም ጊዜያት ጀምሮ ከሁሉ በላይ የብሔራዊ መግባባት እንዳይኖሩ አድርገዋል በተባሉና ወደፊትም ልዩነቶችን አስፍተው ወዳልተገባ ችግር ውስጥ ይከታሉ የተባለላቸው ችግሮችን በመለየት በምክክር መፍትሔ የማፈላለግ ተልዕኮን ይዞ ሥራ እንደጀመረ ይነገራል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ገዢ መርሆች ያሉት ነው፡፡ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የብዙ ተግባራት ቅንጅት ወሳኙን ሚና ይጫወታል፡፡ በሂደቱ ያለፉ ሀገራትን ተሞክሮ መነሻ አድርጎ መሥራቱም አዋጭነት ይኖረዋል። በዚህ መሠረት እንደ ሀገር የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በማንኛውም ሀገር የሚካሄድ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት መርሆች የተገዛ መሆን እንደሚገባውም በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ የዘርፉ ባለሙያዎችም የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡

በግልፅ ከተቀመጡት የሀገራዊ ምክክር ሂደት መርሆዎች አንዱ አካታችነት ነው፡፡ አካታችነት ሲባል በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በሁለት ዓይነት መንገድ ሊተገበር ይችላል፡፡ የመጀመሪያው በተለያየ ምክንያት በውሳኔ ሰጪነት ድምፃቸው ሳይሰማ የኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ አካታችነት የሀሳብ ብዝኃነት እንዲኖር ማድረግና በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ አዳዲስ እና ምናልባትም ከዚህ ቀደም ያልወጡ ሀሳቦች እንዲንፀባረቁ ማስቻል ነው፡፡

ሌላው መርሆ የጋራ ባለቤትነት ነው፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሁሉም ባለድርሻ አካል በምክክሩ ሂደት ውስጥ የባለቤትነት ስሜት ሊሰማው ይገባል፡፡ በሂደቱም ባለድርሻ አካላት ሂደቱ የተሳካ እንዲሆንና ችግሮች ሲያጋጥሙም የመፍትሔው አካል ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡

በሰብዓዊነትና የሌላውን ችግር ለመረዳት መፍቀድ ከመርሆዎቹ መካከል ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ነው፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ አንዱ ሌላውን የሚያዳምጠው ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ሌላው ወገን ያለበትን ችግር በመረዳት እና ራስን በዛ አካል ቦታ አስቀምጦ በማየት መሆን ይገባዋል የሚለውን አስታራቂና ይበጃል የሚለውን ሃሳብም ማቅረብ ይኖርበታል።

ከመርሆዎቹ አራተኛው የሚመነጩ የመፍትሔ ሀሳቦች ዘላቂነት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም ሲባል በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሚነሱ የመፍትሔ ሀሳቦች ችግሮችን ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚፈቱ ሳይሆኑ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ የሚሰጡ ብሎም ዜጎች ለሀገራቸው ችግሮች ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማመንጨት ማኅበራዊ ውሎቻቸውን የሚያድሱበት ሂደት ሊሆን ይገባዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የኮሚሽኑ ሥራ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ያገባኛል በሚል መንፈስ አብሮ ሲራመድ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ እኛም በእዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታን አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በእስከ አሁኑ እንቅስቃሴው ምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚሠራውን የሚሄድበትን መንገድና የሚያልፋቸውን ነገሮች ብሎም ውጤታማ ሥራን ለመሥራት የሚከፈሉ ዋጋዎችን በሙሉ ሕዝቡ ሊያውቀው ሊገነዘበው ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ 17 ወራት አካባቢ እያለፉት ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ደግሞ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፤ በተለይም ሀገር ካለችበት ሁኔታ አንጻር የሚጠበቅበት ምን ዓይነት ተግባር ማከናወን ነው? የሚለውን በጥልቀት በማየትና በመገምገም ብዙ ርቀቶችን ለመጓዝ ሙከራን አድርጓል፡፡

አሁን ላይ የቅድመ ዝግጅት ጊዜውን አጠናቆ የዝግጅት ምዕራፉንም በማገባደድ ላይ ይገኛል። ይህም ሲባል በመላው ሀገራችን ምን መሠራት አለበት? ተሳታፊ ሊሆኑ የሚገባቸው እነማን ናቸው? የሚለውን የማየትና የመወሰን ሥራንም አብሮ እየሠራ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች የምንላቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሲሆኑ፤ ሁሉም አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ያሳትፋል። ለምሳሌ በራሳቸው የሚተዳደሩበት ዘዬ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የግልና የመንግሥት ሠራተኞች የሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ሰዎች እድሮች እንዲሁም በተያየ መልኩ ኅብረተሰቡ የሚያገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፤ ሁሉ ድምፃቸው መሰማት እና ችግሮቻቸው መታየት ያለበት፡፡ ሀገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ያላቸው አስተያየትና ሀሳብ መደመጥም ስላለበት ሁሉም ይካተታተሉ ፡፡

ሌላው በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችም እንደ ዜጋ ሀሳባቸውና አጀንዳዎቻቸውን መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያቀርቡበት መድረክ ሁሉ የማመቻቸት ሥራው በመሥራት ላይ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በራሱ ፈዋሽ ነው፡፡ ሕዝቦች ዜጎች ፊት ለፊት አይን ለዓይን ተያይተው መሠረታዊ በሆኑ ችግሮቻቸው ዙሪያ የሚነጋገሩበት ነው፡፡ ለመሸናነፍ ሳይሆን ለመረዳትና እውነትን አግኝቶ ሰላምን ለማምጣት የሚመክሩበት በመሆኑ፤ ኮሚሽኑም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ከኮሚሽኑ ሥራ በፊት ሀገራችን ላይ በሕዝቦች መካከል መቃቃሮች ሲኖሩ፤ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ሂደቱ አናሳ የነበረ ከመሆኑም በላይ የመጠፋፋት መንገዶችን በሙሉ ሞክረናቸው አልፈናል፡፡ ችግሮችን በአፈሙዝ የመፍታት ኩነቶች ውስጥ ገብተን በግጭት እና በጦርነት ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ በርካታ ዜጎቻችን አልቀውብናል፤ ሕዝቦች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ተኪ የሌለው የሰው ልጆች ሕይወት በጣም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ጠፍቷል። በመሆኑም አሁን ላይ ሁላችንም ወደሀገራዊ የምክክር ሂደት እንግባ ያለነው ይህ መንገድ እንደማያዋጣ አውቀን ነው፡፡ በሌላ በኩልም የመጣንበት መንገድ ሀገርን የሚያወድም፤ ብዙ የሚያከስር መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

የሚገርመው ነገር እኛ ወደዚህ የምክክር መድረክ እንድንመጣ ካደረጉን ነገሮች መካከል፤ አሁን እኛ እያደረግን ያለውን ነገር ሲያደርጉ የነበሩና ከዛም እንደ ሀገር መቀጠል አቅቷቸው የፈራረሱ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትን አይተናል። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ዕጣ እንዲደርሳት የሚፈልግ ዜጋ የለም፤ በመሆኑም ሀገራችንን ከዚህ ችግር ማውጣት፣ ማሻገርና ሀገርን መታደግ የሚቻለው በሀገራዊ ምክክር ብቻ ነው፡፡

አሁን የምክክር ኮሚሽኑ የደረሰበት ደረጃ የተሳታፊዎች ልየታ ላይ ነው፡፡ ይህ ሥራ ደግሞ የኮሚሽኑ ሥራ ሆኖ ሳለ የምንተማመንባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሂደቱ ውስጥ እንዲገቡና እንዲያግዙ ጥረቶች ተደርገዋል። እነዚህ የሚያግዙን አካላት ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ መምህራንና ሌሎችም አብረውን እየሠሩና ሂደቱን በቅርብ እየተከታተሉ እየተሳተፉበትም ነው፡፡ ‹‹ሂደቱ አካታችና አሳታፊ ነው››፤ የምንለውም እነዚህን እውነታዎች በመያዝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦እስከ አሁን በሄዳችሁበት ልክ በተለይም አብረዋችሁ ከሚሠሩት አካላት ውጪ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ተሳትፎ እንዲሁም ምክክር ያስፈልገኛል ይጠቅመኛል ብሎ የማመን ደረጃው እንዴት ይለካል?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ትልቁ የተገነዘብነው ነገር ቢኖር በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ጉጉት መኖሩን ነው፡፡ አንዳንዶች ሲገልጹት እንደውም ይህ ለሀገራችን የመጨረሻው እድል  ነውና እድሉን ማጣት የለብንም መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን ሀገራችን ቀደምት ብሎም ሰፊ ታሪክና ባሕል ያላት ትልቅ አገር ከመሆኗ የተነሳ የምክክር ኮሚሽን ያሉብንን እፀፆች በሙሉ በአንድ ጀንበር ይቀርፋል ማለት ደግሞ ይከብዳል። ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑና አሁን ባለው ፖሊሲ ሕግጋት ልንፈታቸው የማንችላቸው መንግሥት ሊፈታቸው ያልቻላቸውን ችግሮች ለመፍታት ይሠራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማኅበረሰቡ መካከል እልፍ ልዩነቶች አሉ፤ ይህ ደግሞ እየዋለ እያደረ በመካከላችን ትልቅ ክፍተት እንዲኖር አድርጓል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩም ያስፈለገው ከዚህ ለመውጣት ነው፡፡

ይህ ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ የሕዝቡ ፍላጎት መሆኑን ከሄድንባቸው አካባቢዎች በሙሉ ባየነውና በሰማነው ሃሳብ ለመገንዘብ ችለናል። በእርግጥ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ወደትግራይ ክልል የሄድነው አሁን በቅርቡ ነው፤ በዛም ቢሆን በሄድንበት ጊዜ ከክልሉ አመራሮች ጋር የመጀመሪያው ንግግር ተፈጥሯል፤ በቀጣይ ደግሞ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እናሳትፋለን፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የምክክር ኮሚሽኑን ሥራና ሂደት ሁሉም አምኖበትና በፍቃደኝነት እየተሳተፈበት ስለመሆኑ መናገር ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ሀገራዊ ምክክሩ በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ተጠቃሽና ውጤታማ እናደርገዋለን ብላችኋልና ይህ ምን ማለት ነው?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ምክክር ኮሚሽኑ እየተጓዘ ያለው ትልቅ ራዕይ ሰንቆ ነው ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ከታሪክ አንጻር ብንመለከት የመጣነው የነበሩ በርካታ እድሎችን አጥተን ነው፤ እነዛን እድሎች ያጣንበት ዋናው ምክንያት መመካከር አለመቻላችን ነው፡፡ በተደጋጋሚ በግጭት፣ በጉልበትና በኃይል ችግሮች እንዲፈቱ ተሞክሯል፤ አንዳንድ ምክክር መሰል ሂደቶች ቢኖሩም እንዲከስሙ ሆነዋል። ይህኛው ወይም አሁን በሀገራችን የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር አንደኛ አሳታፊነቱ የተጠበቀ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያካትት ተዓማኒነት ያለውና በሕዝቡም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ከተካሄዱት የምክክር ሂደቶች ሁሉ ግዙፉ ነው ብንል ማጋነን አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከፍተኛ ናት፤ የአገሪቱ ታሪክን ስንመለከት ደግሞ በራሱ ገላጭ ነው ፡፡

ሌላው በአፍሪካ ውስጥ የተካሄዱ አንዳንድ የምክክር ሂደቶች ቁንጽል በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተካሄዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የኬንያን ብናይ ድረ ምርጫ የተከሰቱ ኩነቶችን ለማብረድና ሕግ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማጽናት የተካሄደ ነው፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምክክር የማይዳስሳቸው አጀንዳዎች የሉም፡፡ በጣም ሰፊ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ እኛ እንደ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳው ያ ይሁን ወይም ይሄ ይሁን የምንልበት አግባብ የለም፡፡ ሕጉም አይፈቅድም፤ ነገር ግን እስከ አሁን ከተገነዘብነውና ካየነው በሕዝቡ ዘንድ ያለው ስሜትና የተሳታፊዎች ልየታ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ በሚደረጉ ስብሰባዎች፤ ምክክር የሚመስሉ ነገሮች ይካሄዳሉና እንደ ግብዓት በሰበሰብነው መረጃም የታዘብናቸው ብዙ ነገሮች አሉ።

ከግጭት አፈታት አንጻር ደግሞ የሩዋንዳው ሂደት በጣም የተሳካና የሰመረ ነው ይባልለታል። እውነት ነው፤ የተሳካ ስለነበር ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ያሸጋገረ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ግጭቱ በሁለት ጎሳዎች መካከል የተካሄደ ነበር። እኛ አገር ውስጥስ ችግሮች ያሉት በስንት ጎሳዎች መካከል ነው? ይህንን ቤት ይቁጠረው። በመሆኑም መሠረታዊ የሆኑትን ልዩነቶቻችንን በጥብቅና ሕዝቡ ራሱ በተሳተፈበት አግባብ የሚፈታበት ሂደት ይኖራል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ኮሚሽኑ የውጭ አገር ስኬታማ የምክክር ውጤቶችን እንደ ተሞክሮ መውሰዱ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ግን ደግሞ እንደ ሀገርም ብዙ የግጭት አፈታት ሂደት ያለን በመሆኑ እሱን ተሞክሮ ለመቀመር የተሄደበት መንገድ ይኖር ይሆን?

አምባሳደር መሐሙድ ፦ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምሥረታ አዋጅ ላይ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው። ይህም ማለት የአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሀገር በቀል እውቀትን መጠቀም እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም እነዚህን በተለይም የግጭት አፈታት፤ የመመካከር እና የመደማመጥ ባሕሎች በሰፊው ሀገራችን ላይ ይታያሉ። ያም ቢሆን የተጠቀምናቸው እስከ አሁን በጣም ውስን በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ ብቻ ነው። በመሆኑም እነዚህን እውቀቶች ወደሀገራዊ ምክክሩ እንዴት ልናመጣቸው እንችላለን? እንዴት እንጠቀምባቸው? የሚለው እየታሰበበት ከመሆኑም በላይ ወደምክክር ሂደቱ ዓውድ ስንገባ የምንተገብረው ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፦አንዳንድ ወገኖች የምክክር ሂደት የሚባለው ነገር የመንግሥት የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው ይላሉና እንደው እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ መጠቀሚያ ሳይሆን፤ የትኛውንም ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታትና ለመቅረፍ የምንጠቀምበት ሂደት ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው የሚሉ ወገኖች ሀሳቡ የራሳቸው ስለሆነ መተው የሚሻለው ነው፡፡ ሆኖም ሀገራዊ ምክክሩ የሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብ ነው ስንል ደግሞ ሕዝብ በራሱ አንደበት አጀንዳዬን ወደ መንግሥት ያቀርቡልኛል ብሎ የሚያምናቸውን ሰዎች ወክሎ ይልካል፡፡ እነዛ ተወካዮች ደግሞ አጀንዳዎቹን ይዘው በመምጣት ይቀረፃሉ፤ ይህ አጀንዳ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ካሉባቸው ዓለማት በሙሉ የሚላኩ ናቸው፡፡ አጀንዳዎቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ምክር ቤቱና አማካሪ ካውንስሉ በመቅረጽ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ይሆናል፡፡ በዚህም ሕዝቡ ምክክር ኮሚሽኑ ሂደቱን የሚያደርገው በእነዚህ አጀንዳዎች ዙሪያ ነው ሲል ይፋ ያደርጋል፤ ምንም የተደበቀ ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡

አጀንዳው ከሕዝብ የመነጨ፤ እንደገና ለሕዝብ የተላለፈ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ በእጅጉ የሚፈለግና ጠቀሜታውም ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ምክክር ይካሄዳል፤ ምክክሩ ተካሂዶ የሚወጡ ምክረ ሀሳቦች ደግሞ ዝም ብለው የሚቀመጡ ሳይሆኑ፤ መንግሥት እንዲተገብራቸው የሚሰጡ ናቸው፡፡ መንግሥት በቃ ይተግብራቸው ብሎ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አይበተንም፡፡ ምን ያህሎቹ ተተገበሩ? በምን አግባብ ተስተናገዱ? ብሎ ያያል ይጠይቃል፤ ይከታተላል፡፡ በመሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ ይሳካል፤ ከአፍሪካም ቀዳሚ ይሆናል ብለን የምንገልጸው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር መሐሙድ፦ እስከ አሁን ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህም ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህ ጥረት ግን ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፤ ምክንያቱም ሁሉንም ያሳተፈ ስንል መንግሥት ሊሰማው የሚፈልገውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሊሰማው የማይፈልገውንም ሀሳብ ሀገራችን ላይ እስካለ ድረስ፤ እነዚህም አካላት የምክክሩ አካል የማይሆኑበት ሂደት ፈጽሞ አይኖርም፡፡

እስከ አሁን ድረስ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተቀራረብን እንሠራለን፡፡ በሂደቱ ጥርጣሬ ያላቸው አሉ፡፡ ይህም የራሳቸው አቋም በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጥርጣሬ እንዲወጡ ለማድረግ በእኛ በኩል የማያቋርጡ ጥረቶች ይደረጋሉ። ሆኖም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እነዚህ ሰዎች አቋማቸው የተለየ ነው ብሎ የማግለል ፍላጎት የለውም፡፡

አዲስ ዘመን፦እንደ ምክክር ኮሚሽን አሁን በሥራችሁ ላይ ዋና ተግዳሮት የሆነባችሁ ነገር ምንድነው?

አምባሳደር መሐሙድ፦ በሀገሪቱ ያለው የሰላም መደፍረስ ትልቁ ተግዳሮታችን ነው። በእርግጥ ሀገራዊ ምክክር የሚካሄደው በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ብቻ አይደለም፤ በአንጻሩ ግጭቶች ባሉበት ቦታ ሁሉ የሚካሄድበት አጋጣሚም አለ። ይህ ከመሆኑም በላይ የግጭት ተዋንያንም መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ምክክሩ እንዲገቡና የምክክሩ አካል እንዲሆኑ ይፈለጋል። በሌሎች ሀገሮችም በዚህ መልኩ የተሄደባቸው ሁኔታዎች አሉ ፤ እነዚህንም ተሞክሮዎች ቀምረን በሀገራችን ውስጥ ነፍጥ ያነሱ ወገኖች ወደምክክሩ እንዲመጡ ጥረቶቹ ይቀጥላሉ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን አምባሳደር በተለይም ጽንፍና ጽንፍ ያሉ ሀሳቦችን ይዘው ነፍጥ ያነገቡ አካላትን ወደ አንድ ማምጣት ለኮሚሽኑ ፈተና አይሆንበትም? እንዴት እንወጣዋለን ብላችሁ ታስባላችሁ?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ትልቁ የምክክር ሂደቱ ተግባር ብሔራዊ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ሀገራዊ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር በግልጽ በጋራ መምከር ችግሮችን በግለሰቦች በቡድኖች ላይ ሳይሆን በችግሮቹ ዙሪያና እነሱን ለመፍታት በጎና ቀናኢ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የሀገራዊ ምክክር ውጤቱ ሀገራዊ የጋራ መግባባትን የጸና የመንግሥት ሥርዓት መገንባትን አዲስ የሆነ ፖለቲካዊ ምዕራፍ ማስጀመር ነው፡፡

እዚህ ላይ ግን በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች ከተፈቱ በቀጣይነት ሌሎቹም የማይፈቱበት ምክንያት የለም ፡፡

አዲስ ዘመን፦ ይህ የምክክር ሂደት ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል?

አምባሳደር መሐሙድ፦ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ይጠበቃል፡፡ ከአረጀውና ለዘመናት ወደነውጥ ወደግጭትና ነፍጥ ወደማንሳት ሲወስደን ከነበረው አስተሳሰብ ወጥቶ በሰከነና በተረጋጋ ዓውድ ውስጥ ገብቶ ወደምክክሩ መቀላቀል እንዲሁም ይወክለኛል የሚላቸውን ተሳታፊዎች በአግባቡ መምረጥ ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል ተሳታፊዎች ከውስጥና ከውጭ ጫና ራሳቸውን አግለው የማይበገሩ መሆን፤ ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገራቸውን የሚያስቡና የሚያስቀድሙ መሆን አለባቸው፡፡ ሀገራቸውን ካለችበት ችግር ለማላቀቅ ሌት ተቀን የሚሠሩ ዜጎች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ከታየን ደግሞ የሀገራችንን ችግሮች ለይተን አለመግባባቶቻችንን ለመፍታት እንችላለን የሚል እምነት አለን፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እስከ አሁን ከመጣችሁበት መንገድ ተነስተው፤ ቢሆን ብለው የሚመኙትን መልዕክት ያስተላልፉ?

አምባሳደር መሐሙድ፦ በውስጥም በውጭም ያለን ኢትዮጵያውያን ይህንን እድል ተጠቅመን ሀገራችንን ከችግሮቿ እንድትላቀቅ ሕቦቿም በእኩልነት በዴሞክራሲና በሰላም እንዲኖሩባት፤ የሰላሙ ትሩፋት ደግሞ ወደልማት አንቀሳቅሶን ሀገር እንድንገነባ የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን አምላክ ይርዳን!

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

አምባሳደር መሐሙድ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You