
አዲስ አበባ፡- ቢሾፍቱ ከተማን በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። በከተማዋ በአራት ቢሊዮን ብር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው።
የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በቢሾፍቱ ከተማ የቱሪዝሙ ዘርፍ ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሠራበት በመሆኑ ከተማዋን ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው።
እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለጻ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በጀት በመያዝ የተለያዩ የቱሪዝምና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው።
በሆረ አርሰዲ 283 ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ የውበትና የገጽታ ማሳመር ፕሮጀክት እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 500 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ለዘንድሮው ዓመት ሥራ 150 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን አመላክተዋል።
የሆረ አርሰዲ ፕሮጀክት በቀጣይነት በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን አስገንዝበው፤ የኢሬቻ ማክበሪያ ቦታው ለቱሪስቶች መስህብነት እንዲያገለግል የሚያስችል ሰፊ የፓርክ ግንባታ እንደሚከናወንበት ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ይዘት የአካባቢውን ባህልና ወግ በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ከአባ ገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎችና ወጣቶች ጋር በመነጋገር የታቀደ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የሆረ አርሰዲ ፕሮጀክት የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ወደ ፕሮጀክት ትግበራው ለመግባት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።
ከተማዋ የበርካታ ሐይቆችና የተፈጥሮ መስህቦች ማዕከል መሆኗን ተናግረው፤ የአየር ንብረቷ በርካታ ቱሪስቶችን የሚስብ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተማዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭና ቀዳሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ በዘርፉ ለመሰማራት ለሚመጡ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባስቦ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በመደበው በጀት ከሚከናወኑ ግንባታዎች መካከል 138 ፕሮጀክቶች የጨረታ ሂደታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ከ13 ፕሮጀክቶች ውጪ አብዛኛዎቹ በዘንድሮ ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል ለወጣቶች የሚተላለፉ 510 ሼዶች እንደሚገኙ ተናግረው፤ ፕሮጀክቶቹ በዋናነት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውና በቋሚነት የሥራ ዕድልን ሊፈጥሩ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በዘንድሮው ዓመት ለ40 ሺህ ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ፤ እስካሁን ለ15 ሺህ 156 ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ በከተማዋ የ24 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድና የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ንጣፍ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀው፤ የከተማውን ነዋሪዎች ኢኮኖሚ ሊያሳልጡ የሚችሉ የውበትና ቱሪዝም ሥራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አመላክተዋል።
በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ስምንት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የገለጹት አቶ ገዘኸኝ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለ25 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሐግብር የተጀመረ በመሆኑ አስገንዝበዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም