እሳትእናውሀ

ባሏ ትቷት የኮበለለው ጎረቤቴ ቡና ስትወቅጥ ይሰማኛል..ብቻዋን ልትጠጣው:: ጽናቷ እንዲህ ተክዤ ባለሁበት ሰዓት መበርቻዬ ነው:: ብቻዋን ጀግና የሆነች ሴት ናት:: ትላንት የማያስቆጫት..ነገ የማያስጎመጃት:: አንዳንድ ጊዜ እሷም መሆን እሻለው..ለምንም ለማንም ግድ የሌላትን ነፍሷን::

……….

ያልገቡኝ እንዲገቡኝ ብዙ ጠይቄ፣ ብዙ መጽሀፍትን አገላብጨ አውቃለው:: ግን አሁንም እንዳልገባኝ ነኝ:: በገባ ጥያቄ ያልገባን ሕይወት መኖር..መምረር..ነው አልኩ:: ከመምሬ አድባር ስር ጌታዋን ጥበቃ ቁጭ እንዳለችው ነፍስ፣ በኤፍራታዱር ጌታን እንዳስተኛችው ግርግም ነፍሴ ማረፊያ ቢኖራት:: ልቤ ቦታ ቢያገኝ..እላለው

ሕይወት..መንታ ነፍስ ናት:: እየሳቁና እየተሳቀቁ መጥተው የሚሄዱባት..ኖረው የሚያልፉባት:: የእግሬን መረማመጃ ከምን ባንጸው ከእንቅፋት እንደምድን አስቤ አልደረስኩበትም:: የሆነ ነገር እሻለው..እኔም ያልገባኝን የሆነ ነገር:: ለሀሳቤ ዓለም ጠባኛለች:: ዞሬ እዛው ነኝ::

የዓለም መጥበብ የሀሳብ መጥበብ እንደሆነ አልገባኝም:: ሰው በሀሳቡ ሲጠብ ዓለምን በጋቱ ይሰነዝራታል:: ዘላለማትን እንደ አንድ ቀን ንጋት ይዳፈራል:: አእምሮ ከፍትህ ሲርቅ፣ ልብ ፍቅርን ሲያጎድል ጠይቀን ለማንመልሰው ብንመልሰውም ልክ ለማንሆነው ግብዝ እውቀት እየተሰናዳን ነው::

ሁለት አይነት ሰዎች አሉ..በመኖር የሚስቁና የሚሳቀቁ:: ለሁለቱም ሕይወት አንድ አይነት ናት:: መነሻዋን የፈጣሪ ሀሳብ አድርጋ መድረሻዋን ሞትና ትንሳኤ ያደረገች:: ትንሳኤዋን ረስተው ሞቷን ብቻ የሚያስታውሱ ይሳቀቁባታል:: ሞቷን ረስተው በትንሳኤዋ ውስጥ የቆሙ ደግሞ ለመሳቀቅ ጊዜ አያገኙም:: እናም..ልብሳችንን ከፍ አድርገን ዓለምን የምናይበትን መነጽራችንን እናብስ..ያኔ ልክ መሆን እንጀምራለን:: የሚል ሀሳብ ከገባኝ ዘመን የለውም:: ፍርሀት የአእምሮ መጋረጃ ነው:: ጥሩውን እንዳንመርጥ የሚያደርግ:: ፍርሀት የስጋት ቦታ ነው:: የጥርጣሬና የተስፋቢስነት መነሻ:: ፍርሀትን ማሸነፍ ዓለምን መረዳት ነው:: የፍርሀት ማብቂያ የሕይወት መጀመሪያ ነው:: ፍርሀታችን የተሸነፈበት ቦታ ጋ መኖር እንጀምራለን:: እሱጋ ሕይወት አለ:: የሕይወት ትላልቅ ጥያቄዎች ከፈራ አእምሮና ልብ የሚወጡ ናቸው:: የሚል እውቀት ካወኩ ሰንብቻለው:: ግን አልበረታሁም:: ላለመፍራት ብዙ ታገልኩ:: የባሰ ፈሪ ሆንኩ..

……….

እንደ ጎረቤቴ ግድ የሌለው አእምሮ ናፈቀኝ:: ለሆነውና ለሚሆነው ግድ የሌለው:: ስለነገ የማይጨንቀው..ስለዛሬ ምንም የማይመስለው:: ሕይወትን በግዴለሽነት ውስጥ አላውቃትም:: ስኖር ተጠንቅቄና ተሳቅቄ ነው:: ግን እንደሀሳቤ ሩቅ አልተራመድኩም:: ከዛሬ የሚያርቀኝን እውነት እሻለው::

መኖር ስሻ ትቼው ወደመጣሁት ውብ ጊዜዬ አቀናለሁ:: በዛ ጊዜ ሕይወትን ያጣመችልኝ አንድ ነፍስ አለች:: ከእናቴ ቀጥሎ ሁሌ አነሳታለሁ:: አሁን በሕይወቴ ውስጥ ሁለቱም የሉም:: የእናቴ ትከሻ እንደ ገነት አውድ ናቸው…ብርሀን እየረጩ ውጋግ የሚሰጡኝ:: ያቀፉኝ ክንዶቿ..የጨበጡኝ እጆቿ በገነት እርፍኝ ደጅ እንኳን ደህና መጡ ሲሉ ድቃንን እንደሚቀበሉ መላዕክተ ሀመልማል መሳይ:: ያስተኛኝ ደረቷ..ያሞቀኝ ጉያዋ እንደ ክረምት ጣይ በነፍስ ቆፈን ላይ የሚያርፍ..:: በዚች ሴት ትከሻ ላይ ሕይወት ጥማኝ ሰው ሆንኩ:: ከዛም ከአንዲት የእናቴን መሳይ ነፍስ ካላት ወጣት ጋር ተዋሃድኩ:: የእናትና የሚስት ፍቅር ለወንድ ልጅ የዘላለም ድርሰቱ ነው..በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚጽፈው:: ሰው የሕይወትን ጨምዳዳ እንዳያይ አይኑን ቢሸፍን ኖሮ ብዙ ደስታ እንዳለው ይቆጥር ነበር:: ከእናት ወደ ሚስት ከሚስት ወደ ልጅ ከዛም ወደልጅ ልጅ..ሕይወትን በዚህ ብቻ እናሞካሻት ነበር::

የሕይወት ትልቁ ተንኮሏ ድንገት ሰጥታ ድንገት መንሳቷ ነው:: ከእናት እና ከሚስቴ በኋላ ሕይወትን አላምናትም:: በሁለቱም በኩል የዓለምን ክፋት አልተማርኩም:: በሁለቱም በኩል ስለሕይወት አልሰማሁም:: ሕይወት ውብ ብቻ እንደሆነች ነው የተማርኩት:: የእናት ልብ የልጆቿ የመከራ መሸፈኛ ነው:: የእናት ልብ ለልጅ እንደጓዳ ነው..ገመና መሸፈኛ:: በወላጆቻችን የተሸፈነ ብዙ ገመና እንዳለን የሚገባን ወላጅ ከሆንን በኋላ ነው:: በእናት ጥላ ስር የብዙ ልጆች መከራ ተከልሏል::

አንድ ልጅ አለችኝ..ከዛች ሴት የወለድኳት:: ማንነት ውርስ አይደል? ልክ እንደ እናቴና ሚስቴ ልጄንም ክፉ ላሳያት አልቻልኩም:: መከራዎቼን ደብቄ..ሳቄን እያሳየኋት አባቷ ነኝ:: ጉንጭዋን ስሜ አጠገቧ አረፍ አልኩ:: ብቻዋን ስትሆን በምትዝናናበት ዘመን አመጣሽ ቲክ ቶክ እየተዝናናች አቀርቅራለች::

‹አባ ባለፈው በለቀኩት ፎቶ እኮ ከሁለት መቶ በላይ አስተያየት አገኘሁ:: ደስ አይልም? አለችኝ በበራ ፊት.. አይኗን ከስልኳ ስክሪን ላይ ሳትነቅል::

ዝም አልኳት:: ብዙ ጊዜ እንዲህ አውርታኝ ታውቃለች:: አብሬአት ስሆን ብዙ ጊዜአችን የሚያልፈው በፎቶ ነው:: እንዲ ሁን እንደዛ ሁን እያለችኝ::

‹ትላንትና ለፖሰትኩት ፎቶ የተሰጠኝን አስተያየት ላንብብልህ› ብላ..በተቀመጠችበት ተመቻቸች:: ዝም ብዬ አስተውላታለሁ:: ዘመን ሰው ይፈጥራል ይገላልም የሚለው አባባል የመጣልኝ እሷ ፊት ነው:: ዘመንን በስልት ካልተቀበሉት ስለት ነው:: ዘመንን በጥበብ ካልተዋሃዱት ጥበት ነው:: ጊዜን በእውቀት ካልሄዱበት ድቀት ነው እያልኩ ስብሰለሰል ወሬዋ አደናቀፈኝ::

ልጄ ስታወራ ጣልቃ የማይገባ አባት ነበርኩ:: ያሰኛትን እንድትሆን የበዛ ነጻነት ሰጥቻት ነበር:: ግን ይሄ ሁሉ ልክ እንዳይደለ የገባኝ ዘግይቶ ነው:: ነጻነት በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ቀጣፊ ነው:: ብዙ ነፍሶች የተቀጠፉት በበዛ ነጻነታቸው ነው:: እናም ልጄን እንዲህ አልኳት..

‹በልቤ ውስጥ ዘመን ያላደበዘዛቸው ሁለት ሴቶች አሉ…እናቴና እናትሽ:: አያትሽ እና ሚስቴ:: እንደነዚህ ነፍሶች በአባትሽ እና በባልሽ ልብ ውስጥ መቼም እንዳትረሺ የሕይወት ሕግን እሰጥሻለው:: የመጀመሪያው..እንደእናት አስቢ:: ቀጥሎ እንደ ሚስት በመጨረሻም እንደ ልጅ::

ዝም ብላ ስታደምጠኝ አያታለሁ:: የከፈተችው ቪዲዮ ድምጽ አውጥቶ ሲረብሸን ዘጋችው::

‹እንደ እናት ማሰብ..ሴት ብቻ አለመሆን ነው:: በአእምሮና ልብ መንገስ:: የአንቺ ለሆነው ሁሉ ክብርና ዋጋ መስጠት:: እንደ ሚስት ማሰብ በፍቅር የበረታ ክንድን መፍጠር ነው:: በአንቺ በኩል ወደምድር የሚመጡ ነፍሶች እንዳሉ በማሰብ ከሁሉም ትልቁ ፍቅር በርሽን መክፈት:: እንደ ልጅ ማሰብ ብዙ ነገዎች እንዳሉሽ ተረድተሽ አካሄድሽን ማስተካከል ነው::

‹አሁን ያለችው ኑሃሚን ደስታ አልሰጠችህም? ከልጄ የተነሳ ጥያቄ ነበር::

‹በጣም ስለምወዳት እንድትጎዳብኝ አልፈልግም:: እናም እናትሽና እናቴ በሄዱበት የሴትነት ጎዳና ላይ እንድትራመጂ እሻለው› ክንዴን እያሳየኋት ‹ይሄ ክንድ መቼም አይጥልሽም..እስከፈለግሽው ድረስ አብሮሽ ነው::

‹በጣም ቀላል ከሆነና ሁሉም ሊያደርገው ከሚችል ነገር ራስሽን መከልከል አለብሽ:: በጣም ከባድ ከሆነና ሁሉም ሰው ሊያደርገው ለማይችል ነገር ልብሽን ስጪ›

‹ያ ነገር ምንድነው?

‹የመጀመሪያው ዋጋ ያላት ሴት መሆን ነው:: ሁለተኛው ዋጋ ያላት ሴት ሊያደርጉሽ በሚችሉ ነገሮች ላይ መጠመድ ነው:: ሶስተኛው..አራተኛው..አምስተኛው..ራስሽን መሆን ነው› አልኳት::

‹የአንተ ልጅ ሆኜ ዋጋ የሌላት ሴት የምሆን ይመስልሀል?

‹እሱ ዋስትና አይሆንሽም:: የማንም ልጅ ብትሆኚ አካሄድሽን ካላስተካከልሽ መውደቅሽ አይቀርም:: እንዳትወድቂ ደግሞ የማይጥል ሀሳብና እምነት ያስፈልግሻል:: የማይጥል ሀሳብና እምነት ደግሞ ከቀላል ሳይሆን ከከባድ ተግዳሮት ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: ጊዜሽን ተጠቀሚ..ጊዜ ወዳሻሽ ለመሄድ መረማመጃሽ ነው::

‹ከየት ልጀምር?

‹የማይቻል ከሚመስለው› መለስኩላት::

ጣቷን ከንፈሯ ላይ ጥላ ‹የማይቻል የሚመስል..የማይቻል የሚመስል? አለች::

‹አሁን አንቺ እያደረግሽው ያለው ነገር ሁሉም የሚችለው ቀላል ነገር ነው::

‹ምንድነው እሱ?

‹ድረሺበት› አልኳት:: ሳቅ ብላ ዝም አለች:: የገባት ይመስላል..

‹የሕይወት መብቀያ ልብ ነው:: ሕይወት ያለው ልብ ውስጥ ነው:: የልብሽና የአእምሮሽ ሴት ሁኚ›

‹የልብና የአእምሮ ሴት መሆን ምን አይነት ነው? ስትል ጠየቀችኝ::

‹ሕይወት ሲገባሽ ይገባሻል› መለስኩላት::

‹ሕይወት አልገባኝም?

‹ሕይወት ከጊዜ ነው የሚጀምረው› ብዬ ዝም አልኩኝ:: ድጋሚ እንዳትጠይቂኝ በሚመስል ሁናቴ የፊቴን አቅጣጫ ወደሌላ አዙሬ ተቀመጥኩ:: ዳርዳርታዬ ቢገባት ምኞቴ ነው:: ብዙ ልናገራት አቅም ነበረኝ ግን በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ልሰራት አምኜ ዝግታን መረጥኩ::

አሁን ላለችው ልጄ ሕይወት ማለት ደስታ ብቻ ነው:: ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዳ ሙገሳና አድናቆት ማግኘት ብቻ ነው:: በለበሰችው ልብስና በተጫማችው ጫማ ተከታይ ማፍራት ነው:: ባልተገቡ ፎቶዎች ኮሜንት መሰብሰብ ነው:: አሁን ላለችው ልጄ ሕይወት ማለት ጊዜ እንደሆነ አልገባትም::

………

ወደራሴ ዞርኩ..ወደፍቅር አልባው ራሴ::

ፍቅርን ከልቤ ጽላት ላይ ፍቄዋለው:: መኖር በታከተው፣ ፍቅር በሌለው ልብ ውስጥ ነኝ:: ወደነገ የሚያራምድ አቅምን መጣያ ከዘራ እሻለው:: የሕይወት ትልቁ ባዶነት የኔ ከሚሉት ሰው እቅፍ ውስጥ መራቅ ነው:: ወደተውኩት እቅፍ መመለስን ምርጫ አደረኩ:: ፍቅር ባለበት ሕይወት ውስጥ መኖር ጥያቄ ፈጥሮ አያውቅም:: የጥያቄዎቻችን መጀመሪያ የሕይወት ትርጉም አልባ መምሰል ነው:: እናም እንጠይቃለን..ምንድነኝ..ምንድነን? ስንል::

መጨረሻችን በመጀመሪያችን ውስጥ ነው ያለው:: የነገ ኮቴዎች ከአሁን የሚጀምሩ ናቸው:: እናቴን አይነትና ሚስቴን መሳይ ሴት ከጀልኩ…ባሏ ትቷት ወደኮበለለው ጎረቤቴ ሸፈትኩ::

ከክንዷ ሳርፍ፣ ከጉያዋ ስገባ..መኖርና ሕይወት ይጥሙኝ ይሆናል:: እድሜና ሰው መሆን አልጠገብ ይሉኝ ይሆናል:: ብቻ ከእሷ ልኑር..

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2/2016

Recommended For You