እንደ ሌሎች ሸቀጦችና ምርቶች አቅርቦቱ ዘምኗል፡፡ፊት በትልቅ ጆንያ ብቻ ይገኝ ነበር፤ አሁን ለራሱ በተዘጋጀ መሸጫ ቦታ በትንሽ ጆንያ እና በየሱቁ ደግሞ በፌስታልም ያገኙታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየመንደሩ በመኪና ይቸረቸራል፡ ከሰል፡፡
ተክለሃይማኖት አካባቢ የሚገኝ አንድ ምግብ ቤት የሚሰሩት ወይዘሮ ሰሚራ አብደልቃድርም ከሰል ፍለጋ መሄድ ቀርቷል ይላሉ፡፡የሚሰሩበት ቦታ ድረስ በአይሱዙ ተጭኖ ይመጣላቸዋል፡፡
‹‹በየሳምንቱ በመኪና ሆቴሉ ድረስ ይመጣል።በፊት ብዙ ሄደን ዞረን አሸክመን እናመጣ ነበር››የሚሉት ወይዘሮ ሰሚራ፣ ከሰል እንዲህ መብዛቱ ደን እየተጨፈጨፈ ስለመሆኑ የሚያውቁት እንደሌለ ይገልጻሉ ።
የፉሪ አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ስሜነሽ ተሾመ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ምግብ ለማዘጋጀት የሚመርጡት ከሰል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ወይዘሮ ስሜነሽ ኤግዚቢሽን ማዕከል አካባቢ ምግብ እያዘጋጁ ይሸጣሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይሉ አቅም በቂ አለመሆኑን ተናግረው፣ ለላፉት አራት ዓመታትም በከሰል ሲጠቀሙ ነው የቆዩት፡፡
የጀበና ቡና የሚሸጡት ወይዘሮ ፋጡማ ረዲም በከሰል መጠቀም ለገበያቸው እንደሚረዳቸው ይናገራሉ፡፡‹‹በኤሌክትሪክ ለማዘጋጀት ብናስብ እንኳ ያለው ኃይል ቶሎ ሊያደርስ አይችልም፤ ሰውም በከሰል የፈላ ቡና ይመርጣል››ይላሉ።
በመርካቶ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በከሰል ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ፋሪስ ከማል በፊት ከሰል ከሚሸጥባቸው አካባቢዎች በመሄድ እየገዙ ይሸጡ ነበር። አሁን ግን በመኪና በየመንደሩ እየተዘዋወረ እንደሚሸጥ ጠቅሰው፣በዱቤ ወስ ደው በፌስታልና በማዳበሪያ እንደሚቸረችሩ ይናገራሉ።
በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን የደን ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አብርህት ገብረሕይወት ለከሰል ገበያው መድራት ምክንያቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ በሚፈለገው ልክ አለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ በሠለጠነ መንገድ እንዳይሠራ ኃይል የለም ሲሉ ይገልጻሉ ።
በከተማ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ህብረተሰብ በቀላሉ በትንሽ ገንዘብ ከጉልት ገዝቶ በከሰል እንደሚሰራ፣በህላዊ ለሆነው ቡና አፈላል ወጥ አሠራርም ጋር ከሰልን የሚመርጡ ጥቂት እንዳልሆኑ ያብራራሉ፡፡
‹‹የከሰል ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው ፤አቅራቢው ደግሞ ገበያውን እያየ ያቀርባል›› ያሉት ወይዘሮ አብርህት፣ ከሰሉ ከየት እና ከምን እንደሚከሰል መረጃ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
በአፋር ክልል ‘ፕሮሶፒስ’ የሚባል መጤ እሾሃማ ዝርያ ያለው ዛፍ የአርብቶ አደሮችን መሬት እየወረረ ሌላ ዕፅዋትና ተክል እንዳይበቅል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ዛፉ እንዲጠፋ በሚል ለከሰል እንዲጠቀሙበት እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ትልቁ ስጋት ግን መጤውን ወራሪ ዛፍ ምክንያት አድርገው የግራር ዛፍን እንዳያከስሉ ነው ይላሉ፡፡
ደን በማልማትና መጠበቅ ላይ አንዱ ትልቁ ችግር ክልሎች በተፈለገው መልኩ ይቆጣጠራሉ ወይ የሚለው እንደሆነም ጠቅሰው፣ ከመዋቅር ጋር በተያያዘ በክልል ደረጃ የባለቤትነት ችግር እንደሚኖርም ያመለክታሉ።ይህን ክፍተት በመጠቀም ነጋዴ ወደ ዛፍ መቁረጥና ማክሰል ሊገባ እንደሚችልም ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለህብረተሰቡ በማስተማር ከሰል ማክሰሉ እንዲቀንስ ማድረግ ይገባል። ከሰልን በባህላዊ መልኩ ከማክሰል ይልቅ ኢነርጂው በማይባክን ሁኔታ ውጤታማ በሆነ መንገድ አካባቢ በማይበክል ሁኔታ አክስለው መጠቀም እንዲችሉ አንድ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ ነው።
ዳይሬክተሯ የተፈጥሮ ደኖች እንዳይቆረጡ፣ ለከሰል አገልግሎት እንዳይውሉ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ፣የሰው ሠራሽ ደኖች በማልማት ማከሰል እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡
በደን ሳይንስ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውና በአሳታፊ የደን አስተዳደር ላይ የሚሰሩት ዶክተር ሙሉጌታ ልመንህ፣ የኢትዮዽያ የደን ሀብት እየተመናመነ ለመምጣቱ ፣ለአፈር መሸርሸርና ለበረሃማነት መስፋፋት አንዱ ምክንያት ከሰልና የማገዶ እንጨት ያለ ቁጥጥር መመረቱ ነው ይላሉ።
በሀገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ደኑን ለመጨፍጨር ሊያጋልጠው እንደሚችል ተናግረው፣ አሁን የከሰል ምርት በስፋት ወደ ከተማ እየገባ ያለውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ኬላዎች ላይ ያለው ቁጥጥር መላላት አንዱ የችግሩ መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም ነው ዶክተር ሙሉጌታ የሚናገሩት፡፡ በዚህ በኩል ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የተሠራው ጥቂት ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ህዝቡ የደን ሀብቱን እንደ ከብቶቹና እርሻዎቹ እንዲንከባከብ አለመ ደረጉንም እንደ ትልቅ ፈተና እንደሚቆጥሩት ያብራራሉ።
‹‹የማገዶ እንጨትና የከሰል ምርቶች አይኑሩ ማለት አዳጋች ነው።›› የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፣ ዛፍ ራሱን የሚያድስ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ችግኙን ስንተክለው ይበቅላል፤ የደረሰውን ብንቆርጠው ተክለን ዛፍ እናደርሳለን። ቀድሞ የሚወጣውን የደን ውጤት ማግኘት አለብን፤ ደኑን ማልማት መቻል ግን ሁል ጊዜ መታሰብ አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በደን መመንጠር የሚመጣ አማቂ ጋዝ ፕሮጀክት ;ሬድ ፕላስ/ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገሪቱ በየዓመቱ ወደ 92ሺ ሄክታር የሚሆን ደን ማጣቷን ይገልጻሉ፡፡
የኬላዎች መነሳት፣ የሕግ ማስጠበቅ አቅማችን ከተቋማት ጀምሮ ከአቅምና ዕውቀት ጋር ተያይዞ በሚፈለገው ልክ አለመሆን ለከሰል በስፋት ገበያ ላይ መውጣት በምክንያትነት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ያመለክታሉ፡፡
‹‹የኬላዎች ሥራ የላላ ይመስለኛል፤›› ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ በአሁኑ ወቅት በጎጃም በደን አልሚዎች ከሰል እንደሚመረት ይናገራሉ፡ ፡ የተፈጥሮ ደን እየጨፈጨፉ የሚያከስሉ እንዳሉም ጠቅሰው፣ ‹‹የተፈጥሮ ደን የሁላችንም ስለሆነ መነካት የለበትም። አልሚዎች ግን እንደ ባህር ዛፍ ያሉትን ማክሰል ይችላሉ›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹የፈረንጅ ግራር እያለሙ የሚያከስሉት ቢጠቀሙ ችግር የለውም። ከሰሉ ቀጠን ቀጠን ያለና ረጃጅም ከሆነ የአልሚዎች ነው።››ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ የፈረንጅ ዛፎችን እየተከሉ የሚያከስሉ ሊበረታቱ እንደሚገባም ነው የሚናገሩት፡፡የተፈጥሮ ደኑን ግራሩን እየቆረጡ በማክሰል በሚሸጡ ላይ ክትትልና ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ
ፎቶ ከኢንተርኔት