በሙዚቃ በደመቀው ግቢ የኢንቨስትመንት ተቋማት ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፤ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የከተሞች የኢንቨስትመንት ቢሮዎችም የኤግዚ ቢሽኑ ታዳሚዎች ናቸው፡፡ ምርትና አገልግሎት ማስተዋወቅ እና ባለሀብቶችን ማማለልም ከኢግዚቢሽኑ ዓላማዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡
ለአንድ ሳምንት የሚካሄደውን የኢንቨስ ትመንት ሳምንት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል በቀረበው ኢግዚቢሽን ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የናዲ ፕላስቲክ ከረጢቶች ማምረቻ ፋብሪካ የፋይናንስ ሰራተኛ አቶ አደፍርስ ለገሰ እንደሚሉት ፤ በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ የፕላስቲክ ውጤቶችን ያመርታል፡፡
ፋብሪካው 12 ማሽኖችን ይዞ ነው በ2007 ወደ ስራ የገባው፡፡ ወደ ስራ እንደገባ በቀን 14 ሺ ከረጢቶችን ያመርት የነበረው ፋብሪካው ፣ አሁን የማሽኖቹን ቁጥር ወደ 30 በማሳደግ በቀን የሚያመርተውንም እስከ 50 ሺ ማድረስ ችሏል፡፡ የሰራተኞቹን ብዛት ስራ ሲጀምር ከነበረበት 45 አሁን 120 ማድረስ ችሏል፡፡
በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ጊዜያዊ ችግር ነው፤ ያን ያህል ስራችንን የሚያ ደናቅፍ አልነበረም ያሉት አቶ አደፍርስ፣ ስራቸውን ለመስራት እንዳልተቸገሩ ይና ገራሉ። ‹‹የኛ ችግር ዶላር አለማግኘት ነበር ፤እሱንም ልማት ባንክ ባደረግልን ትብብር ጥሬ እቃዎችን አስገብተን እየሰራን ነው፤ይህን ችግር በቀጣይም መንግስት በዘላቂነት ሊፈታ ይገባዋልም፡፡ ››ይላሉ፡፡
አቶ አደፍርስ አዳዲስ ባለሀብቶች አሁንም በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ምክር እየጠ የቋቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ በሚገባ እንደሚያስተናግዳቸው ገልጾ እንዳሻ ቸውም ይናገራሉ፡፡
በሀዋሳ የሚገኘው የአልሚ የወተትና ወተት ማቀነባበሪያ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ታፈስ ድርጅቱ ወተት ያቀነባብራል፤ የዴይሬ ኢንስቲትዩትም አለው ይላሉ፡፡ አቶ አስማማው የፈጠራ ባለሙያም ናቸው፡፡ የወተት ማቀነባበሪያውንና የአረቄ ማውጫ ማሽንም ራሳቸው መስራታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የወተት ማቀነባበሩን ስራ የጀመሩት ጥሬ ወተት በመሰብሰብ ሲሆን በጥቃቅንና አነስተኛ በከተማ አስተዳደሩ በ1997 ዓ/ም ታቅፈው ነው፡፡ ‹‹በ7 ሺ ብር ካፒታል የተነሳው ማቀነባበሪያ፣ አሁን ካፒታሉን ወደ 22 ሚሊየን ብር አድርሷል፤ በቀን እስከ 20 ሺ ሊትር ማቀነባበር የሚችል ዘመናዊ ማሽንና ወደ 78 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉን፡፡›› የሚሉት አቶ አስማማው፣ በከተማዋ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት በኢንቨ ስትመንታቸው ላይ ያሳደረው ጫና እንዳልነበረ ይገልጻሉ። ‹‹ወተት የምናገኘው ከኦሮሚያና ደቡብ አካባቢዎች ነው። ሁሌም ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሂደት ያጋጠመን ችግር የለም፡፡ በአካባቢውም ሆነ ሌሎች ከተሞች ላይ የተፈጠረው ችግር በኢንቨስትመንታችን ላይ ያደረሰው ችግር ግን የለም ይላሉ፡፡ በአዳዲስ ባለሀብቶች ላይ መጓተት ሊኖር ይችላል፡፡ ያን ያህል ግን ከባድ ችግር አይደለም።
ይህን አይነት ፎረሞች በጣም ያስፈ ልጋሉ። ኢንቨስትመንቱ ወደፊት እንዲራመድ እና ኢንቨስተሮች እንዲተሳሰሩ ያስች ላል። ባለሀብቶች ሲተሳሰሩ አክሲዮንን ያስባሉ፤ ከተሞች ያድጋሉ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ ሲሉም ያብራራሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ሳምንቱ በጣም ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰው፣‹‹እኛ በከተሞች ፎረሞች ብዙ ጊዜ ተሳትፈናል፡፡ ተሳትፏችንም እያደገም ነው፡፡››ይላሉ፡፡
የኢንቨስትመንት ሳምንቱ ኢንቨስትመንቱን እንደሚያነቃቃና ተጠናክሮ መቀጠል እንደ ሚኖርበት ጠቅሰው፣ አመራሮቹ ባለሀብቱ የሚያ ቀርበውን ጥያቄ ወዲያው በመመለስ ማስተናገድ አለባቸው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ቢሮ የጥናትና ፕሮሞሽን ኬዝ ቲም አስተባባሪ አበራ መንግስቱ ድሬዳዋ እንደ ሌሎች ከተሞች ብዙም አለመረጋጋት እንዳልገጠማት ተናግረው፣ በዚያ ችግር ውስጥ ነበረች ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ፡፡
ባለሀብቶች አስተማማኝ ሰላም ስለሚፈልጉ ብቻ ትንሽ መቀዛቀዝ መታየቱን ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ የበለጠ ጥሩ ሁኔታ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢንቨስትመንቱ ይበልጥ ተቀዛቅዞ የነበረው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡ ያም አለመረጋጋቱ ያመጣው ነው ይላሉ፡፡
ለውጡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር እያረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁንም ይገል ጻሉ፡፡ ባለሀብቱ ወደ ፓርኩ ለመግባት አሰፍስፎ እየጠበቀ መሆኑን በማብራራት፡፡ ‹‹እኛም እንደ አስተዳደር ወደ 65 ሄክታር መሬት በነባሩ ላይ ጨምረን መሰረተ ልማት አሟልተን ባለሀብቱን እየጠበቅን ነው ሲሉም ዝግጅቱን ይገልጻሉ፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ከንቲባው ህብረተሰቡ ዘንድ ወርዶ እየሰራ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ሰላሙን ይጠብቃል፡፡ ብጥብጥ ይፈጥራሉ ተብለው የሚታሰቡትን ሰዎች ለይቶ ያውቃል፡፡ ያ ማለት ኢንቨስተመንቱንም ይጠብቃል፤ አንድ ባለሀብት እቃ ቢበላሽበት የሚጎዳው እሱ ብቻ አይደለም፤ ባለሀብቱ እና አስተዳደሩ ብቻ አይደሉም የሚጎዱት ሰራተኛውም ነው፤በዚህ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው፡፡‹››ይላሉ
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ገለታው ገረመው አንደ ሀገር በአንዳንድ ከተሞች የጸጥታ መደፍረስ አጋጥሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ መንግስት በጸጥታው ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ወደ መረጋጋት እየሄድን ነው የሚሉት አቶ ገለታው፡ የጸጥታ መደፍረሱ ዋነኛ ችግርም አንዳንድ ግለሰቦች ለውጡ ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ይገልጻሉ። እንደ ከተማ አስተዳደር ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እና እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች ሲሉም ነው ያመለከቱት፡፡ ለዚህ ማሳያውም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከአምናው የዘንድሮው በእጥፍ ጨምሮ መገኘቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆናቸውን ያብራራሉ ፡፡
አንዳንድ ወገኖች በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስራጩት ወሬ ከተማዋን የማይገልጹ የሀሰት ወሬዎች ናቸው ያሉት አቶ ገለታው፣ ከተማዋ አሁንም የሰላምና የፍቅር ከተማ ሆና ቀጥላለች። ይህን በአካል ተገኝቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡በእዚያ ያለ ነዋሪንም አነጋግሮ መረዳት ይቻላል፡፡››ይላሉ፡፡
ከተማዋን ለማሳደግ ካለን ጽኑ ፍላጎት በመነጨ በኢግዚቢሽኑ በስፋት መጥተናል ያሉት አቶ ገለታው፣ ከሆቴል ከግብርና ከማኑ ፋክቸሪንግ ዘርፎች የተውጣጡ ባለሀብቶች በፎረሙ መገኘታቸውን ያብራራሉ፡፡‹‹ሊጎበኝ የሚመጣውን አካል ያሉን አማራጮች በማሳየት ተሻምተን እንወስዳለን፡፡ይሄው ነው ዋና አላማችን ፡፡›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል