ከዋጋ ግሽበቱ እንዴት ይወጣ?
ባለፈው ሚያዝያ ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱ እና ይህም በኢኮኖሚክስ ሲታይ ግሽበቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይገለጻል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ችግሩን ለመፍታት የግብይት ትስስሩ እንዲስተካከል እና አቅርቦት ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ እን ዲሁም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላምን በጠ በቀና ህዝብን ባከበረ መንገድ ሊከናወን ይገ ባል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል፣የዋጋ ግሸበት ሲባል አጠቃላይ የፍጆታም ሆነ በሁሉም እቃዎች ላይ በተከታታይ የሚታይ የዋጋ ጭማሪ ማለት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ለዋጋ ግሽበቱ ማሻቀብ በምክንያትነት የሚጠቀሱት በጥቅሉ ሁለት ጉዳዮች እንደሆኑ ተናግረው፤የመጀመሪያው በሁ ሉም ዘንድ የሚታወቅ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሽከረከረው የገንዘብ መጠንና ፍጥነት መጨመር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ይህ ደግሞ አጠቃላይ የአገሪቱን የፍጆታ እቃ ፍላጎት ስለሚጨምርና አቅርቦት ደግሞ ያንን የማይከተል ከሆነ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከተል መቻሉን ያመለክታሉ፡፡ ይህን ችግር ፈጥኖ የገንዘብ መጠንን በመቆጣጠር መቀነስ እንደሚቻል በሳይንስ ላይ የተደገፈ መላ ምት እንዳለና ይህን ለመዋጋት ምርትና አቅርቦትን መጨመር እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ፡፡
ሁለተኛውና እርሳቸው ከኢትዮጵያ ጋር ይዛመዳል ብለው የሚያምኑት የኢኮ ኖሚውን መዋቅር ነው፡፡ይህም የአመራረት ዘይቤን የሚያሳይ ሲሆን፣መዋቅር ሲባል ግን ከኢኮ ኖሚው የመዋቅር ሽግግር ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ የፍጆታ አወቃቀርን የሚመለከት ነው ይላሉ፡፡
‹‹የፍጆታ አጠቃቀማችን እንጀራና ከእርሱ ጋር የሚሄዱ ማባያዎች ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነው፡፡በተለይ ዝቀተኛ የደመወዝ ተከፋይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በአማካይ የሚጠቀሙባቸው እቃዎች ላይ የሚታይ የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የአኗኗር ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቀር አይደለም፤የግድ የባህሪ ለውጥ ማምጣትን ይጠይቃል›› ይላሉ፡፡
የካናዳ ክርስትያን ህፃናት ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተርና የኦሮሚያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ፕሬዚዳንት ዶክተር ጉታ ቴሶ ፤ለግሽበቱ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚ ችሉት ባለፈው አንድና ሁለት ዓመታት ውስጥ የነበረው የአገር አለመረጋጋት፣ ንግዱ እንደተፈለገው አለመሳለጥ፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በጣም አለማደግ መሆናቸውን ያብ ራራሉ ፡፡
ዶክተር ጉቱ እንደሚሉት፤አገሪቱ በርካታ መገልገያዎችን ከውጭ ታስገባለች፡፡ለዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በማነሱ ግብዓቶቹ በሚፈለገው ጊዜ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋል። ይህም የግብዓት ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል። የግብዓት ዋጋ ሲጨምር የምርቱም ዋጋ ይጨምራል፡፡ከዚህ የተነሳ የገበያ ሰንሰለቱ ይንዛዛል፡፡ይህ ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምርት ዋጋ እንዲንር ያደርገዋል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት የተስተጓጎለበት ሁኔታ እንደነበርም ዶክተር ጉቱ በመጥቀስ ፣ ምርት እና ከውጭ የሚገባ ግብዓትን የማጓጓዙ ስራ በመንገድ መዘጋት ይሁን በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሲስተጓጎል እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮች ምርት የተፈለገውን ያህል እንዳይመረት፣የተመረተው በትክክል በጊዜው እንዳይሰበሰብ፣የተሰበሰበው ደግሞ በሚፈለገው ፍጥነት ወደሚፈለግባቸው ቦታዎች እንዳይጓጓዝ ያደረጉበት ሁኔታም እንዳለ ይጠቁማሉ። ለዚህም በምዕራብ ኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ያሉ አርሶአደሮች ምርታቸውን ለመሰብሰብ ያልቻሉበትን በአብነት ያነሳሉ፡፡
‹‹አንድ ሁለት ሶስት ቀን የገበያና የትራን ስፖርት መስተጓጉል ሲከሰት ነገሮች በነበሩበት አይቆዩም፡፡ይህም በዋጋ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም። የግብይት ስርዓቱ ከተናጋ በርካታ ጉዳዮችን ነው የሚያበላሽው፡ ፡ይህ ሁሉ ሁኔታ ተደምሮም ነው የዋጋ ንረቱ እንዲያሻቅብ ያደረገው››ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ ከአምራች እስከ ተቀባዩ ድረስ ያለው የገበያ ትስስር በጣም ኋላ ቀር፣አምራቹንና ተጠቃ ሚውን የማያገናኝ፣ አምራቹን የማይጠቅም፣ ተጠቃ ሚውንም ቢሆን የሚጎዳ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር አጥናፉ፣በዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት አገናኞች መሆናቸውን ይገልጻሉ። አገናኞች የሚባሉት የፖለቲካ ሰዎችንም የሚያካትት ነው››ይላሉ፡፡
ማህበረሰቡ ይህን አይነቱን ሂደት ለማፍረስ የተደራጀ አለመሆኑን፣አቀባባዮች ግን በደንብ መደራጀታቸውን በመጥቀስ፣ የተደራጁት ዋጋ የመቆጣጠር ኃይል አላቸው ይላሉ፡፡
ዶክተር አጥናፉ፣‹‹በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ አዲስ አለመሆኑን ጠቅሰው፣‹‹እንዲያውም ኢትዮጵያውያን የተረ ጋጋን በመሆናችን ነው እንጂ በሌሎች አገሮች እንደኛ አይነት የፖለቲካ ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ ለሶስትና ለአራት ወራት ያህል ሁሉ ደመወዝ የማይከፈልበት ጊዜ አለ፡፡ በአገራችን ግን ይህ አልሆነም፡፡ በመደበኛ ህይወታችን እየኖረን ነው ያለነው››ብለዋል ፡፡
ዶክተር ጉቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ሰላምን በጠበቀና ህዝብን ባከበረ መንገድ ማካሄድ፣መንግስት ሰላም የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በሚገባ መወጣት ከመፍትሄዎቹ መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ መንግስት የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታትቶ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚኖርበት፣ መጪውን የግብርና ወቅት በሁሉም አካባቢዎች ግብዓትን በማቅረብ ስራው ቀና እንዲሆን መስራትም ከመንግስት እንደሚጠበቅ ይጠ ቁማሉ፡፡
‹‹የግብይት ትስስሩን ማስተካከል ያስፈል ጋል›› የሚሉት ዶክተር አጥናፉ፣ይህንንም የስዊዲን ተሞክሮ በመጥቀስም ያብራራሉ፡፡ በስዊድን የፍጆታ እቃዎች ተጠቃሚ ማህበር መኖሩን፣አራት አምስት ዓመት ድረስ የዶሮ ስጋ ዋጋ አንድ ተመሳሳይ መሆኑን ያብራራሉ፡፡በእኛ አገር በፍላጎታቸው የተደራጁ ተጠቃሚዎች ዋጋ ሲጨመር ለምን ብለው እንደማይጠይቁም ነው የሚናገሩት፡፡ ማህበረሰቡ የፍጆታ ባህሪውን መለወጥ መቻል እንዳለበት፣ የድንች ዋጋ ሲጨምር ወደ ሌላው ተቀራራቢ ምርት ፊቱን ማዞር እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ፡፡
ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ዋና መፍትሄ ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል አምራቾቹ ላይ የሚጣል ታክስ ለጊዜው መቀነስ አንዱ መሆኑን ዶክተር አጥናፉ ጠቁመው፣ይህም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚጠቀመውን እቃ የሚያመርቱና የሚያቀርቡ ባለድርሻዎችን የሚመለከት መሆን እንዳለበት ያመለከታሉ፡፡ እርምጃው የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡት ጭምር መልካም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በቅርቡ የመስሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚከስ አሳሳቢ የሚባል እና መንግስትም ወደ ነጠላ አሀዝ ለማውረድ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ግሽበቱን ለማውረድ የመንግስትን ወጪ በመቀነስ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ ዶክተር አጥናፉ የገንዘብ መጠንን መቆጣጠር ሲሉ የገለጹት እየተሰራበት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አቶ አህመድ እንዳሉት፤የሞኒተሪና የፊሲካል ፓሊሲ እየተመጋገበ እንዲሄድ እየተደረገ ነው ። የመንግስት የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ እንዳይበልጥ እየተሰራ ነው፡፡
በሞኒተሪ ፖሊሲም የገንዘብ አቅርቦት የብድር አቅርቦት ከሚፈለገው የነጠላ አሀዝ አላማ አንጻር እየተቃኘ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ፍላጎት ላይ በማቀብ ከሚደረገው በተጨማሪ ምርታማነት ላይ በጣም መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤በተለይ የግብርና ምርቶችን ማሳደግ ላይ በስፋት መሰራት ይኖር በታል። በቆላማው አካባቢ አነስተኛ የመስኖ ስራዎችን በማከናወን እንዲሁም በቀጣይ አመት ወደ 20 ቢሊየን ብር በመያዝ ለመስኖ የሚመደበውን በጀት በማሳደግ በተለይ ከውጪ የሚመጣው ስንዴ በሀገር ውስጥ የሚተካበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ ነው፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዞር፣ ከፍተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣የግሉን ዘርፍ ምርታ ማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል፣የስራ እድል ማሳደግ የሚሉትም ሌሎች እርምጃዎች ናቸው፡ ፡
በተያዘው በጀት አመቱ የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሀዝ ማውረድ ቢታቀድም፣ በዘጠኝ ወሩ መጨረሻ ግሽበቱ ወደ 12 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ 11 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል፡፡
ዶክተር ጉቱ የህዝቡ 90 በመቶ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ ህይወቱ የተመሰረተው ግብርና ምርት መሆኑን በመጥቀስ አርሶ አደሩ አንዲት ስንዝር መሬት ሳትባክን ማረስ መቻል አለበት ይላሉ፡፡ ዶክተር ጉቱ ይህን ምርት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻልና የዋጋ ግሽበቱ እንደሚረጋጋ እምነቱ አላቸው፡፡
ዶክተር አጥናፉ፣አቅራቢዎች፣ ጥቅማቸው መቀጠል የሚችለው ደስተኛና የተረጋጋ ማህበረሰብ ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው፣ የዋጋ ጭማሪ ማህበረሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዳይኖር እንደሚያደርግ የተሸከመው ገንዘብ የመግዛት አቅም እንዳይኖረው እና ጎዳና ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ጉዳዩ የሞት ሽረት ነው የሚሉት ዶክተር አጥናፉ፣ በዳቦ ዋጋ መጨመር እንደተነሳው የሱዳኑ ነገር እንዳይገጥም መጠንቀቅ ይገባል ይላሉ፡፡ ይህ ከሆነ አቅራቢውም፣ ተጠቃ ሚውም፣ መንግስትም ማትረፍ አይችሉም፡፡ አምራቹም ሰራተኛ ያባርራል፤ ፋብሪካ ይዘጋል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩ የጋራ ነው፤መከተል ያለብን ፍልስፍና አንዱ ለሁሉም፤ሁሉም ደግሞ ለአንድ ሰው መሆን አለበት የሚል መሆን አለበት››ይላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
አስቴር ኤልያስ