ድሮ ድሮ እኛ ተማሪዎች ሳለን ልክ በዛሬዋ ቀን (ሰኞ ሰኞ) የምንከውናት አንዲት ልምድ ነበረችን። የሰልፍ እና ብሄራዊ መዝሙር ስነ-ስርዓትን አጠናቀን፤ ከመማሪያ ክፍላችን እንደገባን ሁላችንም እጆቻችንን ከጠረጴዛው ላይ እንዘረጋለን። መምህራችን አሊያም የክፍል አለቃችን ደግሞ አንድ በአንድ እየዞሩ ይመለከቱናል። በዛሬ ተማሪዎች ዘንድ ይህ ልማድ ስለመኖሩ አላውቅም። በእኛ ጊዜ ግን ይህ የሚደረገው የሳምንቱ በኩር በሆነችው ሰኞ ሁሉም ተማሪ ንጽህናውን በተገቢ መንገድ መጠበቅ አለመጠበቁን ለማረጋገጥ ነበር።
የደንብ ልብስ በስርዓት ታጥቦ መለበሱ፣ ጥፍር መከርከሙ፣ የወንድ ጸጉር መበጠሩ፣ የሴቷም በአግባቡ መጎንጎኑ፣ … ሁሉ ይታይ ነበር። ይህንን አጉድሎ የተገኘም ቅጣት ይጠብቀዋል። ይህ ልማድም አንድም ህጻናት ስለ ንጽህና አውቀው በመተግበር ጤናቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል። ሁለትም ከሰኞ ማለዳ በዚህ መልክ የተጀመረ ሳምንት በንቃትና በጥሩ መንፈስ እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችላል። ከሁሉ በላይ ግን ታዳጊዎች ስነ-ስርዓት እንዲማሩና እንዲያውቁ ለማድረግ ያስችላል።
ይህንን ሰዋዊ ልምድ ለከተሞች ብናደርገው ብለን ብናስብስ? እኛ ራሳችንን ፈታሽ አድርገን እንሰይም፤ ከዚያም በሃገራችን የሚገኙ ትልልቅ ከተሞችን ንጽህና በዓይነ ህሊናችን እንፈትሽ። የእናንተን ባለውቅም፤ በእኔ እይታ ግን ንጽህናዋን ባለመጠበቅ፤ ቁንጥጫ፣ አለንጋ አሊያም መንበርከክ የሚከተላት ከተማ መዲናችን አዲስ አበባን ትመስለኛለች። ለምን ቢሉ፤ በነዋሪዎቿ ስርዓት አልባነት ከስሟ በተቃራኒ የምትቆም ንጽህና አልባ ከተማ በመሆኗ ነዋ። መቼም ከትልልቅ መንገዶች እስከ መንደሮች ብናካልል ግማሽ አካሏ ጽዱ ነው የማለት ድፍረት አናገኝም። ስልጣኔዋም በህንጻዎች ይለካ ይሆናል እንጂ በውበት ልትነሳ አትችልም።
እስኪ ለጥቂት ደቂቃዎች በመንገድ ላይ ያለን አካባቢያችንን እናስተውል፤ ከመንገድ ያልወጣንም የምንገኝበትና የምንኖርባቸው አካባቢዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን እናስብ። ሰውን ከእንስሳ ያልለዩ መንገዶችና ትርምስ፣ ፈሳሽን ከጠጣር መለየት ተስኗቸው መንገዳቸውን የሳቱ ቦዮችና የፍሳሽ መውረጃዎች፣ እንደ ህጻናቱ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ምኑንም ምኑንም ለጣጥፈው የተዘበራረቁ ህንጻዎች፣ ጥቁረታቸው የውሃነታቸውን አሻራ ያጠፋና የሚረጩት ሽታም የሚተነፍግ ወንዞች፣ ከወዲያ የመኪና ጡሩንባ፣ ከወዲህ የሰው ሁካታ፣ አለፍ ብሎም የሙዚቃና የማሽኖች ጩኸት አቅሏን ያሳቷት፣ ሰዎቿ የቱ ነውር የትኛው ስርዓት መሆኑን ዘንግተው በየጥጋጥጉ የሚጸዳዱ፣ … ከሆኑ ውለው አድረዋል።
በልጅነታችን የተማርናቸው ስርዓቶች የት እንደገቡ እንጃ፤ አሁን ሁሉም ነገር ስርዓት አልባ ሆኗል። ከቤታችን የሚወጡት ውጋጆችን አውጥተን ከደጃችን እናከማቻለን(ደግሞ እኮ በዚያ ስናልፍ አፍንጫችንን ሸፍነን ነው!)፣ በተሽከርካሪ ስንጓዝም በኩራት መስኮት ከፍተን ወዲያ እያሽቀነጠርን ነው፣ ከየቤታችን የሚወጡትን ፍሳሾችም ከቦዮችና ወንዞች እናያይዛለን፣…። እኔን የሚገርመኝ እንዲህ በማድረጋችን የምናሳየው ኩራት ነው። ከመንገድ ዳር ያውም በርካታ ወጪ ወራጅ ባለበት ተጸዳድቶ እጁን ኪሱ ከቶ እያፏጨ መንገዱን የሚቀጥል ስንት ኩሩ አለ መሰላችሁ።
እንዳይሸታት አፍንጫዋን በደማከሴ ዘግታ ያለ አንዳች እፍረት ቆሻሻ የምትደፋ ስንቷ መሰለቻችሁ። መንገዱን እየጠረጉ አቧራና ሌላውን ደረቅ ውጋጅ በጋሪ ጭነው ከቦይ የሚገለብጡ የመንገድ ጽዳትባለሙያዎችም አሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሰው የገነቡትን ፋብሪካ ተረፈ ምርት (ዕዳ) በወንዞች ላይ የጣሉም ጥቂት አይደሉም። የሚሰራውንና የሚሆነውን ህገወጥነት እየተመለከቱ እንዳላየ የሚያልፉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እና ተቋማት በመኖራቸውም ነው ከዚህ የደረስነው። አዲስ አበባን ከሌላው ልዩ የሚያደርጋት ሌላም ባህሪ አላት።
የመንገዱ ግርግር፣ ሽታ እና አቧራ «ሰለቸኝ» ብለው ጥቂት ወደላይ ከፍ ካሉ ሌላ የባሰ ነገር መመልከትዎ አይቀርም። ጣሪያዎች የእቃ ማጎሪያና የዝገት መለያ ናቸው። የተገለገልንበትን ዕቃ በአግባቡ ማስወገድ መቼም አይሆንልንም፤ ብረታ ብረት፣ አሮጌ የቤት ዕቃዎች፣ ጨርቃ ጨርቅና ፕላስቲኮች፣… ሌላም ሌላም መመልከታችሁ አይቀርም። ደግሞ እኮ አናምንም፤ የዚህ ስርዓት አልበኝነት ምክንያትም ሰለባም እኛ ሆነን ሳለን ሌላ አካል እንደፈጠረው ሁሉ እንማርራለን።
ነጋራ ሳያሻን ማከናወን ቢገባንም «አጽዱ» ስንባል «ምን አግብቶኝ» በሚል እንደነፋለን። በነጻነት የመጓዝ መብታችን ከመገደቡም ውጪ ለተለያዩ በሽታዎች ስለመዳረጋችን ዘንግተናል። እንዲህ ባለ አካባቢ የምንሰራው ስራም በነጻ አእምሮ የታገዘ ስላለመሆኑም ማስተዋል ተስኖናል። ወገን፤ አካባቢያችን የእኛነታችን መገለጫ ነው። በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ገንቢያችን የመሆናቸውን ያህል ስርዓት አልባ ሲሆን ደግሞ ያፈርሰናል። ቤታችን ጽዱ እንዲሆን የምንጥረውን ያህል፤ አካባቢያችንም ቢጸዳ ጥቅሙ ለራሳችን ነው። እኛ አካባቢያችንን ከመሰልንም፤ አካባቢያችን «ይጽዳ፤ እናጽዳ» ሳይሆን «እንጽዳ» ብለን ብንነሳ መልካም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ብርሃን ፈይሳ