ሰላም ሰዎች! ሁሉ አማን ነው? ጽዳትስ እንዴት ይዞናል? ከስንት ዓመት በፊት እንደሆነ አስታውስበት አቅም የለኝም እንጂ ድምጻዊና ባለክራሩ ጋሽ አበራ ሞላ /ስለሺ ደምሴ/ አዲስ አበባን አዲስና ንጹህ ገጽታ እንድታገኝ በብዙ ሠርቷል። ያኔ ታድያ ባለው ኃይል፣ በነበረው አቅምና ደረጃ ሁሉም አካባቢውን እያስዋበ፣ ዙሪያውን እየጠበቀ ቆየ።
እንደውም ያኔ ከተሠሩ ሥራዎች ብዙዎቹ አሻራቸው ዛሬም ድረስ አለ። ግን የእኛ ነገር! ጉዳያችን ሁሉ በትኩስ በትኩስ ነው የሚሰምረው መሰል፤ ከጊዜያት በኋላ እርግፍ አድርገን ተውነው። እንደውም ሳይብስብን ቀረ ብላችሁ ነው? ቆሻሻችን ጨመረ፤ በዛ ተባዛ፤ ከተማዋን አጥለቀለቃት።
በእርግጥ እውነት ነው፤ የጠጣነው ውሃ ሥራውን ጨርሶና አጣጠቦን አሳቻ መንገድ ላይ ሆነን ሳለ አስወጡኝ ቢል መጸዳጃ ቦታ አልነበረም። በእጃችን የተገኘ አንዳች ቆሻሻን እንጣለው ብንል መጣያ በቀላል አይገኝም ነበር። ይሁንና ይህም ተመቻችቶ ሲገኝ በየት በኩል? ከቆሻሻ መጣያዎች ይልቅ አስፋልቱ የተሻለ የመቀበል አቅም አሳይቷል አልያም ለራሳችን ሥራ መፍጠር ቢያቅተን ለሰዎች ሥራ እየፈጠርን ነው መሰለኝ በየመንገዱ ቆሻሻችን አለ።
እንደው ግን በሞቴ አስቡት! ቆሻሻን ለመጠየፍ ስልጣኔና እውቀት ያስፈልጋል? በየመንገዱ በግዴለሽነትና በቸልተኝነት ቆሻሻን በየዕለት በሚንቀሳቀሱበት መንገድ ላይ ላለመጣል ትምህርት ይጠየቃል? የምንገርመውኮ ለጉድ ነው! ልንገራችሁ! በሥራ አጋጣሚ ወደተለያዩ ክፍላተ አገራት የመንቀሳቀስ እድሉ ገጥሞኛል። ታድያ በተሳፈርንበት መኪና መስኮት ንጹህ አየር እንዲገባ መስኮቱን የሚከፍቱ ተጓዦች በዛው መስኮት ቆሻሻቸውን አውጥተው ሲጥሉ አያለሁ።
እንዴት እንደሚጨንቅ! ሳልናገር የቀረሁ አይምሰላችሁ። እውነቴን ነው! ግን ከጨዋ ተቆጠርኩ፤ ምንም ከማያውቅ ሰው ተራ ተመደብኩ። «እንዴ መኪናው ይቆሽሻላ!» አሉኝ። መቼም ሰዎቹ ህጻናት አይደሉ! ቆንጠጥ ተደርገው ወይ በቁጣ «አገርስ አይቆሽሽም? ያውም ባዕድ ነገር ከማያውቅ የአርሶ አደር መሬት ላይ ይህ ይጣላል? ነውር አይደለ?» ተብሎ አይነገራቸው። ለ’ትልቅ ሰው’ መንገር አስቸጋሪ ነው።
ወይ ጉድ! ነገሬ እንኳ ከዚህ ሳይሆን ከጊዜያት በፊት ስለተጀመረው የጽዳት እንቅስቃሴ ነው። ከዛ ደግሞ ተነሳሽነትን ለመፍጠር መጥረጊያ ይዘው ስለሚያጸዱ አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች። ይህን ሳስብ ነው እንግዲህ «መጥረጊያ ለቆሸሹት እንጂ ለጽዱዎች አይደለም» ያልኩት። መቼም «እንትን ሰፈርን አድርገኝ» አይባልም እንጂ፤ ቢባል ኖሮ ጽዳታቸው እጅግ የሚያስቀና እና የሚመኟቸው ጽዱ አካባቢዎች በከተማችን አሉ። እነዚህ አካባቢዎች በረንዳም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ የባለኮከብ ሆቴሎች በረንዳ።
ባለፈው ይኸው የጽዳት ንቅናቄ የተጀመረ ጊዜ እነዚህ ጽዱ ቦታዎች ላይ ግዙፍና አዳዲስ መጥረጊያዎችን የያዙ የተቋማት ኃላፊዎችን ባለፈው አይቼ ሳቅሁ። ከልባቸው ምሳሌ ለመሆን ነው ወይስ «ሙድ» እየያዙብን ነው? እንደው መቼስ ብዙ ክምር ቆሻሻ ካለበት ቦታ ይሂዱ ማለቴ አይደለም። በእርግጥ የእኛ ሰው ቆሻሻ የማይጥለው የገዛ ቤቱ ውስጥ ብቻ ነው። በእነዚህ ጽዱ በሚመስሉ ቦታዎች አልፎ አልፎ የውሃ ኮዳ አይጠፋም። እሱማ የዛፍ ቅጠል ርጋፊ ወይም አቧራ ይኖራል።
ቢሆንም መጥረጊያው እና ጓንቱ ወጪ ወጥቶበታል። ሕዝቤ ፖለቲካው ላይ ተመስጥኦን እና ወከባን በአንድ አጣምሮ ይዞ፤ በዚህ በኩል ኢኮኖሚው የወደቀበትን ፈተና ዘንግቷል። እንጂ እያንዳንዱ ወጪአችን በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጊዜ ላይ ነን። ይሁን ይውጣ! መጥረጊያ ለቆሻሻ እንጂ ለንጹህ ስፍራ ምኑ ነው? እንደውም የመንገዶች ባለስልጣን «ንጹህ መንገድ እየጠረጋችሁ አስፋልቱን እንዳታሳሱት» እንዳይል እሰጋለሁ።
ባለስልጣናቶቻችን እንደ ቀደመው ጊዜ በጥቁር መኪና ተጋርደውብን እየሄዱ አይደለም። እንደዛ ቢሄዱም አሽከርካሪው በአቋራጭ መንገዶች እየወሰዳቸው ካልሆነ በቀር ቆሻሻ ያለበትን ስፍራ መለየት ከባድ አይደለም። ጉራንጉር ውስጥ ይገቡ እያልኩኝም አይደለም፤ ግን ቢያንስ ከልባቸው ያድርጉት ነው። አንዳንድ ሰው «ይቀልዳሉ እንዴ?» ሲል ስሰማ ምሳሌ ለመሆን የተደረገው ጥረት በቂም ሆነ አሳማኝ እንዳልሆነ ስለምረዳ ነው።
እነሱን አልኩ እንጂ እኛንም ታዘቡ! በምኖርበት ሰፈር አካባቢ ካለ አንድ ግዙፍ አደባባይ ላይ የሚታየውን ነገር አንድ የሥራ ባልደረባዬ እንዳስተውለው አሳሰበችኝ። አደባባዩ ሰፊና አረንጓዴ ነው፤ በዛም ላይ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎትም ይሰጣል። ፍቅረኛሞች ይገናኙበታል፣ ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር ይታዩበታል። አለፍ ስትሉ እኔ ነኝ ያሉ ቆሻሻዎች ይጣሉበታል።
ሸገር አዲስ አበባችን ዘመን ሳንቆጥር፣ ቀን መቁጠሪያ ሳናገላብጥ ወቅቷን በመንገዷ ብቻ የምታሳውቅ አስማተኛ ከተማ የመሆኗ ሚስጥር እዚህ ላይ ይገለጣል። ክረምቱን በበቆሎ፣ ከዛ አለፍ ስንል እሸት፣ ከፍሬፍሬ ማንጎ፣ ፕሪም፤ ወቅቱንና ጊዜውን መንገዱ ይነግረናል። ታድያ በዚህ በሰፈራችን አደባባይ በዓል ሰሞን ከሆነ የበሬና የበግ ጭንቅላት በርከት ብሎ ይታያል ማለት ነው። የዶሮይቱስ የት እንደሚደርስ እንጃ!
እና የሰፈር ሰው ሆ! ብሎ ለጽዳት ሲወጣ አደባባዩን «ባላየ» ያልፈዋል። እንግዲህ ማን ላይ ልንፈርድ ነው ታድያ? ብቻ የእኛ ሰፈሩ ጽዳት በየትዕይንተ መስኮቱ የማይታይና እንደ አሸን በሆኑት የቴሌቭዥን ጣብያዎች የማይሰራጭ በመሆኑ ተርፈናል። ባለስልጣናቶቻችን ግን እያየናቸው ነውና ይደብራል! ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተመሳሳይ አረአያነት ለማሳየት መጥረጊያ ይዘው ሲወጡ በትክክል ቆሻሻ ያለበት ቦታ ነው የተገኙት። መጥረጊያ አፈጣጠሩ ለቆሸሸ ስፍራ ነዋ!
አለማወቄ ይሆን? እሱማ ይሄ ፕሮቶኮል የሚባል ነገርም አለ። አስቸጋሪ ነንኮ! «ጽዳት ሠራተኞች እያሉ እንዲህ ቸክሎ ማጽዳት ምን ማለት ነው? ባለስልጣን አይደሉ?» ልንላቸው ሁላ እንችላለን። የእኛን ነገር ተውት! ብቻ ግን እነርሱም ንጹህ ስፍራ እየፈለጉ መጥረጊያ ከሚይዙ ጽዳትና ትኩረት የሚሹት ቢቃኟቸው ለማለት ነው። እኛም የተጣለን ቆሻሻ ለዓይናችንና ለአፍንጫችን ከመጠየፍ ባሻገር እስቲ በየመንገዱ መጣሉን ያሳፍረን ለማለት ነው። መልካም ጽዳት፤ ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
ሊድያ ተስፋዬ