የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቆሻሻ ነዋሪዎቿን መሄጃ አሳጥቷል።ሁሉም ተማሯል።ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ የአገሪቷን የኢኮኖሚ አቅም በሚያፈረጥም ቆሻሻ ምክንያት ንፁህ አየር እና ፅዱ መንደር የማግኘት እድላችን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
‹‹አዲስ አበባ›› የሚለውን ስሟን ለሰማ በመዲናችን ውስጥ እንኳን በአይን የሚታይ ቆሻሻ ይቅርና ህዝቦቿ ቆሻሻን አይተው የሚያውቁ አይመስልም።በየቦታው ተከምሮ የሚታይ ቆሻሻ መብዛቱ ያሳሰበው በመንግሥት እራሱ የፅዳት ዘመቻ እያካሄደ ነው።እንዴት ከተማችን በመንግስት ጎትጓችነት እናጽዳት? ይህ ሁኔታስ እስከመቼ ይዘልቃል? በቀጠሮስ እስከመቼ እናፀዳ ይሆን? ጥያቄያችንን እንዲመልሱልን ብለን በተለያዩ የከተማችን ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎችን አነጋገርን።እነሱም በደስታ እንዲህ ሲሉ መለሱልን፡፡
ወጣት እስከዳር ፍስሃ በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ነው።በጉዳይ ላይ እንዲህ በማለት ሃሳቡን ይሰነዝራል።የንፅህና ጉዳይ የሁሉም ነው።ለባለስልጣንም ሆነ ለአንድ ግለሰብ የሚተው ጉዳይ አይደለም።አስቀድሞም ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን ቢወጣ ከተማዋ አሁን ባለችበት ሁኔታ አትገኝም ነበር።እናም ሁሉም ከተማውን እንደየቤቱ መንከባከብ አለበት።በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ የላስቲክ አወጋገድ ስርአቱን ትኩረት ቢሰጠው በጣም ጥሩ ነው፤ ለረጅም ጊዜ ሳይበሰብሱ የሚቆዩና የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦዮችን በመዝጋት ለተጨማሪ ብክለት ያጋልጣል።
‹‹ሕብረተሰቡ ከተማውን ለማፅዳት የመንግስትን ቅስቀሳ መጠባበቅ የለበትም›› የሚለው እስከዳር፤ መንግሥትም እኔን እያያችሁ አፅዱ ማለቱን ትቶ ህዝቡ ላይ የአስተሳሰብ ሥራ መስራት መቻል አለበት የሚል አስተያየት ይሰጣል።ማንኛውም ሰው ፊቱን በየቀኑና ያለማንም አነሳሽነት ለራሱ ጥቅም መሆኑን አውቆ እንደሚታጠበው ሁሉ አካባቢውንም ከብክለት ያለማንም አነሳሽነት ማፅዳት ይገባዋል የሚል አመለካከት አለው። ቆሻሻን እንደየመልኩ ለይተን የማስወገድ ልምዳችን ዝቅተኛ ነው የሚለው ወጣት እስከዳ አንዱ ሲያፀዳ ሌለው ቆሻሻን መንገድ ላይ መጣል እንደሌለበት ይናገራል።ቆሻሻን ማስወገድ የሚቻለው በጋራና በህብረት መሆን ሲቻል ብቻ መሆኑንም ያስረዳል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ሃይመሎ በበኩላቸው ለከተማ ፅዳት ወሳኙ ነገር የነዋሪዎቿ ተነሳሽነት ነው ይላሉ።ስሜት የሌለውን ህዝብ መንግሥት ቢያስተባብርም ዘላቂና አመርቂ ሥራ ውጤት ማምጣት አይቻልም።እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ መንግሥትን የሚደግፉ ነዋሪዎች በወር አንድ ጊዜ ነቂስ ወጥተው ሊያፀዱ ቢችሉም፤ ነገር ግን በፍላጎት ከሆነ በየቀኑ አካባቢያችንን ማፅዳት እንችላለን ብለዋል።
‹‹ንፅህናችንን ለመጠበቅ መንግስት በየወሩና በየሁለት ወሩ የፅዳት ዘመቻ ሲያካሄድ መሆን የለበትም ምክንያቱም ንፅህና የዕለት ተዕለት ጉዳይ ነው›› የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘካሪያስ ለዚህ ደግሞ ዋናው አመለካከት ላይ መስራት በማለት የመፍትሄ ሃሳብ ያመለክታሉ፡፡
አቶ ዘካሪያስ የሩዋንዳዋ ኪጋሊ ከተማን ጠቅሰው «በአጭር ጊዜ ውስጥ በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ብዙ ህዝቧን በሞት አጥታለች፤ ነገር ግን በአገራቸው ጉዳይ አንድ ናቸው። መዲናቸውን በውበቷና በማራኪነቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደምት እንድትሆን አድርገዋል።» ብለዋል። ኢትዮጵያም ፅዱ እንድትሆን ከበቀል፣ ከብሔር ፖለቲካ፣ ከተንኮልና ከጎጠኝነት ሁሉም ራሱን በማፅዳት ከተማዋን ብቻ ሳይሆን መላ አገሪቱን ውብና ጽድ ማድረግ እንችላለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ኢንጅነር ጉተማ ሞሮዳ እንዳሉት፤ ሁሉም ሕብረተሰብ በጽዳት ሥራው ላይ በቀጣይነት እንዲሳተፍ ለማድረግ እስከወረዳ ድረስ መዋቅር ተዘርግቷል።ቆሻሻን ማፅዳት ለራስ መሆኑንና የቆሻሻን አስከፊነት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ ነው።ካሁን በኋላ ሕብረተሰቡ ያለ ማንም ቀሽቃሽነት እንዲያፀዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠንክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ ፅዱ ከተማን መፍጠር ለራሱ መሆኑን በመገንዘብ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአቱን ማዘመን አለበት ያሉት ኃላፊው፤ በተለይ ደግሞ መዲናችን የብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኽሪያ ስለሆነች፤ ፅዱና ምቹ ሆና ለቱሪስትም ሳቢ እንድትሆን ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
ሞገስ ፀጋዬ