ግብጽን ለመደገፍ ጉቦ በመቀበል የተከሰሱት አሜሪካዊ የምክር ቤት አባል ክሱን አስተባበሉ

የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተከሰሱት የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ቦብ ሜንዴዝ ከወንጀሉ ነጻ ነኝ ሲሉ ተናገሩ።

በቤታቸው በፍተሻ የተገኘው ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር ለአስርት ዓመታት የለፉበት ገንዘብ እንደሆነም ገልጸዋል።

ቤታቸው ውስጥ ይህን ያህል ገንዘብ ያስቀመጡትም በባለሥልጣናት ሊወሰድ ይችላል በሚል ከኩባ ወላጆቻ ቸው በተላለፈባቸው ስጋት መሆኑንም አስረድተዋል።

የኒውጀርሲው ተወካይ ሮበርት ሜንዴዝ ከሙስና ክስ ነጻ መውጣት ብቻ ሳይሆን በሚቀጥለው ዓመት በምርጫ እንደሚወዳደሩም ተናግረዋል።

የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ፖለቲከኛውና ባለቤታ ቸው የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ሲል ከሷል።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት ይፋ በሆነው ባለ 39 ገጾች ክስ መሠረት ሜንዴዝ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በሀገራቸው እና በውጭ ሀገራት ባሉ የሙስና እቅዶች ላይ ተጽእኖ በማሳደር ክስ ቀርቦባቸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ መንበር በአሜሪካ በሚገኘው የግብጽ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ ዲፕሎማቶችን በተመለከተ ከፍተኛ ምስጢራዊ መረጃዎችን በማጋራት እንዲሁም የግብጽን መንግሥት ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ የሚደግፉ ርምጃዎችን ወስደዋል ተብለዋል።

ለዚህም ሜንዴዝና ባለቤታቸው ናዲን አርስላኒያን ከሦስት የኒውጀርሲ ነጋዴዎች ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ለቤት ብድር የተፈጸመ ክፍያና የቅንጦት ተሽከርካሪ ጉቦ እንደተቀበሉም ክሱ ያስረዳል።

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር በትውልድ ሀገራቸው ኒውጀርሲ ከሚገኙ ዲሞክራቶች ከአባልነታቸው እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄም ውድቅ አድርገዋል።

“ሁሉም እውነታዎች ግልጽ ሲሆኑ ከወንጀሉ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን አሁንም በኒውጀርሲ ከፍተኛ የምክር ቤት አባልነቴ እቀጥላለሁ” ሲሉም ሜንዴዝ ሰኞ እለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ፖለቲከኛው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከተከሰሱ ጀምሮ በአደባባይ ላይ ሲታዩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

“በኔ ላይ ለመፍረድ የተጣደፋችሁ አቃቤ ሕግ በሰጣችሁና ሆን ተብለው በተወሰኑ መረጃዎች ላይ ተመስርታችሁ ነው።” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የፌደራል የደኅንነት ሠራተኞች የፖለቲከኛውን ቤት በፈተሹበት ወቅት ከ480 ሺህ ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ በአብዛኛው በፖስታ ውስጥ እንዲሁም በልብስ ውስጥ ኪሶች፣ በቁም ሳጥኖች እና ካዝናዎች ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውም ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ከግል ቁጠባ አካውንቴ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር በጥሬ ገንዘብ አውጥቻለሁ። ይህንን ገንዘብ ቤት ያስቀመጥኩት ለድንገተኛ አደጋ እና ወላጆቼ ኩባ በነበሩበት ወቅት በባለሥልጣናት ገንዘባቸው ከመወረሱ ጋር ተያይዞ ያደረብኝ ስጋት ነው።” ሲሉም ነው የተናገሩት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026

Recommended For You