የአውዳመት እንኮይ

ሙሉጌታ ብርሃኑ

ሆ ብለን መጣን

ሆ… ብለን

………

አበባየሆሽ

……….

አበባየሆሽ

……….

ባልንጀሮቼ

………

ግቡ በተራ

……..

ይህችን ዜማ ለብቻ ሲሏት እንዲያው ውበታዊ ለዛዋ ይቀንሳልና አዝማቿን ብታግዙኝ ብዬ ተመኘሁ። የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታታ ነውና ዜማዋን ከመግቢያዬ ላይ ሳሰፍር የዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ ጉዞ ወዴት እንደሆነ አስቀድማችሁ መገመት አያዳግታችሁም። አዎን! አልተሳሳታችሁም። ጀንበር አዘቅዝቃና ማልዳ አዲስ ፀሐይ ልትፈነጥቅ ስትሰናዳ ፣ አዲስ ጨረቃም ሰማይ ምድሩን ብሩህ ልታደርገው የመስከረምን መጥባት ስትጠባበቅ፣ በወርቃማዎቹ የጳጉሜን ቀናት አልፈን አዲሱን ዓመት ስንቀበል ሌላ ስለምን ልናወራ እንችላለን?።

አዲስ አመት ሲነሳ ከነ ማጣፈጫ ቅመሙ ነው። ማጣፈጫ ቅመሙ ደግሞ ምንድነው ብላችሁ እራሳችሁን በመጠየቅ ምላሹንም ከራሳችሁ ለማግኘት የማሰቢያ ጊዜ እንደማትሹ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም አዲስ ዓመትን ባስታወስን ቁጥር የበዓሉ ግርማ ሞገስ የሆነውን ሙዚቃውንም አንዘነጋውምና።

ይሸታል ዶሮ ዶሮ፣

ይሸታል ዶሮ ዶሮ፣

የእማምዬ ጓሮ፣

ይሸታል ጠጅ ጠጅ፣

ይሸታል ጠጅ ጠጅ፣

የአባብዬ ደጅ፣

እያልን ዘመን በማይሽረው የባህል ዜማ ተሰባስበን ልባችን ውልቅ እስኪል መጫወታችን ከዶሮና ጠጁ ጋር የአውዳመቱ ሽታ የእውነትም ቢያውደን ነው “ይሸታል ዶሮ ዶሮ ” የምንለው። ይሄን ጣፋጭ የዶሮ ወጥ ያለ በርበሬና ጨው፣ ያለ ቅመማ ቅመሙ ጣዕሙን ከወዴት ሊያመጣ…”ይሸታል ጠጅ ጠጅ” ስንልስ የጠጁ መዓዛው ማወዱ ከእሜትዬ ሙያ በስተጀርባ ማሩ በመኖሩ አይደል…! ታዲያ ልክ እንደዶሮውና ጠጁ ሁሉ የአዲስ ዓመት በዓላችንን አውዳመት አውዳመት እንዲሸት የሚያደርግልን እጹብ ማጣፋጫ ሙዚቃዎች ስለመሆናቸው ማናችንም የማንክደው የጋራ ሀቅ ነው።

ሀቅ የተቀላቀለበትን ይሄን አስተያየት በግራም ሆነ ቀኝ ይዘን ወደ ሙዚቃዎቻችን መንደር እንዝለቅ። የዛሬዎቹ ሙዚቃዎችችን መነሻዎቻቸው እንቁጣጣሽ ናትና ስለእርሷ ጥቂት ሳንል አልፈን ቅር እንዳትሰኙ እንቁጣጣሽ መቼ ተፀነሰች? ከአዲስ ዓመትስ ጋር እንደምን ብላ ተቆራኘች? ለሚሉት ጥያቁዎች መልስ መስጠቱ ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ኃያልነትና የነገሥታቷ ጀብደኝነት በመላው ዓለም ገኖ በወጣበት ዘመን መሆኑን ታሪክ ይነግረናል። በዘመነ ሳባውያን የሳባውያኑ ንግሥት የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ በጊዜው ከሌላኛው የዓለም ጫፍ ስለነበረ ስለ አንድ ጠቢብ ንጉሥ ታሪክና ዝና ትሰማና በጣም ትገረማለች። ይሄኔ ታዲያ ልቧ ይማረካል። ዝናው በዓለም ሁሉ የናኘው ሰውም የንጉሡ የዳዊት ልጅ፤ጠቢቡ ሰለሞን ነበር። ንግሥተ ሳባም የሰማሁትን ሰምቼስ እውነታውን ባይኔ በብረቱ አይቼ ሳላረጋግጥ አልቀመጥም ስትል የኮበለለውን ልቧን ተከትላ፣ጃንደረባዎቿን አስከትላ፣ ስጦታው አሰልፋ ወደ ሀገረ እስራኤል አቀናች።

የተባለውንና የተነገረውንም ደርሳ በአይኗ አየች፤ በልቧም አመነች። የተወሰኑ ጊዜያትን እዚያው አሳልፋ ሁሉንም መልክ መልኩን፣ ፈርጅ ፈርጁን አስይዛ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ የዘር ሐረግ መዛ በድል ወደ ሀገሯ ተመለሰች። ሀገሯ እንደገባች የክረምቱ ወራት አልፎ መስከረም በአደይ አበባ ተንቆጥቁጣ ነበር። የእርሷን የመመለስ ወሬ የሰማ የሀገሬው ሕዝብም ከሕጻን እስከ አዋቂ በተለይ ደግሞ ልጅ አገረዶች ስጦታ ይዘው ከመጠበቂያ ማማው ተጠገጠጉ።

ንግሥቷ በደረሰች ጊዜም እንደ ሀገሬው ወግና ሥርዓት እንኳን ደህና መጣሽ እያሉ “ከእሩቁ ሀገር ከብዙ ድካም የመጣሽ ነሽና ባዶ ቤት ስትገቢ እንዳይከፋሽ በማሰብ እንቁ ለጣጣሽ(ለሚያስፈልግሽ ሁሉ) የሚሆን እንቁ አምጥተንልሻል ሲሉ ለንግሥታቸው ያመጡትን ሥጦታ ከአደይ አበባ ጋር እያደረጉ አበረከቱላት። ይሄው ዛሬም ድረስ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በአደይ አበባ እየተንቆጠቆጥን እንቁጣጣሽ የማለታችን ሚስጥር የያኔው የእንቁ’ ለጣጣሽ ስጦታ ነው።

ሙዚቃና አዲስ ዓመት እንደ ዳቦና ቢላ ናቸው። ዳቦ ያለ ቢላ እንደማይቀርብ ሁሉ አውዳመቱም ያለ ሙዚቃ አይታሰብም። አዲስ ዓመት ሲቃረብ ዘንድሮስ ማን ምን አዲስ ሙዚቃ ያሰማን ይሆን ብለን እንደዋዛ እራሳችንን ሳንጠይቅ አናልፍም። ምክንያቱም በየዓመቱ ከጆሮዎቻችን ወደ ውስጣችን እየፈሰሱ ተጠራቅመው ኩሬና ሀይቅ የሰሩ ሙዚቃዊ ትዝታዎች ከነትውስታዎቻቸው ልባችንን ሞልተውታልና። ምስጋና ለድምጻውያኑ በተለይ ደግሞ ለቀደምቱ ይግባና በየዘመናቱ ዘመን አይሽሬ የአዲስ ዓመት የሙዚቃ ገጸ በረከት አኑረውልናል።

የጠጅና ዶሮ ወጡ ሽታ ከአፍንጫችን ሽው እያለ የሆዳችንን አምሮት ሲቀሰቅሰው፤እነዚህ ሙዚቃዎችም ከጆሮዎቻችን እየዘለቁ ልባችንን እየፈነቀሉ በውስጣዊ ስሜት አጥለቅልቀውናል። አዲስ ዘመን በውበት አጊጦ እንደ ሰለሞን ቤተ መንግሥት በእንቁ ሲንቆጠቆጥ፣እንቁጣጣሽም በአደይ አበባ ታጅባ ስትመጣ፤

“እንቁጣጣሽ

እንኳን መጣሽ

በአበቦች መሐል

እንምነሽነሽ”

እያለች ድምጻዊቷ በሙዚቃዋ ተቀብላታለች። ለስለስ አድርጋ ስትጀምር በዚህ ጥኡም ሙዚቃዋ ለጆሮዋችን ሳይሆን ለልባችን የቀረበች ያህል ይሰማናል። እንቁዋ ድምጻዊት ዘሪቱ ጌታሁን የእንቁጣጣሽን የመምጣቷን ብስራት በዚህ ሙዚቃ ስታበስረን ለበርካታ ዓመታት ሳንጠግብ እንደ አዲስ አድምጠናታል። በሔድንበት በገባንበት ሁሉ ይህን ሙዚቃ በሰማን ቁጥር ከድምጻዊቷ ጋር አብሮ ለማንጎራጎር ልባችንስ ሳይነሽጠው መች ቀረና… ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የሙዚቃውን ግጥምና ዜማ አምጠው ወልደው በዓመታት ብዛት እንዳይገረጅፍ አድርገው እንዲህ ባማረ መልኩ ሠርተውታል። የድምጻዊቷ ዘሪቱ መረዋ ድምጽ ሲታከልበት ደግሞ እንደ መስከረም አደይ አበባ ፈክቶ፣ እንደ ዶሮውና ጠጁ ሁሉ መዓዛው የሚያውድና ከሩቁ የሚጠራ ሆኗል። የዘሪቱን የሙዚቃ ጥሪ ያደመጡም፤ ከአንጋፋዋ ድምጻዊት አስቴር አወቀ ጋር እንዲህ ሲሉ አብረው እያዜሙ ይገባሉ።

“እዮሃ አበባዬ

መስከረም ጠባዬ

መስከረም ሲጠባ

ወደ ሀገሬ ልግባ”

የዚህን ጊዜ ወደ ሀገሩ መግባት የማይናፍቅ ማን አለ? የዛሬን አያደርገውና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመድረኳ ፈርጥ አስቴር አወቀ በዚህ ሙዚቃ ያላቀጣጠለችው መድረክ፣ ያላሞቀችው አዲስ ዓመት አልነበረም። እሷ በተገኘችበት መድረክ ቁዘማ ብሎ ነገር የለም። ከስርቅርቅ ድምጿ ጋር ማራኪ እንቅስቃሴዋ ታክሎበት በመድረኩ ላይ ከጫፍ ጫፍ ሽር ብትን እያለች የታዳሚውን ቀልብ እየሳበች የሁሉንም ስሜት በቁጥጥሯ ሥር ስታደርገው የነበረውን ደማቅ የመድረክ ውበት፤ ‹‹ነበር!›› ብለን እንደ ትዝታ ልናልፈው ነው። ለማንኛውም ግን የአዲስ ዓመት ሙዚቃ ኮከብና ባለ ልዩ ቀለሟ፤ድምጻዊት ሀመልማል አባተ እንኳን አደረሳችሁ ትለናለች። እኛም እንደ ወጉ እንኳን አብሮ አደረሰን እንበላትና በሙዚቃዋ መግቢያ ላይ የምታቀልጠውን እልልታዋን ሳንዘነጋው ስንኟን ቀንጨብ አድርገን እናስታውሳት።

“የክረምቱ ወር አልፎ የበጋው መጥቷል፣

ሜዳው ሸንተረር ጋራው በአበቦች ደምቋል፣

ሸመንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ፣

ድረስ ለአውድአመት በሀገር መንደሩ፣”

ጥሪዋ ከባድ ነው፤ ድምጿ ከጆሮ ሲደርስ ከልብ ላይ ያይላል። ተፈጥሮ ሳይቀር የሚያከብረው የአዲስ ዓመት ድባብ ከጋራ ሸንተረሩ እየተወነጨፈ፣ ከሣር ቅጠሉ ሁሉ እየበነነ በከባቢው ላይ ሲረብብና ውስጣችንን በሀሴት ሲሞላው ከአየሩ ላይ መቅዘፍ ያስመኘናል። በሙዚቃው ውስጥ ያለው መግነጢሳዊ ኃይል ምነው ንቧን ባደረገኝና ከአፈር ምድሩ ላይ ከተንቆጠቆጠው አደይ አበባ በቀሰምኩ ያስብላል። ለካስ ሙዚቃም የሚያውድ ሽታ አለው፤ ታዲያ ለአፍንጫና ምላስ ሳይሆን ለማይታየውና ለስድስተኛው የስሜት ሕዋስ…ኩልል ያለ መዓዛ፣ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ውበትን የተጎናጸፈ አምሳለ ምስል በልብ ላይ ይቀርጻል።

በኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ታሪክ የሙዚቃ አብዮት የተቀሰቀሰበትና በርካታ አይረሴ ሙዚቃዊ አሻራ በማሳረፍ ደረጃ ክብረ ወሰኑን በመስበር እስከ ዛሬም አላስደፍር ያለው ዓመት የሚሊኒየሙ አውዳመት ነው ብለን በቀዳሚነት ብንይዘው ስህተት አሊያም አድሎ አይሆንብንም። በዚህ ጊዜ ከተለቀቁ የምንም ጊዜም ምርጥና ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች መሃከል የቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)- አበባየሆሽ አንደኛው ነው። በተለያዩ ችግሮች ለተደቆሰችው ለሀገራችን ኢትዮጵያ ከአውዳመት ማድመቂያነት አልፎ መልዕክቱ ዛሬም ትኩስ ነው። አበባ፣ከአበባም ቢጫ አበባ፣ ከቢጫም ደግሞ ተፈጥሮ በልምላሜ የምትችረን ይሄው አደይ አበባ የተስፋ ተምሳሌታችን ነው። ድምጻዊው በዚሁ የአደይ አበባ ማሳ ውስጥ ወደፊት እያስጓዘን ዛሬ ምንም ቢከፋ መጪው ዓመት የትንሳኤ ነው፤ ደግሞም ጥሩ ይሆናል እያለ ውስጣችንን በተስፋ ያስታጥቀዋል።

“ምልኤላዊው ዘመን

የአምላክ በረከቱ

በኢትዮጵያ ትንሳኤ

ዘመነ ሁለቱ

ስትሰሙ መለከት

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ…”

ሲል የተስፋውን አበባ እያመለከተ እንድንቀስም ይነግረናል፤ ያሳየናል። ታዲያ ከተመለከትን ወዲያ የምን ቁዘማ ነው በጨዋታው እየቦረቅን ተሰባስበን ወደ ተስፋው ማሳ መሮጥ ነው እንጂ… እሱም ከመሃሉ ሞቅ ባለው ዜማ “አበባየሆሽ” እያለ በማጀብ ድፍን አስራ አምስት ዓመታትን ስንሻገር ዛሬም ታዲያ ሙዚቃው አልበረደም ፤ስሜታችንም አልቀዘቀዘም። እነዚህንና የመሳሰሉ ውብ ዜማዎች አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በየዓመቱ አድምጠናቸዋል። ከዘመድ ወዳጅ ጓደኛ ጋር ሆነን ወገባችንን ፈትሸንባቸዋል። ደስታና ፍቅር ተለዋውጠን ተመራርቀንባቸዋል። ግን ዛሬም አይሰለቹንም፤ እንናፍቃቸዋለን። አዎን በእነዚህ ውስጥ ያሳለፍነው ልዩ ትዝታ እንዴት ይረሳል?

በአስራ ሦስት ወራት ፀጋ የተቀነበበ ነውና የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ “የአውዳመቱ ትዝታ አይጠፋም ህያው ነው” ሲል ይነግረናል። በበዓሉም ሆነ በበዓሉ ማግሥት ይሄን መሳይ እጹብ ሙዚቃ እያደመጥን ትዝታውን ከተስፋ ጋር እናዋህድበታለን። በታላቁ ድምጻዊ ጥላውን ገሰሰ “የአስራ ሦስት ወር ፀጋ” በተሰኘው ልዩ የአዲስ ዓመት ዜማ ውስጥ ከተካተቱ የግጥም ስንኞች መሃከል እነዚህ ይጠቀሳሉ።

“በፀሐይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ፣

የትውልድ ማገር ያላት የአስራ ሦስት ወር ፀጋ፣

ወግና ልማዳችን የወረስነው ካበው፣

የአውደ ዓመቱ ትዝታ አይጠፋም ህያው ነው፣”

እውነት ነው፤ ትዝታው ከአይነ ህሊና ዜማዎቹም ከአንደበታችን አይጠፉም። ጊዜና ሁኔታ ስሜታችንንም ያወጁ በመሆናቸው እንደ እንጀራና ወጡ ብሉኝ ብሉኝ፤ እንደ ጠላና ጠጁም ጠጡኝ ጠጡኝ ያሰኛሉና ይሄን ማን ከቶ ይጠላል። እኚህን የመሳሰሉ ከትናንት እስከ ዛሬ የነገሱ የአውዳመት ሙዚቃዎችን ቃኝተን ዞር ስንል ታዲያ ዛሬስ ምነው እንደ እነዚሁ ሁሉ ዘመናትን በፍቅር የምናደምጣቸው ሙዚቃዎችን የሚያበረክትልን ሙዚቀኛ ጠፋ? ብለን ለመጠየቅ ቢቃጣን እንደ አጉል ነገር አይቆጠርብንም። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈዞ የመፋዘዝ ድባብ ውስጥ ሳንሰጥም አንቀርም።

ድሮ ድሮማ አዲስ ዓመት ደረሰ በተባለ ቁጥር ተሽቀዳድመው በሙዚቃዊ አንደበታቸው እንኳን ደህና መጣህ ሲሉ አዲስ ዓመትን የሚቀበሉት ሙዚቀኞቹ ነበሩ። አዲስ ዓመት ብቻ ሳይሆን አዲስ ሙዚቃም እንሰማ ነበር። ሌላው ቀርቶ አዲሱን ዓመት ተከትሎ የሚዥጎደጎዱት የአልበም ብዛቶች እንደ ዛሬው ብርቅ ድንቃችን አነበረም። ዛሬም ድረስ አውዳመትን የምንቀበለው ከአስርና አስራ አምስት ዓመታት በፊት በተሰሩ ሙዚቃዎች ነው። ይህ በመሆኑ ለእነዚሁ ቀደምት ሙዚቃዎችና ሙዚቀኞች ያለን አድናቆት በእጅጉ ላቅ ያለ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከእነዚህ ተርታ የሚሰለፍ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ሙዚቃ ከዛሬዎቹ ሙዚቀኞቻችን ዘንድ ስለምን አላገኘንም ስንል ቅስማችን ባይሰበርም ማዘናችን ግን አይቀርም።

መስከረም ሲጠባ፣ አደይ ሲፈነዳ፣ የክረምቱ ጭጋግ አልፎ ብሩህ ሰማይ ሲገለጥ፣ አዕዋፋት በዝማሬ ቅኝት ሲያጀቡ፣እጽዋትም በለመለመው መስክ ከንፋሱ ጋር ሲያሸበሽቡ፣ ምድርም በውበት ተንቆጥቁጣ የገነት አምሳል በምትመስልበት በዚህ ጊዜ አዲሱ ዓመታችን በእነዚህ ሁሉ ሰማያዊ ስጦታዎች ታጅቦ በመወለዱ፤ለግርማ ሞገሱ ጽንፍ አይገኝለትም። እንደ ጋቢና ነጠላ የነጣውን ባለ ሀምራዊ ቀለም ሀገራዊ ፍቅር፣አንድነትና መተሳሰቡን ደግሞ ለእኛ ያድርገው እያልን በቀጣዩ ስንኝ እንሰናበት! መልካም አዲስ አመት!!

በኛማ አውዳመት፣

በኛ እንቁጣጣሽ፣

ሀገሬ አይክፋሽ፣

ፍቅር እንዳይርብሽ፣

ነይ! ውጪ ከሃጃሽ፣

አብረን እንምነሽነሽ።

ጥጋብ ከአዝርቱ፣

በማር በወተቱ፣

ሰላም ሰበከቱ፣

ፍቅርም እንደ ጥንቱ፣

በረካው ከቤቱ፣

ይሙላ ከማጀቱ።

በአውዳመታችን፣

ካውደ ምረታችን፣

ሰላም ይፍሰስብን!

ፍቅር ይዝነብብን!

እያልን አበቃን ፣

እንኳን አደረሰን!!

አዲስ ዘመን  መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You