ብዙ ህፃናትን ጨምሮ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች ያካሄዱት ምርመራ ውጤቱ በደማቸው የኤች አይ ቪ ቫይረስ መኖሩን ማመላከቱ አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ህፃናቱ ለቫይረሱ የተጋለጡት በጤና ተቋማት ከሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በደቡብ ፓኪስታን ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስመርመር ስጋት እንዳደረባቸው እና ምናልባትም የኤች አይ ቪ ቫይረስ የህክምና ባለሙያዎች ለህክምና በሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ሳቢያ ተጋላጭነቱ ተስፋፍቷል ተብሎ እንደሚገመት ትናንት አልጀዚራ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡
በሲንዲን ግዛት ላራንካን ዋሳዮ መንደር ባለፈው ወር አምስት የምርመራ ክፍሎች ተዘጋጅቷል፤ ሆኖም የቁሳቁስ እና የጤና ባለሙያ እጥረት አጋጥሟል፡፡ የማካሺፍት ክሊኒክ ሐኪሙ ‹‹ ነዋሪዎች በደርዘን ለመመርመር እየመጡ ነው›› ካሉ በኋላ ሆኖም ግን በበሽታው የተያዙትን በአግባቡ የሚመክር እና የሚንከባከብ አለመኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ቢሮ ባሳለፍነው ሳምንት በፓኪስታን ከተመረመሩ ሰዎች ውስጥ በ400 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት ጥራቱ እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ የህክምና ቁሳቁስ እና የህክምና ስህተት መሆኑን በይፋ ጠቁሟል፡፡ ባለሥልጣናቱ በአደባባይ የሕፃናት ሐኪም የሚያደርሱት ጉዳት በቸልተኝነት ወይም በተንኮል አዘል ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፤ ይህ ወረርሽኝ በድሃ መንደር ውስጥ ኃይለኛ ብስጭትና ፍርሃት ማስከተሉን ገልፀዋል፡፡
ከመንደሯ ነዋሪዎች ደፍረው ለመመርመር የመጡት ሙክታር ዝፓቬብ የሴት ልጃቸውን ውጤት ሲጠባበቁ ያገኙት ውጤት እንደሌሎቹ ሁሉ የሚያበሳጭ ሆኖባቸዋል፡፡ በክሊኒኩ የአንድ ዓመት ልጁን ያስመረመረው ናስር አህመድም ልጁ በኤች አይ ቪ የተያዘችው በሐኪሞቹ ቸልተኝነት መሆኑን በመናገር እጅግ በብስጭት ሲዝት እንደነበር ተዘግቧል፡፡
አምስት ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ያስመረመሩት ኢማም ዛይድም በአንዲት የልጅ ልጃቸው ላይ ቫይረሱ መኖሩ እጅግ ያሳዘናቸው ሲሆን በመንደሩ ግንዛቤው ባለመኖሩ ‹‹ ትገለላለች፤ አብሯት የሚጫወት ሰው ታጣለች፤ ስታድግም የሚያገባት ባለመኖሩ ትዳር አትመሰርትም›› የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ለአሥር ዓመት ተገቢው የጤና አገልግሎት ሽፋን ባለመኖሩ በተለይ በድሃ መንደሮች ቫይረሱ ታክሎበት የአካባቢው ኢንቨስትመንት እየተጎዳ መሆኑን እና ሰዎቹ ላይም ከፍተኛ ጫና እያደረ እንደሚገኝ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በፓኪስታን የኤች አይ ቪ ስርጭት አነስተኛ እንደሆነ ይነገር ነበር፡፡ አሁን ግን በአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች እና በሴተኛ አዳሪዎች ላይ በስፋት ከመታየቱም ባሻገር ህፃናት ላይም እየተገኘ ሲሆን እ.አ.አ በ2017 አዲስ 20ሺ የቫይረሱ ተሸካሚዎች መኖራቸው ታውቋል:: በዚህም ሳቢያ ከኤዢያ አገራት ውስጥ አገሪቷ በኤች አይ ቪ ስርጭት የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም
ምህረት ሞገስ