የጤናው ዘርፍ ዛሬና ነገ

በ2015 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታላላቅ ሀገራዊ የጤና ጉዳዮች ተከናውነዋል። በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ የደረሰችበትን እድገት የሚያሳይ ታላቅ ሀገራዊ የጤና አውደ ርዕይ ቀርቧል። የጤናውን ዘርፍ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ አሰራሮችም ተዋውቀዋል። የኮሌራ፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር፣ የኮቪድና የፖሊዮ ክትባቶች በተጠናከረ መልኩ ተሰጥተዋል።

ይህ በጀት ዓመት በታላላቅ ዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤዎች ላይ ተሳትፎ የተደረገበትና ከጉባኤዎቹ ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት፤ ብሎም በጉባኤዎቹ የኢትዮጵያን የጤና ሴክተር ሊለውጡ የሚችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው። በተመሳሳይ በሀገር ውስጥም በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ጉባኤዎችም ተስተናግደዋል።

በዚህ በጀት ዓመት የጤናውን ዘርፍ የሚደግፉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል። የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ስምምነቶችም ከአጋር አካላት ጋር ተፈርመዋል። ከድርቅ፣ ግጭትና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ምላሽ የተሰጠበትና በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ሰፋፊ ሥራዎች የተሰሩበት ዓመትም ነው 2015 ዓ.ም። በጀት ዓመቱ ነፃ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት፣ የደም ልገሳና ሌሎችም ጤና ነክ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተሰጥተውበት አልፏል።

በ2015 ዓ.ም በጀት መግቢያ የሥርዓተ ምግብ ትግበራን ለማጠናከር የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ የመቀንጨር ምጣኔን ከመቀነስ አኳያ እየሰራች ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብርና ምላሽ አጠቃላይ ልምድና በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ቀርበዋል።

ይህንኑ ተከትሎ 24ኛው የጤና ሴክተር ዓመታዊ ጉባዔ ለሁለት ቀናት በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል። በዚህ ጉባኤ ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለተገልጋዮች ለማቅረብ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል። ከጉባኤው ውይይት የተገኙ ሃሳቦችን እንደግብዓት በመውሰድ እና ተግባራዊ በማድረግ ለማህበረሰቡ ጤና መሻሻልና ለጤና ሥርዓት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።

ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የሚደረገውን ጤና ሥርዓት ለማጠናከርና አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ፤ እንዲሁም፣ በተሻለ ጥራት ለመሥራት እንዲያስችል በ200 የጤና ጣቢያዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ላይ ሥራ መጀመሩ ተገልጿል። የአውሮፓ ህብረት በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም 31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉም የዚሁ በጀት ዓመት መግቢያ ዐቢይ ክስተት ሲሆን፤ የአውሮፓ ህብረት በዩኒሴፍ በኩል ተግባራዊ የሚያደርገው ድጋፍ በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል በጦርነት የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ተግባራት ላይ ውሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የጤና መድህን አገልግሎትን እንደሚያሻሽልበት የታመነበትን ስልታዊ የጤና አገልግሎት ግዢን አስመልክቶ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል። ጥናቱ ስልታዊ የጤና አገልግሎት ግዥ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማሻሻል እንዲሁም ፍትሀዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለዜጎች ለማዳረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ ተነግሯል።

ይኸው የ2015 ዓ.ም በጀት መግቢያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ የተጀመረበትም ነው። ዘመቻው ከታኅሣሥ 13 እስከ 22/2015 በሀገር አቀፍ ደረጀ የተካሄደ ሲሆን፤ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት፣ የአጣዳፊ የምግብ እጥረት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ እደላ፣ የሆድ ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እደላ፣ የሕጻናት የዞረ እግር ልየታ፤ እንዲሁም፣ በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላ ልየታ በቅንጅት የተሰራበት ዓመት ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኮሌራ ምክንያት የሚከሰተውን የሞት ምጣኔ ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የሚያስችል ብሔራዊ የኮሌራ በሽታን የማስወገድ እቅድ (National Cholera Elimination Plan) ተዘጋጅቶ በትግበራው ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዚሁ በጀት ዓመት መጀመሪያ ተካሂዷል። ዕቅዱ በኮሌራ ምክንያት የሚከሰተውን የሞት ምጣኔ 90 በመቶ ለመቀነስ ያለመና በተደጋጋሚ ኮሌራ የሚከሰትባቸውን 118 ወረዳዎች በዕቅዱ ውስጥ ያካተተ መሆኑ ተገልጿል። ከ15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ መቃረቢያ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ሕዝብ የሚገለገልባቸው የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የሕክምና ግብዓት ማከማቻ ተቋማት እና ሌሎችም መውደማቸውን አስታውሰው፤ የጤና ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ከተለያዩ ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እየተወጣ እንደሚገኝና ለጤና አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችንና ሰብዓዊ ርዳታዎችን በተለያዩ ክልሎች የማድረስ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ በጀት ዓመት አጋማሽ መግቢያ 7ኛው ዓለም አቀፍ ኢትዮ-ኸልዝ ጉባኤ እና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ይህንኑ ተከትሎ 4ኛው ሀገር አቀፍ የወባ ፕሮግራም ግምገማ ተደርጓል። በፕሮግራሙ በኢትዮጵያ የተሠሩ የወባን መከላከል ሥራዎችና ሥራዎቹ ያሉበት ደረጃ ተገምግመዋል። ግምገማው በዓለም ጤና ድርጅት የመገምገሚያ መስፈርቶችና በውጭ የግምገማ አካላት በኩል ጭምር እንደተከናወነ ታውቋል። በተመሳሳይ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሆኗል።

በተያያዘም የጤና ሚኒስቴር ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም የሕጻናት አድን ድርጅት ጋር በመተባበር 31 ነጥብ 5 የአሜሪካን ዶላር በሆነ ወጪ በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋዎች የወደሙ የጤና ተቋማትን በተሻለ መልሶ ለመገንባት፣ አቅም ለማጎልበት እና የጤና አገልግሎትን ለማስቀጠል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። 4ኛው ዙር የተቀናጀ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በተለያዩ ክልሎች በዘመቻ መልክ የተሰጠውና ይህንኑ አስታኮ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት እድሜያቸው 14 የሞላቸው ልጃገረዶች እንዲወስዱ የተደረገው በዚሁ በጀት ዓመት አጋማሽ መግቢያ ላይ ነው።

በተመሳሳይ በአፍ የሚሰጠው ሀገራዊ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻም በደቡብ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በናፀማይ ወረዳ፣ ብራይሌ ከተማ በይፋ የተጀመረው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ነው። የእናቶችና ሕፃናትን ጤና ከማሻሻል፣ ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ አሁንም ድረስ ኮሌራን ጨምሮ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባቸው በዚሁ ዘመቻ ወቅት ተነግሯል፡፡

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ሌላው አበይት ክስተት በስዊዘርላንድ (ጄኔቫ) የተካሄደው 76ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ሲሆን፣ በዚህ ጉባኤ የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦችን በማጽደቅ እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል። በኢትዮጵያ መሪነት የተዘጋጀውና ከ80 በላይ ሀገራት ድጋፍ የሰጡበት የውሳኔ ሰነድ (ሬዞሉሽን) ፀድቋል። ሰነዱ ተፈፃሚ እንዲሆን ተጨማሪ ድጋፍ ለማስገኘት ከ90 በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት የጎንዮሽ ፕሮግራም ከማሌዠያ ጋር በመሆን ተከናውኗል።

ከጄኔቫው ጉባኤ በኋላ ደግሞ የ2015 በጀት ዓመት የፀረ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዋሳ ከተማ ተከናውኗል። በመድረኩ በኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል ላይ በተሰሩ በርካታ ሥራዎች ስኬቶች እንደተገኙ ተጠቁሟል። ይሁንና በተገኙ ስኬቶች በመርካትና በመዘናጋት ሳቢያ ችግሩ አሁንም መቀጠሉ ተጠቅሷል። በዓመቱ 11ሺህ ወገኖች በበሽታው ሕይወታቸውን ማጣታቸው፤ 8ሺህ 300 ሰዎች አዲስ በኤች አይ ቪ መያዛቸው፤ ከነዚህም ውስጥ 69 በመቶዎቹ ከ15 እስከ 30 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸው ተመላክቷል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የድንገተኛ ጤና ምላሽ ሥርዓትን በማጠናከር የጤናውን ዘርፍ የመቋቋም አቅም የሚያጎለብት የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ መደረጉ ተገልጿል፡፡ፕሮጀክቱ የማይበገር የጤና ሥርዓትን ለመገንባት (USAID Health Resilience Activity) በዩኤስአይዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር የአምስት ዓመት ፕሮጀክት መሆኑም ታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ያደራጀው የምግብ ላቦራቶሪ በዓለም አቀፍ በተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶች መሠረት በኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ተገምግሞ እውቅና ያገኘው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ፍፃሜ ላይ ነው። የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ቲቢ እና ወባ ጫናን ለመቀነስ የሚረዱ ሶስት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከፈረንሳይ መንግሥት ግሎባል ፈንድ ጋር የድጋፍ ስምምነት የተደረሰውም በዚሁ ጊዜ ነው። ፕሮጀክቶቹ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፤ APOPO፣ REACH Ethiopia እና የጤና ልማት እና ፀረ ወባ ማኅበር በኩል እንደተተገበሩም ታውቋል።

ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኋላ ደግሞ የ2015 ዓ.ም የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃል ኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ዓመታዊ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ በምግብና በሥርዓተ ምግብ ትግበራ ማስፋፋት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ ቢሆንም፣ የሥርዓተ ምግብ ችግርን መፍታት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ተገልጿል። በተለይ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ፣ የምግብ ዋጋ ንረት፣ ድርቅና ከግብዓት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች የምግብና የሥርዓተ ምግብ ችግሮችን እንዳባባሱ ተጠቁሟል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሀገር ውስጥ የክትባት ምርትን አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ ሁለት ደንቦችን ያጸደቀውም ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኋላ ነው። በዚህም የሰው ክትባት ለማምረት የሚቋቋመውን የሺልድቫክስ (ShieldVax) ኢንተርፕራይዝ፣ ነባሩን ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት (NVI) እና አዲስ የሚቋቋመውን የሺልድቫክስ (ShieldVax) ኢንተርፕራይዝን በማካተት እንዲቋቋም የቀረበው የኢትዮ-ባዮፋርማ ግሩፕ የማቋቋሚያ ደንቦች ጸድቀዋል።

ከዚሁ በተጓዳኝ ለቀጣይ 7 ዓመታት የሚተገበር የቲቪ፣ ሥጋ ደዌ እና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች ስትራቴጂክ እቅድ እና ግብ ቫሊዴሽን አውደ-ጥናት ተካሂዷል። እንደ ጦርነት፣ ኮቪድ እና የተፈጥሮ አደጋ ያሉ ተግዳሮቶች በማጋጠማቸው ምክንያት የቲቢ እና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች ጫና እንዲጨምር በማድረጉ ብሔራዊ ስትራቴጂክ እቅዱ እንዲከለስ መደረጉም ተጠቁሟል።

ሌላውና ዋነኛው ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኋላ የተከናወነው ዐቢይ የጤና ዘርፍ ተግባር ‹‹NEXT GENRATION HELATH›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የተካሄደው ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ሲሆን፣ አውድ ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የደረሰችበትን እምርታ በሚገባ አሳይቷል። ወደፊት የምትደርስበትን የጤና ሁለንተናዊ እድገትም አመላክቷል። የተለያዩ አቅሞችን በማቀናጀት የጤና ሥርዓቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል። አውደ ርዕዩን ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች በተቋም፣ ቡድንና ግለሰብ ደረጃ በርካታ ሰዎች እንደጎበኙትም ተነግሯል። የውጭ ሀገር እንግዶችም በተመሳሳይ አውደ ርዕዩን ጎብኝተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ወቅት የኮሌራ ወረርሽኝ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ስለመከሰቱም ተነግሯል። በአፍ የሚሰጠው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻም በሲዳማ ክልል ተጀምሮ፤ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች 111 የኮሌራ ሕክምና መስጫ ማዕከላት ተዘጋጅተው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። በዚህም በ41 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወረርሽኙን መቆጣጠር ተችሏል። በነዚህ ማዕከላትም በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በ2015 በጀት ዓመት መገባደጃ በክረምት የበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ መርሀ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 10ሺህ 400 ዩኒት ደም መሰብሰቡም ተገልጿል። የአፍሪካ ቲቢ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ጉባኤም “One Africa TB Submit” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ጉባኤው የአፍሪካ የቲቢ መከላከልና መቆጣጠር ጥረትን ለማጠናከር፣ ብሎም በቀጣይ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ያገዘ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈ 73ኛው የአፍሪካ አህጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ በቦትስዋና (ገባሮኒ) በዚሁ በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ተካሂዷል። በዚህ መድረክ ሁሉም አባል ሀገራት ድጋፍ የሰጡበት የተለያዩ የውሳኔ ሰነዶች (Resolution) ፀድቀዋል። የዲያግኖስትክ፣ ላቦራቶሪ አገልግሎትና ሥርዓት ስትራቴጂ፣ የህብረተሰቡን ጤንነትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሴክተሮች ትብብር ስትራቴጂ፣ በፀረ ተህዋሲያንና ጀርሞች መላመድ ላይ ሀገራዊ ዕቅድ ትግበራ ክትትል ማፋጠን ስትራቴጂ እና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ የማህበረሰብ ጥበቃና ጠንካራ ሥርዓትን መገንባት አህጉራዊ ስትራቴጂ በመድረኩ ቀርበው የጸደቁ ዋና ዋና የመፍትሔ ሃሳቦች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውና በመጀመሪያ ደረጀ የጤና አሃድ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጉባኤም የተካሄደው በዚሁ በጀት ዓመት ማብቂያ ሲሆን፣ ጉባኤው በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ፣ በጤና ሚኒስቴር እና በኢንተርናሽናል ኢንስቲተዩት ፎር ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር አስተባባሪነት እንደተዘጋጀ ተነግሯል። ጉባኤው የተዘጋጀው ሁሉም ሀገራት ጥራት ያለው እና ፍትሃዊ የመጀመሪያ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ መሆኑም ታውቋል።

የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ እና የመረጃ አያያዝን ለማዘመን የጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራበት የሚገኘውንና “ፋይዳ” የተሰኘውን የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በጤናው ዘርፍ ውስጥ አካቶ ለመሥራት ከስምምነት ላይ የተደረሰበትም ሆኖ ነው የ2015 በጀት ዓመት የተጠናቀቀው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You