
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ውጤታማ መሆኗን መንግሥት ሲገልጽ ቆይቷል፤ የስንዴ ልማቱ ሀገሪቱ ስንዴ ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያዳነም ሆኗል። የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ሀገሪቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ለጎረቤት ሀገሮች ገበያ እንድታቀርብ አስችሏታል።
የስንዴ ልማቱ ስኬታማነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተመሰከረለት ስለመሆኑም መረጃዎች ያመለክታሉ። የአፍሪካ ልማት ባንክ የስንዴ ልማቱን በወቅቱ ከማድንቅም ባለፈው ለልማቱ ድጋፍ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአሜሪካ የውጭ ግብርና ቢሮ ‹‹በኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ትልቅ እመርታ እያሳየና ምርታማነቱ እየጨመረ ነው፤›› ሲልም ገልጾታል። ይህ የአሜሪካ ተቋም በሪፖርቱ ላይም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2022 እና 2023 ውስጥ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ስንዴን ታመርታለች ብሎ መተንበዩንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የስንዴ ልማቱ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ይበልጥ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት በሚል መጀመሩም ይታወቃል። ይህ ልማት አሁን በሁሉም የአየር ንብረት አካባቢዎች በተለያዩ ክልሎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ በየካቲት 2015 ዓ.ም የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ የመላክ መርሃ ግብርን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ይፋ በአደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ “ባሌ ላይ ያየነው ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው። ምክንያቱም የምናደርገውንና የምናቅደውን በተግባር በአረንጓዴ ዐሻራና በሕዳሴ ግድብ እያሳየን መጥተናል። አሁን ደግሞ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆም ባለፈ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ ያሰብነውን በተግባር ፈፅመን ለኢትዮጵያዊያንና ለዓለም አሳይተናል። ኢትዮጵያ ከስንዴ እርዳታ መላቀቅና ወደ ውጭ መላክ አትችልም ያሉንን ችለን በማሳየታችን ኩራት ተሰምቶናል” ብለዋል።
ለዚህ ስኬት ሁሉም ክልሎች ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ በተለይ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ እና የአማራ ክልሎች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ጠንካራ ሥራ ማከናወናቸውን አስታውቀዋል። በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ችግር ይበልጥ በቁጭት ለልማት የሚያነሳሳና “ኢትዮጵያን ኤይድ” በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንድንሠራ የሚያደርግ ነው ሲሉ አስረድተዋል። በዓለም ላይ የተፈጠረውን የስንዴ ገበያ ችግር ለማቃለልም ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ትወጣለችም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በስንዴ ልማት እየተመዘገበ ያለ ውጤትና እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ስኬታማነቱስ ምን ያህል ዘላቂ ነው? የተገኘውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ምን ዓይነት እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው?
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንዳሉት፤ የመስኖ ስንዴ ልማት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የተጀመረው በአንድ ክልል በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ነበር። አሁን ግን ሥራው በየደረጃው ሰፍቷል። ልማቱም በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል ሁኔታ ተስፋፍቷል። ሰፊ የእርሻ መሬት ላይ በማልማት እንዲሁም ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ጭምር በማብዛት በጥቅሉ ዘጠኝ ክልሎች ላይ መድረስም ተችሏል። በዚህ ደግሞ በ2013/14 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 35 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ልማት ለመሸፈን ተችሏል። ከዚህም 53 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ፤ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
ሀገሪቱ ምቹ የሆነ ሥነ-ምህዳር፣ መሬትና ታታሪ አርሶ አደር ያላት ብትሆንም ስንዴን ከውጭ በማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፣ አጠቃላይ የመስኖ ስንዴ ልማቱ እንደ ሀገር ሲጀመር የመጀመሪያው ግብ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህን ዕቅድ ለማሳካት ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወነው ጠንካራ ሥራ በ2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት መቻሉን ያነሳሉ። በዚህም እንደ ሀገር ለስንዴ ግዢ ይውል የነበረ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ ማዳንና ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ ለሌሎች ግልጋሎቶችና ልማቶች መጠቀም እንደተቻለም ያብራራሉ።
ዶክተር መለስ እንዳሉት፤ የስንዴ ልማቱ ስኬት በመስኖ ስንዴ ልማት ብቻ የመጣ አይደለም፤ በሌሎቹም የእርሻ ወቅቶችም በስንዴ ልማት በተሰራ ሥራም ጭምር ነው። በ2014/15 የምርት ዘመን በመስኖ፣ በበልግና በመኸር 4 ነጥብ 47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ልማት ተሸፍኗል። በዚህም በሦስቱም ወቅቶች ከ154 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ስንዴ ማምረት ተችሏል። የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ በ2016 ዓ.ም በመኸር፤ በበልግና በመስኖ ስንዴ ልማት ሰፊ ሥራ እየተከናወነም እንደሆነ ገልጸዋል።
በመኸር የእርሻ ሥራ ወደ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን ብቻ ለማልማት የታቀደ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ ባለው ሪፖርት ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል። በቀጣይ ቀናት ከዚህ በላይ ማሳካት የሚቻልበት እድሎች አሉ። ይህ ደግሞ በስንዴ ልማት ምርት እንደሀገር ከታቀደው በላይ ስኬት ለማስመዝገብ ያስችላል።
ለበርካታ ዓመታት ከአጠቃላይ በጀቷ ቀላል የማይባለውን መዋዕለ ነዋይ ከውጭ ስንዴ ለማስገባትና ለማጓጓዝ የምታውለው ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ግዙፍ የሚባል የስንዴ ልማት ውስጥ ገብታለች። የተፈጥሮ የዝናብ ወቅትንና ኋላ ቀር የእርሻ ሥርዓትን ለዘመናት የሙጥኝ ብለው የሚያለሙ አርሶ አደሮቿን ከዚህ ልማድ ለማውጣትም ‹‹የበጋ ፣ የመስኖና የመኸር ስንዴ) በተሰኘ የልማት ፕሮግራምም እንዲያመርቱ እያለማመደች ትገኛለች የሚሉት ዶክተር መለስ፤ ይህንን ሥራ ለማጠናከር እንደ መንግሥት የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች የውሃ ፓንፖችን፤ የመስኖ ውሃ አቅርቦትና መሠረተ ልማት … ወዘተ መሰል ድጋፎችን በማድረግ ጭምር ሥራውን ማስፋቱን ተናግረዋል። በዚህ ደግሞ በዓይን የሚታይ የስንዴ ምርት ስኬት መመዝገቡን ያነሳሉ። በተገኘው ስኬት በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ጭምር ዕውቅናንና አድንቆት እየተገኘ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
የፖለቲካል ምጣኔ ሀብት ተንታኝና ምሁሩ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን እንዳሉትም፣ የስንዴ ልማት ሀገሪቱ ካላት መልክአ ምድርና የሰው ኃይል አንጻር የተሻለ ምርት ማስገኘት የሚያስችል ነው። የስንዴ ፍጆታዋን በራሷ ምርት መሸፈን የምትችልበት ብዙ ዕድል አላት። ለዚህም ማሳያው በእነዚህ ሦስት ዓመታት በሠራችው ሥራ ምን ያህል ማምረት እንደቻለች የተመላከተው ነው በማለት የዶክተር መለስን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ ይሰጣሉ።
በስንዴ ልማቱ ላይ በርካታ ማነቆዎች ስለመኖራቸው ሚኒስትር ዴኤታውም አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የግብዓትና ፋይናንስ ተደራሽነት፣ የገበያ ሥርዓት ከፍተቶች፣ የምርምርና የኤክስቴንሽን አገልግሎት ውስንነቶች፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ኋላቀር የአመራረት ዘዴ፣ በተለይ አሁን ላይ አርሶ አደሩን እየፈተነ ያለው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት፣ ድርቅ፣ በመኸር እና መስኖ ልማት ላይ እየተከሰተ ያለው የግሪሳ ወፍ … ወዘተ የስንዴ ልማቱ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች መሆናቸውን ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ የሀገሯን ዜጋ ብቻ ሳይሆን የምትመግበው ጎረቤቶቿን ጭምር ነው። ጅቡቲ፤ ሱማሌ ላንድ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ኤርትራ በርካታ ምርቶችን ከኢትዮጵያ ይወስዳሉ የሚሉት ዶክተር መለስ፤ ሀገራቱ ምርቶችን ከሀገሪቱ በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው በሕገ ወጥ መልኩ እንደሚያገኙም ይገልጻሉ። ይህ ደግሞ የልማቱ ውጤት እንዳይታይ ከማድረጉም በላይ የተስተካከለ የግብይት ሥርዓት እንዳይኖር ማድረጉን ያነሳሉ።
በሌላ በኩል ሀገሪቱ ዝቅተኛ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፤ ከዝናብ ጥገኝነት ያልተላቀቀ አርሶ አደር ያለባት በመሆኗ ምርትና ምርታማነቱ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ሊያድግ አልቻለም የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ፣ በመሆኑም ከራስ ፍጆታ ያለፈ ትርፍ ምርት በማምረት ለገበያ ከማቅረብ አኳያ የሚጠበቀውን መዋቅራዊ ሽግግር በሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት ካለመቻሉም በላይ የሀገሪቷን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደማይቻልም ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በበጋም ሆነ በመኸር አለያም በመስኖ እየተመረተ ያለው ምርት ይበል ያሰኛል። ሆኖም እያንዳንዱ የምርት ሂደት ግን መፈተሽ ይኖርበታል። ከሚፈለገው አንፃር ምን የተገኘ ነገር አለ? ሀገሪቱ የሯሷን ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ምን ያህል ምርት አምርታ ወደ ውጭ መላክ ትችላለች? አርሶ አደሩ ምን ያህል እሳቤውን ተቀብሎታልና አስርጾታል? የሚሉትና መሰል ጉዳዮች መልስ ማግኘት አለባቸው። በማንኛውም ጉዳይ ውስጥ የገበሬውን ድካም ማየት ይገባል።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገሮች መካከል በስንዴ ምርቷ በቀዳሚነት ትታወቃለች። በዓመት ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ትሻለች። ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ ለምታስገባው ስንዴም ከ700 ሚሊዮን ዶላር እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ታወጣም ነበር። እናም ይህንን እልባት ለመስጠት የስንዴ ልማት ላይ አተኩራ እየሠራች ትገኛለች። በዚህም የዜጎችን የስንዴ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ከራሷ ፍጆታ የተረፉትን ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብና ከውጭ መግዛትን እንደምታስቀር ይታመናል። ይህም ደግሞ ባለፉት ዓመታት የታየ ሀቅ ነው።
መረጃዎች እንዳሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ በጀመረችው ሀገራዊ የስንዴ ልማት እ.ኤ.አ በ2020 በመስኖ ስንዴ ልማት ብቻ ይሸፈን የነበረው 117 ሺህ ሄክታር ነበር። ይህ አሃዝ አአአ በ2021 ወደ 672 ሺህ ሄክታር፣ እአአ በ2022 ደግሞ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ብሏል። በዚህም በየዓመቱ የሚገኘው ምርትም እየጨመረ መጥቷል። ለአብነት እአአ በ2022/23 የምርት ዘመን በመስኖ፣ በበልግና በመኸር የእርሻ ወቅቶች 4 ነጥብ 47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ በመሸፈን ከ154 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ተገኝቷል።
የስንዴ ምርት ዘርፍ ትልቅ እመርታ እያሳየና ምርታማነቱ እየጨመረ ነው። ይህንን እምርታ ለማስቀጠልም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች መፈታት ይኖርባቸዋል። ችግሩንም ለመፍታት እንደ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው፤ ለእዚህም በኤክስቴንሽን ድጋፍ፣ የመስኖ ልማቱን አጠናክሮና አስፋፍቶ በማስቀጠል፣ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ የእርሻ ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች በማቅረብ በኩል የተከናወኑ ተግባሮችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
በበጋና በክረምት የሚደረገውን የልማት እንቅስቃሴ ቀጣይነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ምርጥ ዘሮች፣ ማዳበሪያና ሌሎች ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ካላቸው ነባራዊ የዋጋ መጨመር የተነሳ ለገበሬው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበትና የሚፈልገውን ያህል ግብዓት የሚያገኝበት እድል መፈጠሩም ሌላው ድጋፍና የመፍትሔ አቅጣጫ ተደርጎ እንደሚወሰድ ይናገራሉ።
አቶ ሸዋፈራሁ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ልማቱን ዘላቂ ለማድረግ የመጀመሪያው መፍትሔ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር ነው። አርሶ አደሩ እንደልቡ ተንቀሳቅሶ መሥራትና ግብዓቶችን ማግኘት እንዲችል ከሁሉም በላይ የሰላም ጉዳይ ዋጋ ሊሰጠው ያስፈልጋል፤ መንግሥት ሰላም መፍጠሩ ላይ ተግቶ ሊሠራ ይገባል።
የስንዴ ልማቱ ሥራ በዘመቻ የሚደረግና ለፖለቲካ ፍጆታ ሥራ የሚውል መሆን የለበትም ሲሉም ገልጸው፣ በዚህ አይነት መልኩ የሚሰራ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መቀዝቀዙ አይቀርም ብለዋል። እናም ከዚያ ይልቅ አርሶ አደሩ ሊያበረታታ የሚችልበትን ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል። አሳምኖ ወደ ተግባሩ እንዲገባ ማድረግ ይገባል። አምኖበት ከሠራ ደግሞ ተጠቃሚና ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚያ ለራሱ ገቢ (ጥቅም) ሲል ሥራውን ቀን ከሌት ጠንክሮ የማይሠራበት ምክንያት አይኖርም ሲሉ ያብራራሉ።
አርሶ አደሩ አስተማማኝ የእርሻ መሬት እንዲኖረው፣ ምርጥ ዘር እንዲቀርብለት፣ የምርት ሽያጭ ሰንሰለቱ ጤናማ እንዲሆንለትም መሥራት ይገባል የሚሉት ኢኮኖሚስቱ፤ አንዳንዴ በኢ-መደበኛ ግብይት ውስጥ ምርቱ ያልፍና መቃቃሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም መታመን አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከደላላው አንስቶ የሀገሪቱን መውጫ ድንበሮች አጥብቆ መቆጣጠር ይጠበቅበታል ብለዋል። አርሶ አደሩ ትርፋማ ከሆነና ውጤቱን ከተገነዘበ ሀገርም ሆነች ሸማቹ ማኅበረሰብ በሁሉም መስክ ስኬታማ ይሆናሉ ብለዋል።
ዶክተር መለስ ስንዴን በስፋት የሚያመርቱት ሀገሮች (ዩክሬይንና ሩሲያ) ችግር ውስጥ በመሆናቸው ዓለም ላይ የስንዴ ምርት እጥረት ገጥሟል ሲሉ ጠቅሰው፣ በተለይ ከነዚህ ሀገሮች የስንዴ ምርት የሚያስገቡ ብዙ ሀገሮች ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ይህን ዓለም አቀፍ ችግር መሻገር የቻለችው በስንዴ ላይ እየተሠራ ባለው ሥራና በተገኘው ውጤት እንደሆነ ያመለከቱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ስንዴን የማልማቱ ጉዳይ የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። ምክንያቱም አርሶ አደሩ ስንዴን በማምረቱ ሀገር ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ከማዳኑ ባለፈ ሀገርን ከተረጂነት ታሪክ ይታደጋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ስለሆነም ልማቱን ፖለቲካ ማድረጉን ትቶ መሥራት ላይና፤ ለሥራው ጉልበት መሆን ላይ ሁሉም ዜጋ ሊያተኩር እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ከትንታኔው መረዳት እንደሚቻለው፤ ሀገሪቱ በስንዴ ልማቱ ያገኘችውን ውጤት አጠናክራ ካስቀጠለች የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ አልፋ፣ ስንዴን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ትችላለች። ስንዴ ከውጭ ለማስገባት የምታውለውን የውጭ ምንዛሬ ለሌላ የልማት ሥራ ማዋል ትችላለች። በተቃራኒው የስንዴ ልማቱን ዘላቂ ማድረግ ካልቻለች ደግሞ ብዛቱ እያደገ የመጣውን ሕዝቧን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ትቸገራለች።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም