በቢጫ አልባሳት የሚደምቀው አዲስ ዓመት

 እነሆ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ነን፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን አዲስ ዓመት በጉጉት ይጠብቁታል፤ በዓሉን ሕብረታቸውን፣ አንድነታቸውን እና አብሮነታቸውን ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ ይጠቀሙበታል፡፡ በበዓላት ወቅት እየተጠራሩ አብሮ መመገብ፣ ችግረኞችን መርዳት፣ አብሮ ገበታ መቋደስ፣ አብሮነትን የሚያጠናክሩ አለባሳትን መልበስ ለኢትዮጵያውያን መገለጫቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

የዚህ አንድነታቸው መገለጫ ከሆኑት መካከል አለባበሶቻቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በእዚህ የአዲስ ዓመት በዓል ወቅት ሕጻናት፣ አዋቂዎችና ወጣቶች የባህል አልባሳት በመልበስ የበለጠ ደምቀው ይታያሉ፡፡ በዚህ ወቅት እንኳን የሰው ልጅ ሰማይ ምድሩ ያሸበርቃልና ኢትዮጵያውያንም በአልባበሶቻቸው ያሸበርቃሉ፡፡ የበዓሉ ዕለት ከሕጻን እስከ አዋቂው ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ በባሕላዊ አልባሳት ይዋባል፡፡ በሕብረት ሆነው ‹‹አበባየሆሽ›› እያሉ ባሕላዊ ሕብረ ዜማቸውን ሲያዜሙም ዋና መድመቂያቸው አልባሳታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በአዲስ ዓመቱ ብቻ ሳይሆን ከበዓሉ ቀደም ብለው ባሉ ቀናትም የበዓሉ መምጣት ጠቋሚ የሆኑ የበዓሉ አድማቂ አልባሳትን ይለብሳሉ፡፡ በየዓይነቱ ከያሉበት ብቅ ሲሉም ሕብረ ብሔራዊነታቸውን ያሳያሉ። እናም በዓሉን በዓል የሚመስለው ምግብና መጠጡ ብቻ ሳይሆን ሰዎች የሚለብሷቸው ባሕላዊ አልባሳት ጭምር ናቸው፡፡ በተለይ አሁን አሁን የሀገራችንን ልብሶች እየዘመኑ በተለያዩ ዲዛይኖች ተሰርተው ከሊህቅ እስከ ደቂቅ ላለው የሕብረተሰብ ክፍል መዋቢያና የአብሮነታቸው መገለጫ እየሆኑ ናቸው፡፡

አዲስ ዓመት አብረው ከመጫወቱ፤ ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ልጆች ብቻ ሳይሆኑ አዋቂዎችም የሚሰባሰቡበትና የተለየ አልባሳታቸውን የሚያሳዩበት ልዩ የመሰባሰቢያ ዕለት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ የሀገራችን ዲዛይነሮች ምን ያህል ብቁ እንደሆኑ ይታይበታል፡፡ ምክንያቱም ብቃትና ላቅ ያለ ችሎታቸውን የሚያሳይ ባህላዊ አልባሳት ሰርተው በበዓሉ አጋጣሚ ለሰዎች ያደርሳሉ፡፡ ሰዎችም በጥሪያቸው ወቅት ተውበውበት ይወጣሉ፡፡

አዲስ ዓመት የፋሽን ዘርፉን ለማሳደግ የሚኖረው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዕለቱ አልባሳቱ ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ዘመነኛ ሆነው ከመስራታቸው በላይ የጥለታቸው፣ የጥልፋቸው፣ የቀለማቸው እና የዲዛይናቸው ውበት ለዓይን የሚስብና ማራኪ በመሆኑ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ተለብሰው ሲታዩ በእጅጉ የሚያኮሩ ናቸው፡፡

እንደ በዓሉ ዓይነት የሚለበሱትም ልብሶች የሚለያዩ ሲሆን፤ የልብሶቹን ዲዛይን ለመሥራት ልብሱንና ጥልፉን መመረጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ነው የሙያው ባለቤቶች የሚናገሩት፡፡ ለአብነት አዲስ ዓመት ሲመጣ ከሌላው በዓል የሚለይበት የራሱ የሆነ ቀለም ይሰራለታል፡፡ ይህም በአብዛኛው ቢጫ ቀለም ያላቸው ልብሶች መሆናቸውን ባለሙያዎቹ ያብራራሉ፡፡

ለአዲስ ዓመት ማንኛውም ባሕላዊ የሆነ የጥበብ ዓይነት ይመረጣል የምትለው ዲዛይነር ትዕግስት አማረ ስትሆን፤ ቀለሙም ሆነ ዲዛይኑ ለባሹ በሚፈልገው መልኩ ሊያሰራው የሚችል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ አሁን ላይ ለአዲስ ዓመት እንደ ፋሽን ሆኖ በብዛት ቢጫ ጥለት ያላቸው ልብሶች ተመራጭ ናቸው። ቢጫ ጥበብ ያለው፣ ቢጫ ጥልፍ ያለው ልብስ በአዲስ ዓመት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ጥበቡ ቢጫ ሆኖ በላዩ ላይ የአደይ አበባ ጥልፍ ይሰራበታል፡፡

በተጨማሪም የተሸመኑ ቢጫ ልብሶች ወይም ነጩን ልብስ በኬሚካል ነክሮ ቢጫ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ጠቁማ፤ ይህም እንደየለባሹ ዓይነትና ፍላጎት የሚለያይ መሆኑን ታነሳለች፡፡ ለባሹ የሚፈልገው አይነት ልብስ በትዕዛዝ ማሰራት የሚችል መሆኑንም ትናገራለች፡፡

ዲዛይነሮቹ ከበዓል ቀደም ብሎ ለበዓል ይሆናሉ ያሏቸውን ውብና ማራኪ ዲዛይን ያላቸውን ልብሶች በራሳቸው ፍላጎት ሠርተው ለለባሾቹ እንዲያዩት ያደርጋሉ፤ ያስተዋወቃሉ የምትለው ዲዛይነሯ፤ በሌላ በኩል በለባሹ ፍላጎት መሠረት የሚታዘዙ ልብሶችን ሠርተው በወቅቱ ለማድረስም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ እነዚህ የለባሹን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ልብሶች በብዛት ተሰርተው እንዳይቀመጡ ልብሶቹ ወቅታዊ ስለሆኑ ከትዕዛዝ ውጭ ሲሰሩ ገዥ ስለማያገኝ ነው ትላለች፡፡

እንደልምድ ሆኖ በዓል ሲቃረብ (የተወሰኑ ቀናት ሲቀረው) ነው ለበዓል የሚያስፈልጉት ልብሶች ትዕዛዝ የሚበዛው የምትለው ዲዛይነሯ፤ አብዛኛው ሰው በዓሉ ስሩ ሲደርስ ልብስ ለማሰራት ይነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት በበዓል በትዕዛዝ በሚሰሩ ልብሶችን ሳቢያ ሥራ ይደራረባል፤ በጥድፊያ የሚሰራ ሥራ ደግሞ ለባሹን የሚያስደስት አይሆንም፡፡ ቅሬታን ሊፈጠርም ይችላል፡፡ ስለዚህም ለባሽ የበዓል አልባሳትን ሲያስብ ቀድሞ ማዘዝ እንዳለበት ትመክራለች፡፡

‹‹እነዚህ ልብሶች ወቅቱን ጠብቀው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ስሜት ይፈልጋሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሰዎች ስሜታቸው ጥሩ ሲሆን ነው የበዓል ልብሶች ለማሰራት የሚመርጡት። ይህ ደግሞ ሁለቱንም ስሜት ለማጣጣም ያስቸግራል›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ ለባሹ በአልባሳቱ መደሰት ከፈለገ ለበዓሉ የሚፈልገውን ልብሶች ከበዓል በፊት ቀደም ብሎ ማዘዝ ቢችል መልካም እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ለበዓሉ ሁሉም ሰው በአቅሙ ልክ የሚሸመተው ዓይነት ልብሶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሳ፤ አሁን ላይ የበዓል ወቅት የተቃረበ ቢሆንም ከሌላ ጊዜ አንጻር ገበያው የተቀዛቀዘ መሆኑን ታነሳለች፡፡

ሌላኛው ዲዛይነር ደስታ እሸቱ ስትሆን፤ እርሷም ከአዲስ ዓመት አልባሳት ጋር በተያያዘ የምትለው አላት። ልምዷን በመጠቀም ለአዲስ ዓመት የሚሆኑ ልብሶችን ለባሹን በአማከለ መልኩ በዓሉን ይመጥናሉ ብላ የምታስባቸውን ታዘጋጃለች፡፡ ሥራዎቿን ደግሞ ቀደም ብላ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ታስተዋውቃለች። ይህንን ማድረጓ ደግሞ ለለባሹም ሆነ ለእርሷ ብዙ አማራጮችን እንደሚሰጣት ትናገራለች፡፡ ለለባሹ ለበዓል የሚፈልገው ዓይነት ልብስ እንዲሰራለት የሚመርጠው ነገር ያገኛል፤ እርሷ ደግሞ አስባበት ዲዛይን አድርጋ እንድትሰራ እንደሚያግዛት ታስረዳለች፡፡

የልብሱን ቀለምም ሆነ ዲዛይን በሚፈልገው መልኩ ይመርጣል፡፡ እኛም እንደባለሙያ አስፈላጊውን ምክረ ሃሳብ እንለግሳለን፡፡ የበዓል ልብስ ማሰራት የሚፈልጉ ሰዎች ቀደም ብለው ትዕዛዙን ቢሰጡ የሚፈልጉት ዓይነት ዲዛይን በሚፈልጉት ልክ በጥራት እንዲሰራላቸው ያስችላልም ትላለች፡፡

ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ ለአዲስ ዓመት ሆነ ለማንኛውም ጊዜ ልብስ ለመግዛት ወይም ለማሰራት የሚፈልገው ሰው ሙያዊ እውቀት ባይኖረውም የሚፈልገው የልብስ ዓይነት ከአሰራሩ ጭምር ጠይቆ በሚገባ አውቆትና ተረድቶት መርጦ ማሰራት (መግዛት) ይችላል፡፡ ይህም አንደኛው ልብስ ከሌላኛው የሚለይበትን ነገር መረዳትና ጠንቅቆ እንዲያውቅ ይረዳዋል፡፡ ካወቀ በኋላም የልብሶችን ዓይነትና ዲዛይን ስለሚለይ የሚፈልገው ለመምረጥ አይቸገርም፡፡ ለባሹ ያለምንም ስጋት የፈለገውን ልብስ መልበስ ይችላል፡፡ ዲዛይነሩም ሙያው እያሳደገ ገቢ እያገኘ እንዲሄድ ያስችለዋል፡፡

ዲዛይነሩ አንድ ነገር መውሰድ አለበት የምትለው ዲዛይነሯ፤ የሕዝቡ አገልጋይ ነውና የለባሹን ሃሳብ በመገንዘብ ያሉትን ልብሶችና ዲዛይኖች በማስመረጥ ፍላጎቱን ሊያሟላለት ይገባል፤ ይህ ደግሞ ሙያ ኃላፊነትን መወጣት ነውና ይህንን እናድርግ ስትል ትመክራለች፡፡

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You