የሀገራዊ ምክክሩ ተስፋና ተግዳራቶች

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። ይህንን ሀገራዊ የውይይት መድረክ የሚያመቻችና የሚመራ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሙ ወደ ሥራ ከገባ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ኮሚሽኑ በተለይ በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ እና የተባባሪዎች ሥልጠና ሥራን እያገባደደ ይገኛል። እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን በተለያዩ አማራጮች የመቀበል ሥራ እያከናወነ ነው። ከዚህ በመነሳት የሀገራዊ ምክክሩ በብዙዎች ዘንድ በአንድ በኩል ተስፋን በሌላም በኩል ካልተሳካ በሚል ስጋትን ይዞ መጥቷል፡፡ ከዚህ አንጻር የሚነሱ ሃሳቦችን በመንተራስ የሀገራዊ ምክክሩ ተስፋና ተግዳሮት ምን ምን ናቸው ስንል ለዘርፉ ቅርበት ያላቸውን ምሁራን አነጋግረናል?

እንደ የሰላም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶክተር) ትንታኔ፤ የአንድ ሀገር ህልውና መሠረቱ የሕዝቦች አንድነት እና መተማመን ነው። ስለዚህ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የሚያመጣ፤ በሕዝቦች መካከል መተማመን የሚፈጥር ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ሕዝብ በሰላም ተከባብሮ አብሮ ይኖራል። አንድ ሰው በተለያየ ቦታ ተዘዋውሮ ሀብት ማፍራት፣ አብሮ መኖር ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትም ሀገርን በሰላም ያስተዳድራል፤ ሕዝቡን ለልማት አስተባብሮ እድገት ያመጣል። እንዲሁም ኅብረተሰቡ አንድ የስነልቦና ውቅር ተላብሶ የሀገርሩን ሉዓላዊነትና አንድነት ያስከብራል። የውጭ ጥላትን በአንድነት ይመክታል።

ምክክሩ ሰላምን ያሰፍናል። እንደ ሀገር በአፈሙዝ ችግሮች ካልተፈቱ ከሚል ኋላቀርና ፋሽን ካለፈበት አስተሳሰብ ተላቆ ባልተለመደ መልኩ ብቸኛው የችግሮች መፍቻ ቁልፍ የሆነውን ሰላምን በሰላማዊ መንገድ በንግግር፣ በምክክር፣ በድርድር፣ በውይይት ማምጣትን የፖለቲካ ባህል ያደርጋል። በሰላማዊ መንገድ የተገኘ ሰላም ደግሞ ዘላቂ ልማትን ያሰፍናል። እንዲሁም በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች … እልባት ያገኛሉ። ከዚህ ባለፈ “የራሷን ችግር በራሷ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የቻለች ሀገር” ተብላ ከቀጣናው አልፎ በመላ ዓለም እንደ ተምሳሌት የሚያስጠቅሳት እንደሆነ ኮምሽነሩ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ መብራቱ አለሙ (ዶክተር) በበኩላቸው የኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ሃሳብን ይጋራሉ። እንደ መብራቱ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ ግጭቶች፣ ጦርነት፣ አለመግባባት በዘላቂነት ሲከሰት፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተለይ የፖለቲካ ተዋናዮች በምክክርና በንግግር የችግሩን መንስኤ ከመሠረቱ ለይተው በዘላቂነት ችግሩን የሚፈቱበት ሂደት ነው። ይህ ሂደት የመጀመሪያ ዓላማው ግጭትን ማስቆም ነው። ሁለተኛው ደግሞ “በመንግሥትና በማኅበረሰቡ መካከል ማኅበራዊ መስተጋብሩ ላልቷል” ተብሎ ከታመነ፤ መስተጋብሩን መልሶ ለመገንባት እና ለማጥበቅ የሚደረግ ምክክር ነው። በዚህ ምክክር ችግሮችን በጠመንጃ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይትና በድርድር መፍታት የሚቻልባቸው አማራጮችና ልምዶች ይቀሰማሉ ይላሉ።

የአንድ ሀገር ግንባታ የሚወሰነው በተቋማት ግንባታ ላይ ነው። በመሆኑም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አንድ ትልቅ የሀገር ምሰሶ ተቋም ነው የሚሉት መብራቱ (ዶ/ር)፤ በሀገራዊ ምክክሩ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ፣ የተለያዩ ሕጎችና ፖሊሲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚተዳደሩባቸው አዋጆች፣ ኢኮኖሚ የሚመራበት የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሥርዓት፣ ገበያ የሚመራበት የገበያ ሥርዓት ወዘተ በሙሉ ይፈተሻሉ ተብሎ ይታመናል። በተለይ ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 30 ዓመታት ጠንካራ ጎኑና ጉድለቱ ምንድነው? ወደ ፊት መሻሻል ያለበት የትኞቹ አንቀጾች ናቸው? በሚል በጥልቀት የሚታይበት መድረክ ነው።

ስለዚህ አሁን በሀገሪቱ ላለው ሠላም መደፍረስ፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ … ወዘተ መሠረታዊ ችግሮች “መንስኤው መዋቅራዊ ወይስ ሥርዓታዊ ነው” የሚለውን ጥልቅ ጥናት በማጥናት የመፍትሔ ሃሳብ የሚቀርብበት መድረክ ነው። በዚህ ሀገራዊ ምክክር ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ባሻገር በቀጣይ ሀገሪቱ በሰላም የምትተዳደርበት፣ ወደፊት በልማት የምትራመድበት ስንቅ የምትሰንቅበት፤ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ አንድነት የሚበጁ የመፍትሔ ሃሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ ይታመናል ብለዋል።

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፤ በየቦታው የሚፈነዳዱ ግጭቶች፣ ተስፋ መቁረጥ ወይም “አይሆንም፣ አይሳካም” የሚል አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲሁም ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ከታች ወደ ላይ ሀገር በቀል እውቀትን መሠረት አድርጎ፤ ከላይ ወደታች ደግሞ የሊህቃኑን፣ የፖለቲካ መሪውን እንዲሁም ወደ ጎን የሚዲያ፣ የምርምር ወዘተ ግብዓትን በሙሉ በመጠቀም የነበረባቸውን አለመግባባት በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትተው ሰላማቸውን ያጸኑ፤ ኢኮኖሚያቸውን ያሳደጉ ርቀን ሳንሄድ በአፍሪካ በርካታ ሀገራት አሉ። ለአብነት ቤኒን በዚህ መሠረት ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል ባለፈ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው መንግሥት በገዛ ፈቃዱ ስልጣን እስከመልቀቅ ደርሷል። በዚህም ዛሬ ላይ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ናት። በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ ወዘተ ገጥሟቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት በተደረገው ውይይት በዋናነት የሀገሬው ሕዝብ ባለቤት ስለነበረ በተጨባጭ ተሳክቶላቸዋል።

በተቃራኒው የምክክር ሂደቱ የተኮላሸባቸው ሀገሮች አሉ። ለአብነት ጎረቤታችን ሱዳን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሰላም ለማምጣት ታትራለች። ነገር ግን በገዥው ፓርቲ ወይም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተነሳ በሰላም ችግራቸውን መቋጨት አቅቷቸው ወደ እርስ በእርስ ጦርነነት የገቡበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የመን ሰላም ለማምጣት ስታደርገው የነበረው ጥረት በውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሳይሰምር ቀርቶ መንግሥት አልባ ሀገር እንደሆነች ይናገራሉ።

“በሁለት ጽንፍ ያሉ የነዚህ ሀገሮች ስኬትና ውድቀት የሚያስተምረው የሀገራዊ ምክክሩ ባለቤት የሀገሬው ሕዝብ መሆን እንዳለበት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈለግ ነው” የሚሉት ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፤ ወካይነትና አሳታፊነት የሀገራዊ ምክክሩ የጀርባ አጥንት ነው።

ሆኖም 120 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ እንዲሁም ከ80 በላይ ብሔረሰብ ማሳተፍ አይቻልም። ይህ ተግባራዊ መሆን የሚችለው ኅብረተሰቡ በቂ ውክልና እንዲኖረው በማድረግ፤ የሁሉንም አስተሳሰብ ማንጸባረቅና ማስተናገድ ሲቻል ነው። ሁሉም አስተሳሰቦች መስተናገድና መወከል ግን አለባቸው። ስለዚህ በየትኛውም ሀገር ሕዝብ የሚወከለው በተወካዮቹ ነው። ነገር ግን በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ውክልናው የሃሳብ ውክልና መሆን አለበት። ማለትም ተወካዩ የሀገሪቱን ታሪክ፣ ትርክቶች፣ ቅርስ፣ ገጽታ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የኅብረተሰቡን ሥነ- ልቦና ፣ ወቅታዊ ችግሩን በቅጡ የተረዳ እንዲሁም ለሀገሪቱ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ የሚያፈልቅና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ መሆን አለበት። በጥቅሉ ውክልናው በብሔረሰብ ስብጥር በኮታ ሳይሆን በሃሳብ ውክልና ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ።

መብራቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው አንድ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆን ሊከተላቸው የሚገቡ ዋና ዋና መርሆች እንዳሉ ገልጸው፤ የመጀመሪያው ምክክሩ ገለልተኛ በሆነ አካል መመራት አለበት። ሌላው ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች … ወዘተ የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ መሆን አለበት። ከዚህ አኳያ ምክክሩን ገዥው ፓርቲ ወደራሱ እንዳይወስደው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ሂደቱን የሚመሩት አካላት በሙሉ ገለልተኛ ሆነው መሥራት አለባቸው። በተለይ ኮሚሽነሮች ያላቸው ቁርጠኝነት ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር የትጥቅ ትግል እያካሄዱ ያሉ ኃይሎችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መጥተው በሰላማዊ መንገድ  ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ የሀገራዊ ምክክሩ አንዱ ትልቁ ፈተና እንደሆነ መብራቱ (ዶ/ር) ጠቅሰው፤ እንደሚታወቀው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የትጥቅ ትግል እያካሄዱ ያሉ አሉ። ያለእነዚህ አካላት ተሳትፎ የሚፈለገውን ወይም የሚባለውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ አይቻልም። ስለዚህ እነዚህ አካላት ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ሁሉም የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት አሳስበዋል።

እርሳቸውም አክለው፤ ከሰባቱ አስተባባሪ ከሚባሉ አካላት አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሆነ ጠቁመው፤ ምክር ቤቱ ስለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በየጊዜው ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር ግምገማና ውይይት ያደርጋል። በዚህም ያሉትን ክፍተቶች ለኮሚሽነሮቹ ጭምር ያሳውቃል። ከዚህ አንጻር በተለይ ከተሳታፊ ልየታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ወረዳዎች የአንድ ፓርቲ አባላት በብዛት እየገቡ ያሉበት ሁኔታ አለ። ይህ አንድ ትልቅ ተግዳሮት ነው። ስለዚህ አጠቃላይ ሂደቱን እንዳያበላሽ በጥንቃቄ መሠራትና መስተካከል አለበት በሚለው ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር መተማመን ላይ ተደርሷል። ከዚህ በተረፈ የሚሠሩ ሥራዎች ግልጽና አሳታፊ መሆን አለባቸው። ለአብነት አጀንዳ ልየታ ላይ ተባባሪ አካላትን በማሰልጠን መሳተፍ አለባቸው። ሂደቱን መታዘብ አለባቸው። ይህ ካልሆነ በኋላ መተማመኑ ላይ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ።

ሌላው ሀገራዊ ድርድሩ ውስጥ አንገባም ብለው “ኮከስ ግሩፕ” ያቋቋሙ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እነዚህ ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል። እንዲሁም የምክክር ኮሚሽን አዋጁ ላይ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ፤ ኮምሽነሮቹ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት ባሉበት እንዲያብራሩ ተደርጓል። በዚህም አንሳተፍም ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ“ኮከስ ግሩፕ” ወጥተው ሀገራዊ ምክክሩን የተቀላቀሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ሌሎቹም ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ኮሚሽኑ ያላለሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው። ስለዚህ ውስጥ ገብቶ የምክክር ሂደቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ ሳይታወቅ፤ ውጭ ሆኖ ቁጭ ብሎ ከመተቸትና ከመቃወም ይልቅ፤ በሀሳብ የበላይነት አምኖ ውስጥ ገብቶ ያሉትን ክፍተቶች እያዩ በጋራ ታግሎ እንዲስተካከል በማድረግ ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባ መብራቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) “ሁሉም ኮሚሽነሮች ወደዚህ ሀላፊነት ከመምጣታችን በፊት የራሳችን ገቢና ሥራ የነበረን ነን። ወደዚህ ሀላፊነት ስልጣን ወይም ሀላፊነት ፈልጎ የመጣ የለም። የበኩላችን አስተዋጽዖ ለሀገራችን ለማበርከት ነው። ስለዚህ ነጻና ገለልተኛ ሆነን ለሀገር የሚበጅ፣ በታሪክ ፊት የማያስወቅስ ሥራ ሠርተን ለማለፍ ነው” በማለት፤ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በወንድምነትና በእኩል አይን ነው የምናየው። ሆኖም አይደለም በፖለቲካ ፓርቲዎች በመንትያማቾች መካከል ልዩነት አለ። የሀሳብ ልዩነቶች ለጊዜው ሊኖር ይችላል። ልዩነት ውበት ነው፤ እንደመጥፎ ነገር መታየት የለበትም። በሂደት ነገሮች እየረገቡ መግባባት እንደሚደረስ ያስረዳሉ።

ከዚህ አንጻር ኮሚሽኑ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መድረኩ እንዲመጡ ወርዶ እየሠራ ነው። በዚህም አንሳተፍም ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባልነት (ከኮስ ግሩፕ) ወጥተው ወደ ሀገራዊ ምክክሩ የገቡ እንደ ኦብነግ (የኦሮሞ ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር) የመሳሰሉ ፓርቲዎች አሉ። የዚህ ፓርቲ መሪ ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብ ይዘው መጥተው ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እየሠሩ ነው፤። ከሌሎች ፓርቲዎችም በግለሰብ ደረጃ በጣም ትልልቅ የእውቀት ሰዎች አብረው በጋራ እየሠሩ እንደሆን ኮምሽነሩ ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት ኮሚሽነሩ አሳስበው፤ በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ለጥፋትም ሆነ ልልማት ትልቅ ጉልበት አላቸው። ለአብነት ሩዋንዳ ወደ የእርስ በእርስ እልቂት የገባችው በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም በተላለፈ የጥላቻ ንግግር ነው። ስለዚህ ሚዲያ በተለይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ጥላቻን፣ መከፋፈልን የሚዘሩና ሀሰተኛ ዜናዎችን በመመከት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት አለበት። በተቃራኒው ደግሞ በሕብረተሰቡ ውስጥ ተስፋን የሚያጭሩ፣ የሰላምን ፈና የሚያበሩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ቀን ከሌት ማስተጋባት፣ ማስተማር አለበት።

እንዲሁም የምክክሩን ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ ፋይዳ፣ ወዘተ በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ በዘመቻ ሳይሆን ሰርክ ማስተማር አለበት። ከጦርነት አዙሪት ተላቀን ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን ስለ ሰላም ባህል ግንባታ በተመለከተ ምሁራንን በመጋበዝ ጭምር ማን ምን መሥራት እንዳለበት ማስገንዘብ አለበት። በሌላ በኩል የሀሳብ ልዩነት ለአንድ ሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና ይጫወታል። ስለዚህ በሀገራዊ ምክክሩ የሚንጸባረቁ የሀሳብ ብዝሀነትን ለህብረተሰቡ በማድረስና በማሳየት ሚዲያ ከፍተኛ ሚና መጫዎት አለበት።

ሌላው የኃይማኖት ተቋማት በጸሎት ሀገርን መርዳት፣ በምክር ሕብረተሰቡን ማረቅና ማስተማር አለባቸው። በተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን በከፍተኛ ሁኔታ እያገዙ ይገኛሉ። አሁንም እርዳታቸውን አጠናክረው በማስቀጠል በምርምራቸውና በጥናታቸው ሁሉ የሀገራዊ ምምክሩን አስፈላጊነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ልቦና እና አዕምሮ እንዲሰርጽ የበኩላቸውን ሚና መጫዎት አለባቸው። በጥቅሉ በየደረጃው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መጫዎት ከቻለ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከገጠማት ችግር ትሻገራለች፤ ከታቀደው በላይ ወደ ከፍታው ማማም ትወጣለች። ሀገሪቱም በጦርነት፣ በረሃብ፣ በችግር፣ በድርቅ … ወዘተ ከምትታወቅበት መጥፎ ገጽታ ወጥታ በቅርቡ በልማት፣ በእድገት፣ በሰላም… ወዘተ የምትታወቅበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተወያይቶ በመፍታት ሀገራዊ መግባባት ማምጣት ካልተቻለ፤ በሰላማዊ መንገድ ችግራቸውን መፍታት አቅቷቸው ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ገብተው የወደሙ ሀገሮች (የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ ወዘተ) እጣ ፈንታ ሀገሪቱ ሊገጥማት እንደሚችል አሳስበዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You