እንደምን ሰነበታችሁ… ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ካስተናገደቻቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ አስቃኝቻችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከነዚህ ታሪካዊ ድርጊቶች መካከል አንዱ ስለሆነው፣ “የጀኔራሎቹ መፈንቅለ መንግሥት” በመባል ስለሚታወቀውና ከ30 ዓመታት በፊት (ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም) በገዢው ፓርቲ (የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ – ኢ.ሰ.ፓ) ሊቀመንበርና በአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ላይ ስለተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ላካፍላችሁ፡፡ ምንም እንኳ የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ደም አፋሳሽ የነበረ ቢሆንም፤ አስቂኝና አስገራሚ የሆኑ ጥቂት አጋጣሚዎችም ነበሩት፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት “የጦር ኃይሎች፤ የክብር ዘበኛ፤ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ” መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከዙፋናቸው አውረደ፡፡ ስያሜውንም “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ብሎ በመለወጥ ስልጣን ይዞ ኅብረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለቲካ- ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ አገር መግዛት ጀመረ፡፡
የመሰረተ ልማት አውታሮችን፤ በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ባሻገር የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስራትና ስርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በተሸነፈ ቁጥር ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃ/ ማርያም የሚወስዱት ርምጃ፤ የሊቀ መንበሩ ግትርነት፤ እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው የጦሩ መሪዎች በሊቀ መንበሩ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው፡፡
በእርግጥ የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተደረገው በ1981 ዓ.ም ይሁን እንጂ የመፈንቅለ መንግሥት ሃሳቡ ከተወጠነ ቆይቷል፡፡ የድርጊቱ ዋነኛ ጠንሳሾችና ጀማሪዎች የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ እና ከአየር ኃይል አዛዥነት ተሽረው የኢንዱስትሪ
ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ናቸው፡፡
ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሄዱ፡፡ በዕለቱም የመጨረሻውን የአድማ ስብሳባ ለማድረግ የተመረጠው ቦታም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ነበር፡፡ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ (የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም)፤ ሜጀር ጀኔራል ኃይሉ ገ/ሚካኤል (የምድር ጦር ዋና አዛዥ)፤ ሜጀር ጀኔራል አምሃ ደስታ (የአየር ኃይል ዋና አዛዥ)፤ ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ (የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ)፤ ሜጀር ጀኔራል ወርቁ ዘውዴ (የፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ)፤ ሜጀር ጀኔራል አብዱላሂ ዑመር (የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ)፤ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ (የኢንዱስትሪ ሚኒስትር)፤ ሜጀር ጀኔራል አበራ አበበ (የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ)፤ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ትርፌ (በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መኮንን)፤ ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ አበበ (የጦር ኃይሎች አካዳሚ ዋና አዛዥ)፤ ኮሞዶር ኃይሌ ወልደ ማርያም (በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የእቅድና ፕሮግራም መምሪያ ኃላፊ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ቢሮ አጠገብ ባለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰቡ፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የጦሩ ባለስልጣናት ይሁኑ እንጂ፤ ከየጦር ክፍሎች የተመለመሉ አዛዦችም የሚሰጣቸውን ጥዕዛዝ ለመፈፀም ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ለአብነት ያህልም የ603ኛ ኮር መምሪያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አውዴ ገብረየስ (ጎንደር)፤ የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሰለሞን በጋሻው (ደብረ ዘይት)፤ የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ (አስመራ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ አንድ መታወስ ያለበት አስቂኝ ድርጊት አለ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሽና የአድመኞቹ ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ወደስብሰባው የመጡት ዘግይተው ነበር፡፡ ወደ አዳራሹ ሲገቡ የሰብሳቢነቱን ቦታ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ ይዘውታል፡፡ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን መልቀቅ ሲገባቸው
ዝም አሉ፡፡ ይባስ ብለውም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን የመልቀቅ አዝማሚያ ሳያሳዩ ስብሰባውን መምራት ቀጠሉ፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የተሰበሰቡት የጦር አዛዦች እዚያው በዚያው ሌላ መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ፡፡ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን ጥለው ወጥተው እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ አድርገው መንጎራድ ጀመሩ፡፡ (ስልጣን እንዲህ ነው ወገኖቼ)
ሌላው ደግሞ፤ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ውስጥ ከተሳተፉ የጦሩ አባላት መካከል አንዳንዶቹ መፈንቅለ መንግሥቱ እንደሚሳካ ቀድመው እርግጠኛ በመሆን “እዚህ አድማ ውስጥ እኔንም አካፍሉኝ እንጂ ጎበዝ! በ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት ሳይነግሩኝ ቀሩ፡፡ ዛሬም ልትተውኝ ነው እንዴ? …” ብለው የተናገሩ የጦር መሪዎች እንዳሉ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተፃፉ ታሪኮች ያሳያሉ፡፡
የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች “ታማኝ ናቸው” ያሏቸውን የጦሩን አባላት ሰብስበው ሲነጋገሩ ንግግራቸው ጭቅጭቅ የበዛበት ነበር፡፡ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አስተዳደር ተወግዶ በምትኩ በጀኔራል መኮንኖች የሚመራ አዲስ መንግሥት የማቋቋም እቅዳቸውን ተናገሩ፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መተማመን እያጡ በሄዱ ቁጥር ጊዜ እየመሸባቸው መሆኑን መገንዘብ አቃታቸው፡፡
የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በሊቀ መንበሩ ሽኝት ላይ ሳይገኙ የቀሩ የጦር አዛዦች ሁኔታ ስላላማራቸው አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ስለነበር እያንዳንዱን ድርጊት ይከታተሉ ነበር፡፡ ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀ መንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው፡፡
ኮሎኔል አዲስ ተድላ እና ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ በሽምግልና ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ቢላኩም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ግን “ያለቀለት ነገር ስለሆነ ሽምግልናና ድርድር አያስፈልግም” ብለው መነታረካቸውን ቀጠሉ፡፡ ለመንግሥት ታማኝ በነበረው ጦርም ተከበቡ፡፡ በሁኔታው ተስፋ የቆረጡት አንዳንድ የጦር አዛዦችም ራሳቸውን አጠፉ፡፡
የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾችና መሪዎች በፈፀሙት የእቅድና የአፈፃፀም ስህተት ለአራት ዓመታት ያህል ታቅዶበት ሲውጠነጠን የነበረው መፈንቅለ መንግሥትም ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በተወደሰው ርምጃም ኢትዮጵያ በርካታና “በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ነበሩ” የተባሉ የጦር መሪዎቿን አጣች፡፡ ደርግም የደመ ነፍስ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ሊቀ መንበር ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከግንቦት 1981 ቢተርፉም ከግንቦት 1983 ዓ.ም ግን አላመለጡም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
አንተነህ ቸሬ