ወርሐ ነሐሴ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሕዝባዊ በዓላት ይደምቃል። እነዚህ ሕዝባዊ በዓላት በተለይም የልጅ አገረዶች ቢሆኑም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አዋቂዎችን ይነካል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መድረክ ተዘጋጅቶላቸው በአደባባይ ስለሚከበሩ ከመንግሥት አመራሮች እስከ ታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ይገኙበታል። ምክንያቱም በዓላቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማክበር የግድ የአዋቂዎች ተሳትፎ ይጨመርበታልና ሕዝባዊ በዓላት ሊባሉ ይችላሉ።
እነዚህ ሕዝባዊ በዓላት በተለይም እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የመሳሰሉ የልጅ አገረዶች ባህላዊ በዓላት በራሳቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ናቸው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የምናውቀው በመንግሥት አካላት አስተባባሪነት መድረኮች ተዘጋጅተው የአንድ አካባቢ ማህበረሰብ ወደ ሌላ አካባቢ ማህበረሰብ በመሄድ የባህልና የተለያዩ ልምዶች ልውውጥ ሲደረግ ነው። እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል ያሉ በዓላት ግን በራሳቸው የሕዝብ ሕዝብን ግንኙነት የሚያመጡ ናቸው። አሸንዳ በትግራይ ክልል ሲከበር ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከታተለዋል። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የዚያን ሰሞን የፕሮግራም ማደመቂያዎቻቸው የአሸንዳ ዘፈኖች ናቸው። የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች የሚታጀቡት በአሸንዳ ዘፈኖችና ትዕይንቶች ነው። የማህበራዊ መገናኛ ገጾች የሚደምቁት በአሸንዳ ትዕይንቶች ነው።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት የነሐሴን ወር ደማቅ ያደርጉታል። ከተሞች እነዚህን በዓላት ለማስታወስ በሚለብሱ ሴቶችና ወጣት ወንዶች ይደምቃሉ። የአልባሳት መደብሮችና የገበያ ቦታዎች ሁሉ እነዚህን በዓላት በሚያስታውሱ ጌጣጌጦች ይደምቃሉ። በየመዝናኛ ቤቶች የሚከፈቱ ዘፈኖች እነዚህን በዓላት የሚያደምቁ ናቸው።
በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች (በተለይም አማራና ትግራይ) የሚከበሩ እነዚህ በዓላት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ያጠናክራሉ። እነዚህ በዓላት ሲከበሩ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የባህል ቡድኖችና ታዋቂ ሰዎች ወደ አካባቢው ይሄዳሉ። ከቦታው ባይሄዱ እንኳን በመገናኛ ብዙኃንና በመድረኮች አማካኝነት ይከታተላሉ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ሁሉ የዚያን አካባቢ ምንነቶች በሰፊው ያውቃሉ። ከዚያ አካባቢ ሰዎች ጋር በቅርበት የመተዋወቅና የመጫወት ዕድሉን ያገኛሉ።
እነዚህ ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያስተዋውቁ በዓላት እንዳይበላሹ በጥንቃቄ ልንይዛቸው ይገባል። በተለይም ከባለፉት ዓመታት ስህተቶቻችን ልንማር ይገባል። ይህን ለማወቅ ደግሞ ግልጽ ማሳያ አለን።
ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት የአሸንዳ በዓል ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲቋረጥ አድርጓል። በዚህ ዓመት ደግሞ በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ የሚከበር አይሆንም። ወደ አካባቢው የሚሄዱ እንግዶች አይኖሩም ማለት ነው። ይህ ማንን ይጎዳል ከተባለ ለሕጻን ልጅ ራሱ ግልጽ ነው። ግንባር ቀደም ተጎጂ የአካባቢው ማህበረሰብ ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ጉዳቱ እንደ ሀገር ነው። የባህል ክፍተት ይፈጥራል፤ የባህል ክፍተት መፈጠር ደግሞ የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል። ስለዚህ የእንዲህ አይነት የሕዝብ በዓላት መቋረጥ የራሱ አሉታዊ ገጽታ አለው። ይህ እንግዲህ ዋናውን የጦርነት አውዳሚነት (የሰውን ልጅ ሕይወት) ሳንጠቅስ ማለት ነው።
ወደ ሕዝባዊ በዓላቱ እንመለስ። ሕዝባዊ በዓላት ስማቸው ራሱ እንደሚያመለክተው የሕዝብ ናቸው። አክባሪያቸውም ሕዝብ ነው። እዚህ ላይ ታዲያ በትልቁ የምንታዘበው ነገር ከሕዝባዊነት አልፈው የፖለቲካ መልዕክት ማስተላለፊያ ሲሆኑ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕዝባዊ በዓላት ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷቸው፣ ድጋፍ ተደርጎላቸው መከበራቸው በጣም ያስመሰግናል፤ ሕዝብን ለሕዝብ የበለጠ አስተዋውቀዋል። ዳሩ ግን በዚያው ልክ ደግሞ ከበዓላቱ ባህላዊ ይዘት ውጭ በሆነ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳ ይመስል የፖለቲካ መልዕክት ሲተላለፍባቸውም እናያለን። የፖለቲካ መልዕክት ለማስተላለፍ የፖለቲካ መድረኮች አይበቁም ወይ?
ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። በአንድ ሕዝባዊ በዓል ላይ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በሚቀጥለው ዓመት ለሚደረገው ምርጫ መልዕክት አስተላለፉ። በወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ አልተጀመረም፤ መድረኩ አካባቢ ያለ ብዙ ታዳሚ ደነገጠ። በሹክሹክታም ትዝብታቸውን ማውራት ጀመሩ። ደግነቱ ለመግባት የተፈቀደላቸው መገናኛ ብዙኃን ውስን ስለነበሩ የመጯጯህ ዕድሉን አላገኘም። ሰውየው የፖለቲካ መድረክ እስከሚያገኙ ድረስ ምን አስቸኮላቸው?
ይህ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ አይደለም። ገለልተኛ ነን ለሚሉ ወገኖችም ጭምር ነው፤ ለሕዝቡም ጭምር ነው። ሕዝባዊ በዓላት (በተለይም ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው) ላይ የፖለቲካ መልዕክት ያላቸው መፈክሮችና አልባሳት አይተን እናውቃለን። የፖለቲካ ቅሬታ ያለው ሰው ፓርቲ ውስጥ ገብቶ መታገል እንጂ ስለዚያ ቡድን ዓላማ የማያውቀውን ሕዝብ ሽፋን አድርጎ የራስን ዓላማ በድብቅ ማስተላለፍ ልክ አይደለም። ባለቤት የሌለው መልዕክት ይሆናል፤ ሕዝባዊ በዓሉንም ክብር ያሳጣዋል።
በተለይ በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚደረገው ግን የበለጠ ያስተዛዝባል፤ ምክንያቱም የተሻለ ኃላፊነት ሊሰማቸው የሚገባ እና አርዓያ መሆን ያለባቸው እነርሱ ናቸው። በሕዝባዊ በዓላት ላይ ፖለቲካዊ ንግግር ማድረግ የመንግሥትን መልዕክትም ተሰልቺ ያደርገዋል። ምክንያቱም መልዕክቱ ለዚያ በዓል ታዳሚያን ዓውዳዊ ላይሆን ይችላል። በዘመነ ኢህአዴግ የመንግሥት ባለሥልጣን ንግግር እንደ አሰልቺ ይታይ የነበረው ከይዘቱ በላይ ያለቦታው ስለሚነገር ነበር። ከእንደዚያ አይነት ልማድ አሁንም የተላቀቅን አይመስልም።
በሌላ በኩል ደግሞ የበዓላቱን ሕዝባዊነት ያደበዝዘዋል። ሊሄዱ ያሰቡ ወጣቶች ረጃጅም ፖለቲካዊ ንግግሮችን አስቀድመው በማሰብ ይሰለቻሉ ማለት ነው። ስለዚህ ሕዝባዊ በዓላት ላይ የፖለቲከኞችን መልዕክት ማስተላለፍ ባህልን ከመበረዝ አይተናነስም።
ከዚያ ውጭ ግን ሕዝባዊ በዓላት በመንግሥት ደረጃ ድጋፍ ተደርጎላቸው መከበራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። ምክንያቱም ለረጅም ዓመታት የነበረው ወቀሳ መንግሥት እንዲህ አይነት አገራዊ እሴቶችን አያበረታታም የሚል ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ መነቃቃት ታይቷል። የባህል ቡድን ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ መሄድም ተጠናክሮ ቀጥሏል። እንዲህ አይነት ባህልና ወጎቻችን ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015