ጥንዶች ወደ ትዳር ከመግባታቸው አስቀድሞ መተጫጨታቸውን የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ቀለበት በማጥለቅ ነው። አሁን አሁን በተለይ አንድ ወንድ ልቡ ሽቶ የሚያጫትን ሴት በጉልበቱ ተንበርክኮና እጇን ይዞ «ታገቢኛለሽ?» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
ለሁለቱም ጥንዶች ድንቅ የሚባል ጊዜና ስሜት እንደሚፈጥር የሚታመንበት ይህ ሁነት የሚፈፅመው ሰዎች በተሰበሰቡበት፣ ባልታሰበ አጋጣሚ፣ በተለይ ሴቷ ምንም መናገር በማትችልበትና እድል በማይሰጥበት ቦታ መሆኑን ትዕይንቱን እጅግ አስደንጋጭም አስደሳችም ያደርገዋል።
ይህ ሁነት ብዙውን ጊዜ ከፍቅርና ከአጋርነት መግለጫነት ባለፈ የአቅምንና የኑሮ ደረጃን የሚመሰከርበት ሲሆንም ይስተዋላል። የቀለበቶቹና የሚቀርቡበት መንገድም እንደ ግለሰቦቹ የተለያየ ሆኖ ይታያል። ኪሳቸው አበጥ ያሉ ወንዶች በጣም ውድ የሆነ ፈርጥ ያለው ያማረ ቀለበትን ለሚወዷት ሲያቀርቡ፤ ያጣ የነጣው በአንፃሩ እንደ አቅሚቲ ያለውን ያበራክታል።
ተቀባዮቹ ሴቶችም በጣም ውድ የሆነና አብረቅራቂ ቀለበት ሲበረከትላቸው፤ ሳይውል ሳያድር ቀለበቱን በማጥለቅ በኩራት ፎቶ እየተነሱ በየማህበራዊ ትስስር ገፅ ይለጥፉታል፣ ይኩራሩበታልም።
የ‹‹ታገቢኛለሽ›› ጥያቄ የቀረበባቸው መንገዶችና የቀረበበትን መንገድ በተለይ የቀለበቱን አይነት በሚመለከት ሚረር ትናንት ይዞት የወጣው መረጃም በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።
ሰዎች ከዓላማው ይልቅ ለ«ታገቢኛለሽ?›› ጥያቄ የሚቀርቡ ቀለበቶች፤ በጣም ውድ የሆነና አብረቅራቂ ሆኖ ካልተመለከቱ ደስታን በማይሰጣቸው በዚህ ጊዜ፤ ዘገባው ከዚህ በተቃርኖ አንዲት ሴት ከወርቅ አሊያም ከአልማዝ ሳይሆን ከጓደኛዋ ፀጉር የተሰራ ቀለበት ማጥለቋን አስነብቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ በጓደኛዋ ተግባር ከመናደድ ይልቅ እጅጉን ሃሴት ያደረገችው ሴት፤ ሳይውል ሳያድር ቀለበቱን በማጥለቅና ፎቶ በመነሳት በኩራት በማህበራዊ ትስስር ገፅ መለጠፏም ታውቃል።
‹‹በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጉር ዘለላዎች የተሰራ ነው›› የተባለለት አስደናቂ ቀለበትም፤ በማህበራዊ ትስስር ገፅ የበርካቶችን አስተያየት አስተናግዷል። በርካቶች ዓላማውን ታሳቢ በማድረግ ‹‹ፍቅር ካለ ይህ በቂ ነው፤ ሰዎች ፍቅራቸውን የሚገልፁበትን መንገድ ማክበር ይገባል፤ ይልቅስ ‹ታገቢኛለሽ?› እንዲህም ይቻላል›› ሲሉ፤ አንዳንዶች በአንፃሩ፤ ‹‹ካልጠፋ ቀለበት መሰል ጥያቄ ክብር ያለመስጠት ነው›› ብለውታል።
የእጮኝነት ቀለበት ጉዳይ በዚህ መልኩ ሲያነጋግር ይህ የመጀመሪያ አለመሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ ‹‹ባሳልፈነው ሳምንት አንዲት እንስት እጅግ በጣም ቀጭን የተባለ ቀለበትን ማጥለቋን ተከትሎ ብዙዎች ተነጋግረውበታልም›› ሲል አስነብቧል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2011
በታምራት ተስፋዬ