አዲስ ዘመን ድሮ

በአንድ ወቅት በሀገራችን ካለ አንድ በረሃማ ሥፍራ የጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲሁም ሌላ እኛ የማናውቀው ሰው መሰል ፍጡርም በውስጡ እንዳለ ጭምጭምታዎች ከአይን እማኞች ተደምጠው ነበር። ስለዚህ ጉዳይ በወቅቱ ምን ተብሎ ይሆን..“አዲስ ዘመን ድሮ” በዛሬው አምዳችን ይነግረናል። “የማታውቁት ነገር ቢኖር” ያሳውቀናል፤ እንደተለመደው ከወይዛዝርት ገጽም ተካተውበታል፤ መለያየት ሞት ነው..ሁሉንም ለእናንተ ለውድ አንባቢያን ይድረስ ብለናል።

የጥንታዊ ታሪክ ቦታ መገኘት ጭምጭምታ

በአሩሲ ጠ/ ግዛት፣ በጭላሎ አውራጃ በጢዮ ወረዳ በዱግዳ ም/ግዛት ባላምባራስ ዓምደ ቡታ ባላባትነት ልዩ ስሙ ቲሮ ኞሮ በተባለው ጭው ያለ በረሃ ሀገር ይገኛል።

………….

በዚሁ ቀበሌ ገለቶ ጦሪ የተባለው ሰው በበረሃው ውስጥ ሲዘዋወር አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ ይበቅላል ተብሎ በማይታሰብበት የደጋ እንጨት ጥድና የመሳሰለውም ጫካ ሆኖ በቅሎ አገኘው። በዚሁ ነገር ተደንቆ ወደ ጥዱ ጫካ እገባለሁ ሲል በማይታሰብበት ቦታ የጠራ ዉሀና በዚያው አጠገብ ፍል ውሀ አገኘ። ከውሃውም አጠገብ አጽፍ(ቆዳ) የለበሰ ጸጉሩ እንደ ባሕታዊ በትከሻው ላይ የወረደ ለአራዊት ውሀ መጠጫ ቦታ ሲያዘጋጅ በደረስሁበት ጊዜ በቁጣ ቃል “ምን ልታደርግ መጣህ? ከመጣህበት ተመልሰህ ሒድ፤ ያየኸውንም ሁሉ እንዳትናገር የተናገርህ እንደሆነ እስከ ሕይወትህ ያሠጋሃል” ብሎ ተናገረ።

ከዚህም በቀር ሌሊቱን በሕልሜ በመዓልት (ቀን) እንደ ገሠጸኝ አደርሁ። በዚሁ ሳልወሰን ተግሣጹን ሳላከብር በማግሥቱ ቦታው እንዳይጠፋብኝ እንጨት እየሰበርሁ በመንገድ እየጣልሁ ተመልሼ ነበርና ያንን ምልክት በመከተል በዚያ ቦታ ስደርስ ከየት መጣ ሳልል ድምጹን በመስማት ብቻ በጥፊ ቢመታኝ አንድ አይኔ ታወረ። አንድ አይኑ እስካሁንም እንደታወረ ነው።

ዳግመኛ እንደዚሁ ቦባሳ በዳሳ የሚባለው ይህንኑ የጥንታዊ ታሪክ ቦታ በማግኘት በዚያ ቦታ በመገኘቱ ብርቱ ተግሣጽ አግኝቶት እንዳይናገርም መከልከሉንና ሊናገር ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል ተብሎ መነገሩን ገልጿል።

ብዙዎች ሰዎች እንዲያሳዩኝ ስጠይቃቸው የበቃ መነኩሴ አብሮ ካልሔደ አይሆንም በማለት ለመሔድ አይፈቅዱም። ይህንንም ሁኔታ ያገኘሁት ከባላምባራስ ዓምድ ቡታ ልጅ ከአቶ ገና ዓምደ ነው። በዚሁ በተባለው ቦታ አካባቢ ኃይለኛ እንደ አውሎ ነፋስ የሚተፋ ዋሻ የሚገኝበት መሆኑን በማስረዳት ነግሮኛል።

ከዚህም ጋር በአጠገቡ የድንጋያ ከሰል በብዛት መገኘቱንና በመሐንዲስ ለመመርመር የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጿል። (አዲስ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 1944ዓ.ም)

ልጅህ ያጨኋትን ልጅ አግብቷል

ሲዳማ-አዱላ ገማሌ የተባለው ሰው በሀገረ ማርያም ወረዳ ግዛት እኔ ያጨኋትን ልጅ ልጅህ አግብቷታል በማለት የአቶ ገንዳ ኤደማን ቤት ስላቃጠለ ሲዳማ አስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከስሶ ቀርቦ በ፫ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። (አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 1959ዓ.ም)

የማታውቁት ነገር ቢኖር

በሕንድ ሀገር ያሉ ጥቂት ጎሣዎች ሴት በታመመች ጊዜ ሐኪሙ ፊቷን አያያትም። ሴትዮዪቱ በአጎበር ውስጥ ትቀመጥና አንድ እጇን ለሐኪሙ ታወጣለታለች። ሐኪሙ የበሽተኛዋን እጅ ይዞ ስለ ሕመሙ የሚጠይቀው ባሏን ነው። ባሏ መመለስ የማይችለውን ሚስቲቱን ይጠይቅና እንደገና ለሐኪሙ ይነግረዋል።

# በ1850ዓ.ም የካቲት 29 ቀን አንድ የስውዲን ወታደር በፓሪስ ከተማ ውስጥ ተገደለና በዚያው ተቀበረ። ወታደሩ ውሻ ነበረው። ውሻው የጌታውን ሬሣ ተከትሎ ጌታው ሲቀበር ከመቃብሩ ላይ ተኛ። ቀንና ሌሊት ሳይነሣ ብዙ ሳምንታት ቆየ። በመጨረሻው በረሀብና በውሃ ጥም ከጌታው መቃብር ላይ ሞተ። (አዲስ ዘመን ታህሳስ 13 ቀን 1958ዓ.ም)

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

# ጧት ከቤቴ ወጥቼ ወደ ቢሮ ሥራዬ በምሔድበት ጊዜ ሚስቴ ቢሮ እስክደርስ በዓይኗ ትከተለኛለች። ምክንያቱ ለምንድነው?

ተስፋዬ ሲሲዶ (ከአርባ ምንጭ)

-እግሯ ቀጥ ብሎ አይሔድ ይሆናል።

# አቶ ጳውሎስ በልጅነትዎ ወራት ቀልደኛ ነበሩ? ወይንስ ተማሪ ቤት በነበሩ ጊዜ? ያስኮርፉኝና ወዮውሎት። 2/ የቅዳሜን ጋዜጣ በተለይ በጣም አድርጌ እወዳለሁ። አንዳንዶቹ የጋዜጣን ጥቅም ባለማወቅ ነው ይመስለኛል አንብበው እንኩአን ሳይጨርሱ ግድግዳ ላይ ይለጥፉታል። በደንብ ለምን አያስቀምጡም።

ወ/ሮ አሰገደች ኃይሉ(ከአዲስ አበባ)

-አላስኮርፎትም እሜቴ። 1/ እኔ ለራሴ ቀልድ የሚባል ነገር አላውቅም፤ በጠቅላላው ነኃሁላ ቢጤ ነኝ። 2/ ጋዜጣን ማስቀመጥ ጥሩ ነው፤ ለማስቀመጥ ሀብት ይጠይቃል። መለጠፉም አይከፋም። ግን ተባይ ይይዛል።

# በሚመጣው ፋሲካ ተክሊል ያልተጨመረበት ጋብቻ እፈጽማለሁ። በዚያን እለት በጥቁር ሱፍ ፈንታ ጢንዚዛ የመሰለ በርኖስ ለብሼ እሞሸራለሁ ባይ ነኝ። ምክንያቱም የጥንቱን ወግ ለማስታወስ ያህል አውቄ ነው። ሙሽራዬስ በምን ትዋብ።

ሕለተ ወርቅ ጸጋዬ(ከሐረር)

-እንዲያ ነው ወንዱ። በርኖስ አይልበሱ፤ በርኖስ የድረገብ ነው። የዚያን ዕለት ልብሳችሁ የአገር ሸማና ካባ ነው። ሁለታችሁም ካባ ልበሱ፤ ሙሽሪት ግን ዓይነ ርግብ ታድርግ፤ ዱብል ባርኔጣው እንዳይረሳ። (አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 1959ዓ.ም)

መለያየት ሞት ነው;

“መለያየት ሞት ነው ለተዋደደ ሰው” ተብሎ የተዘፈነው ዘፈን እንደተዘፈነው ሳይሆን በሌላ መልክ ሲወሰድ መለያየት ሞት ላይሆን ይችላል። ይሄውም ከሞት ጋር ሲነጻጸር ነው። የሞተ አይመለስም። የቆመ ግን መገናኘቱ አይቀርም። ስለዚህም በብዙዎች ቤተሰቦች ዘንድ መለያየት እንደሞት ሆኖ ሲለቀስበትና ሲታዘንበት ይታያል። አዎ ልጅ ከእናት አባቱ፣ አባት ከልጆቹ፣ እኅት ከወንድምዋ፣ ወንድም ከእኅቱ ሲለያዩ ሆድ ይብሳል ዕንባ ያቀርራል። ልብ ይሸበራል፤ትካዜና ኀዘን ይፈጠራል። የማይቻል የማይገታና በቶሎ የማይረሳ ነገር ነው።

“ሞትን ከመለየት ምን አንድ አደረገው

ሞት ይሻላል እንጂ ቁርጡ የታወቀው”

(አዲስ ዘመን ህዳር 3 ቀን 1958ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 16/2015

Recommended For You