አበው ሲተርቱ «የቀበጡ ዕለት ሞት አይገኝም» ይላሉ። እውነት ነው፤ የሚያስከትለውና የሚሆነውን ሳያስተውሉና ሳይረዱ ወደ አንድ ነገር ዘው ማለት መጨረሻው መጥፎ መሆኑ አይቀሬ ነው። ብዙዎች ጀግና ለመባል፣ ታዋቂ ለመሆን፣ እንደሚችሉ ለማሳየት፣ በውርርድ አሊያም በሌሎች ምክንያቶች ያለ ጥንቃቄ አንዳች ተግባር ይከውናሉ። ሳያጣሩ የጀመሩት ነገር ስኬታማ ካልሆነም «ቀበጥ» ያሰኛል፤ በእኛ ዘንድ።
በመጀመሪያ የጀብድ ለመስራት ብታቅድም መጨረሻዋ ጩኸት እና ስቃይ የሆነን የአንዲት ሴት ታሪክ ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል በድረገጹ እንደሚከተለው አስነብቧል። ቻይናዊቷ ወጣት በተንቀሳቃሽ ምስሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በማህበራዊ ድረገጾች በመለጠፍ ትታወቃለች። መጠሪያ ስሟም «ሲሳይድ ገርል ሊትል ሰቨን» የሚሰኝ ሲሆን፤ በዚሁ ተንቀሳቃሽ ምስሏም ጥቂት ተከታዮችን ማፍራት ችላለች።
ታዲያ ከዕለታት በአንዱ ቀን ወጣቷ ስትቀብጥ አደገኛ የሆነ ነገር ለመስራት ታስባለች። የምትከውነው ነገር የሚሳካላት ከሆነም የበርካቶችን ትኩረት በመሳብ ተከታዮቿን ለማበራከት እንዲሁም ታዋቂ ለመሆን እንደሚያግዛትም እምነቷ ነበር። ያሰበችውም ምስሏን እየቀረጸች አንድን የባህር እንስሳ በሕይወት እንዳለ መብላት ነው። ለዚህ እንዲሆናት የመረጠችው የባህር እንስሳ ደግሞ «ኦክቶፐስ» በሚል ስያሜው የሚታወቀውን ዓሣ ነበር።
ዝግጅቷን አጠናቃ ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደጀመረም ወጣቷ ባለ ብዙ እግሩን ፍጥረት በእጇ በመያዝ ወደ አፏ ታስጠጋዋለች። በቅጽበት ውስጥ ግን ነገሮች ተለዋወጡ፤ ዓሣው በእግሮቹ የአንድ ጎን ጉንጯን በቁጥጥሩ ውስጥ አስገባ። ወጣቷም ድንጋጤ ሳይታይባት ለማስለቀቅ ሙከራ ማድረግ ጀመረች። እንዲያውም «ተመልከቱ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ» እያለች ገለጻ ታደርግ ነበር፤ ዓሣው ግን ፍንክች ሊል አልቻለም። እየቆየም ይበልጥ ጉንጮቿ ላይ በመለጠፍ ህመም አስከተለባት፤ መቋቋም ያልቻለችው ወጣትም መጮህ ጀመረች።
«ማስለቀቅ አልቻልኩም፤ በጣም ያማል» እያለች በመጮህ ከዓሣው ጋር የምታደርገው ግብ ግብም አንድ ጉንጯን የሚያሳጣት ይመስል ነበር። በመጨረሻም ዓሣውን ከፊቷ ማላቀቅ ብትችልም ጉንጯ ላይ ጥቂት ጉዳት ማድረሱ አልቀረም። በእጇ እንደያዘችውም «ፊቴን አበላሽቶታል፤ ሆኖም በእቅዴ መሠረት በሚቀጥለው ቪዲዮ የምበላው ይሆናል» ብላለች ለተከታዮቿ።
ይህ የባህር ውስጥ ፍጥረት በርካታ እግሮች ያሉት ሲሆን፤ እግሮቹን ከመዋኘት ባሻገር ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅም እንደሚጠቀምባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ለማሽተት፣ ነገሮችን ለመንካት እንዲሁም ለሌሎች ተግባራትም እግሮቹን ይገለገላል።
ወጣቷ ያሰበችው ተሳክቶ ኦክቶፐሱን በሕይወት እንዳለ መብላት ባትችልም በደረሰባት ነገር ግን ታዋቂ መሆኗ አልቀረም። ተከታዮቿ ተንቀሳቃሽ ምስሉን በመጋራት በመላው ቻይና ያሰራጩት ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም በአውሮፓ እና መላው ዓለም ሊዳረስ በመቻሉ ዝናን አትርፋለች።
በርካቶች ግን ተንቀሳቃሽ ምስሉን በመመልከት በሚሰጡት ግብረ መልስ እየተሳለቁባት እንደሚገኝም ነው ኦዲቲ ሴንትራል የጠቆመው። አንድ አስተያየት ሰጪ «ይገባታል፤ ኦክቶፐሱን ልትበላው እንደሞከረችው ነው የበላት» ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ «እኔ ኦክቶፐሱን ብሆንና ከእነ ሕይወቴ ልትበላኝ ብትሞክር፤ ተመሳሳይ ነገር አደርግባት ነበር» ብሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
ብርሃን ፈይሳ