እስካሁን የእነ ማንን ቆሌ ወዳ እጅ እንደምትሰጥ፤ የእነ ማንን ደግሞ ጠልታ እንደምትመቀኝ የሚያውቅ አልተገኘም። ውል አልባ በመሆኗም መገኛዋን ያወቀ፣ አመጣጧን የተገነዘበ፣ መግቢያዋን የለየ፣ ፍላጎቷን የተረዳ፣ ደስታዋ ከምን እንደሚቀዳ የገባው፣ … የለም።
አንዳንዶች «ጠራችን» ይላሉ (ድምጿ እንዴት ያለ ይሆን?)፤ ሌሎች ደግሞ «ሰተት ብላ ከቤቴ ገባች» ባዮች ናቸው (እንዲያው በር ታንኳኳ ይሆን?)። ከእነዚህ ውጪ የሆኑት ደግሞ «ቆሌዋ ጠርቶኝ፣ ተገልጣልኝ፣ ወደ እኔ አዘንብላ፣…» ይሉናል፤ አይ ጥበብ¡
እኔ ግን እስካሁን ድረስ፤ መንፈስ ትሁን፣ የሚዳሰስ አካል ይኑራት፣… ማወቅ አልቻልኩም። ከማን ተወለደች፣ እነማን አሳደጓት፣ ቀልቧን የሚገዙት የትኞቹ ናቸው፣… የሚለውንም የሚመልስልኝን አላገኘሁም። ግን ግን ባላውቃትም ቀልቤ ለምዷት የት እንዳለች ይነግረኛል (ቀልቤ ስለመጠራቱ ግን እርግጠኛ አይደለሁም)።
መቼም ይህንን ስል «አሁን መገኛዋ ከወዴት ይሆን?» የሚል ጠያቂ አይጠፋም። «ጥሩ ተማሪ ካለ ትምህርት የትም ይገኛል» ይባል የለ፤ ለጠየቃችሁኝ መልሴን በደስታ አደርሳችኋለሁ። በአሁኑ ወቅት የጥበብ መገኛ፤ ከመጠጥ ቤት ባልኮኒ ከጠርሙሶች መሃል ነው (ወይም ይመስለኛል)።
እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከድርሰቶቻችን፣ ከግጥም መድብሎቻችን፣ ከስዕል ሸራዎቻችን፣ ከሙዚቃዎቻችን፣ ከገለጻችን፣ ከማግባባታችን፣ ከማስረዳታችን፣ ከመገንባታችን፣ ከሥራችን፣ ከአርቆ ማየታችን፣ ከግንዛቤያችን፣ … የጠፋችው፤ ስካር ስለጀመረች ነው።
ማታ ማታ ከየመሸታው ቢራዋን ስትጋት ቆይታ፤ ቀኑን በመኝታ ታሳልፋለች (ለዛ እኮ ነው አድራጎታችን ሁሉ ጥበብ አልባ የሆነው)። ወገን ይህ ባይሆንማ የአልኮል መጠጥ ለማስተዋወቅ እንዲያ ባልታተረች ነበር። ደግሞ እኮ መጠጡን፤ ከባህላችን፣ ልምዳችን፣ እሳቤያችን፣ ከልባችን መሻት ጋር እንዴት እንደምታያይዘው።
የሚገባትን ትታ ከማይገባት በር ማንኳኳት ከጀመረችም፤ እነሆ በሀገራችን የቢራ አብዮት ፈንድቷል። እንደሚታወቀው በዓለም ላይ በርካታ አብዮቶች ተነስተዋል፤ እኔ ግን የቢራን ያህል ሀገር ያጥለቀለቀ እና እንደ ደራሽ ሁሉንም መጠራረግ የቻለ አብዮት አላየሁም። ምክንያቱም የጥበብ እጅ አለበታ¡
እርግጥ ነው መጠጥ ያጀግናል፤ የማይቻሉ የመሰሉ ነገሮችንም እንደሚሆኑ ያስረግጣል። ደስታንም ይስባል፤ የተከፋን፣ ያዘነን፣ የተጨነቀንም፣ … ፈውሶ መልካም መልካሙን ብቻ ያሳስባል። ዓለምን ሁሉ በፊትህ ያጎነብሳል፣ የመጨረሻው ስኬታማ ሰውም አንተ ትሆናለህ፣ በየትኛውም ነገር ላይ ነግሰህ ማንነትህን እንድታሳይ ድፍረት ይሰጥሃል።
ግን ደግሞ ብዙ አይቆይም፤ ብዥታው መጥራት ይጀምራል። ሁኔታህንም ትታዘባለህ፣ ያለህበትን ትገነዘባለህ፣ ድንፋታህና ደረት መንፋትህ ሁሉ ከንቱ መሆናቸውን ስትረዳ፤ ያ ሁሉ ደስታ ገደል ገብቶ ራስህን መጥላት ትጀምራለህ። በስኬትህ ቦታ ጸጸት ይተካል፤ በነገስክባት ዓለም ኪስህ ባዶ መሆኑንም ትገነዘባለህ። ይሄኔ በድጋሚ ራስህን ትጠላለህ (እንዲህ ስትሆን ጥበብ ራሷ የምትስቅብህ ይመስለኛል)።
እመነኝ ወገኔ፤ በገዛ የቴሌቪዥን መስኮትህ ብቅ እያሉ በጥበብ በተለበጠ ጠርሙስ የሚያሳዩህ ዓለም በአንተ ውስጥ ጥቂት ዕድሜ ብቻ ነው ያለው (ልኬቱን ከፈለክ፤ ከህልም ትንሽ ከፍ ቢል ነው)። ስትጠጣ ሌላ ሰው ብትሆንም፤ ስትነቃ ከጠርሙሶች መሃል የደበቅከው አንተነትህ ብቅ ብሎ ይወቅስሃል። ምን እንደሆንክ ማስታወስ እስከማትችል ድረስ፤ ማንን ታስደስት ማንን ታስቀይም ባለማወቅ ውዝግብ ውስጥ ትገባለህ።
ጥበብ አእምሮህ ላይ መጫወት ስትጀምር፤ ማስታወቂያዋን አይተህ «አንዴ ፉት ልበል» አሊያም «ምን ምን እንደሚል ልቅመሰው» ትላለህ። ቀጥሎ አእምሮአዊና አካላዊ ቁመናህን ወደ ማበላሸት ይገባል። ከዚያማ ሽምጥ እየጋለበ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወትህ ድረስ ሰተት ብሎ ይዘልቅልሃል።
አሁን አሁን ጥበብ እጇን ያሳረፈችበትና የተጋነኑ ማስታወቂያዎች ከገበያ ሳቢነታቸው አልፈው፤ መወያያና መነጋገሪያ አጀንዳችን እስከመሆን ደርሰዋል። ከማስታወቂያ አስነጋሪዎቹ መብዛትም በላይም ወደ እኛ የሚገቡበት መንገድ እያደር እየረቀቀና እየዘመነ ነው።
በእርግጥ እንደ ነጋዴ እና ገበያ አፈላላጊ የማስታወቂያ ድርጅቶች ስኬታማነታቸውን መካድ አይቻልም። ጥያቄው ግን ይህንን ሁሉ ዕውቀትና፣ ገንዘብ እና ጊዜ በዚህ ላይ ማዋል ተገቢ ነው ወይ? የሚለው ነው(ጥበብም በዚህ ተጠያቂ ናት)።
ልብ አንጠልጣይ፣ እጅግ ሳቢ፣ በባህልና ልምዶቻችንን የተመረኮዙ፣ በቀላሉ በሕፃናትና ታዳጊዎች ልብ መታተም የሚችሉ፣ የትኛውንም የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ ያደረጉ፣ እግራችን በረገጠበት ስፍራ እንድናያቸው ሆነው የጎሉ፣… መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ ተጽእኖ እያደረሰ ይገኛል።
በአንጻሩ ሀገርን ለሚያሳድግ፣ የሕዝብን ኑሮ ለሚያቃና፣ ጤናን ለሚጠብቅ፣ አንድነትን ለሚያመጣ፣ የወደፊትን ተስፋን ለሚያመላክት፣… በዚህ ልክ በሕዝብ ዘንድ የሰረጸ ማስተዋወቂያ መስራት አልተቻለም። ምክንያቱም ጥበብ ሰክራለቻ።
ከመጠጥ አምራቾቹ፣ አስታዋዋቂዎቹ፣ ለሕዝብ ከሚያቀርቡት የመገናኛ ብዙኃኑ፣ በየመንገዱና ሕንፃው ምስሉን ከሚለጥፉት ሁሉ፤ በእውኑ ልጅ የሌለው ለመጪው ትውልድስ የማይጨነቅ ማን ይሆን? መልካም ሕይወቱ በጠጪነቱ እንዲመሰቃቀል የሚፈልግስ ማን ነው? ብሩህ ተስፋውን በጠርሙስ እየሰፈረ በራሱ ገንዘብ የሚሸጥስ ለምንድን ነው?
ይህ ጥያቄ የሁላችንንም ምላሽ የሚሻ ነው። እርግጥ ነው፤ ይህ ዓይነቱ ነገር እንዲቆም የተቆረጠለት ጊዜ ደርሷል። ቢሆንም በቀረችው ጊዜ ይሄን ያህል ካልታወቅን ብሎ መጋነን ምን ይባላል? አሁን የሚታየው ነገር ፈላጊን በእጅ አዙር አስገድዶ ማምጣት ነው፤ ይልቅ በገዛ ፈቃድ ፍላጎትን ከፈላጊ ለማገናኘት ብንሞክር ትልቅነታችን ይጎላል። ነገ ለሚደርሰው ጥፋት ምክንያት ከመሆንና ከአእምሮ ጠያቂነትም እንድናለን። ጥበብም ልብ ይስጥሽ¡
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
ብርሃን ፈይሳ