ረመዳን ከሪም! እንኳን ለረመዳን ጾም በደኅና አደረሰን። አረፈድኩ እንዴ? ከአበሻ ጋር ቀጠሮ የያዙ ጊዜ ነው መሰለኝ «ከመቅረት መዘግየት ይሻላል» ይላሉ አሉ፤ ፈረንጆች። እና አፉ ብላችሁ የእንኳን አደረሳችሁ ምኞቴን ተቀበሉኛ! እንኳን አብሮ አደረሰን። እንደ ክርስትናም ሆነ እስልምና እምነት ጾም ክፉ መንፈስን ማሸበሪያ፣ ለጿሚውም ልብ መግዣና ከአምላኩ መገናኛ ነውና፤ ከጸቢይ ጾም ወደ ረመዳን እየተቀባበልን ይህን ክፉ መንፈስ መድረሻ እያሳጣነው መሆኑን ልብ በሉ።
ተንኖ እስኪያልቅና እስኪጠፋ ድረስ ወዲያ ወዲህ እያለ እረፍት ያሳጣን ይሆናል እንጂ፤ እኛ ጋር ያለው ኃይል ከርሱ ይበልጣል። ልንገራችሁ! የምትወዱት ሰው ሲገባ ሲወጣ መውደዱን ቢነግራችሁ ደስ አይልም? ይህቺን ነገር ከፊልም ላይ ያውም ከአውሮፓውያኑ ነው ብዙ ጊዜ የማያትና የምሰማት፤ እና እቀናለሁ። «…የሚለውን ይስጥሽ!» ብላችሁ መርቁኛ! አንዳንዴ ደግሞ «በተግባር ነው መውደድ የሚገለጠው እንጂ ምንድን ነው አስር ጊዜ እወድሻለሁ ! እወድሃለሁ ! መባባልና መደጋገም» የሚሉ ያጋጥማሉ፤ እጣላቸዋለሁ።
ነገሬ ተግባር አያስፈልግም ከሚለው ሳይሆን ከቃሉም ነገር አለ ለማለት ነው። በልብ ያለ መልካም ነገር ካልተናገሩት ዋጋው የተናገሩትን ያህል ከፍ አይልም። ከተናገሩ በኋላ ደግሞ ተግባር ሲጨመርበት ምሉዕ ይሆናል። መዋደድን በቃል ከዛም በተግባር መግለጽ ነገንም ይታደጋል። በአንድ ዘመን የሚዋደዱ ሰዎች የሆነ ጊዜ ላይ ግጭት በመካከላቸው ቢፈጠር እንኳ የመጀመሪያ ሥራቸው ዱላ ማንሳት ሳይሆን «እወድሃለሁ ብለሽኝ አልነበረ?» ወይም «እወድሻለሁ አላልከኝም ነበር?» የሚል ነው የሚሆነው።
ስሜትን በቃል መግለጽ ትልቅ ዋጋ እንዳለው አምናለሁ፤ መውደድንም ጭምር። ስላደረጉልን ነገር ሳይሆን እንዲሁ የምንወዳቸው ሰዎች ካሉ ማወቅ አለባቸው። ለምሳሌ እናት ልጇን የምትወደው አንዳች ያደረገላት ነገር ኖሮ አይደለም። ግን መውደዷን ሁሌም የምትነግረው ልጅ በአእምሮው አንድ የሚያስበው ነገር ጨምራለታለች ማለት ነው። በቃ! ያለ ምንም ወቅታዊና «አሁናዊ» ምክንያት…አለ አይደለ? «ከመሬት ተነስቶ!» እንደሚባለው ዓይነት እህታችሁ ቀርባ ወይም ወንድማችሁ መጥቶ «እወድሃለሁ» ወይም «እወድሻለሁ» ቢሏችሁ፤ ምን ዓይነት ስሜት ደርሶ እንደሚተላለፍባችሁ የሚያውቅ ያውቀዋል።
ነገር ግን ለምትወዱት ሰው አንዳች መልካም ነገር አድርጋችሁ ስታበቁ «ይህንን ያደረገልኝ’ኮ ለራሱም ስለሚጠቀም ነው» ከመባል ወዲያ የሚያበሳጭ ነገር የለም ባይ ነኝ። በእርግጥ ጓደኛዬን፤ «እወድሻለሁ ጓደኛዬ» ብላት፤ «ምን ተገኘ?» ልትለኝ ትችላለች። ለመዋደድ ብዙ ምክንያት አያስፈልግም፤ እንደውም ሲሆን ሲሆን ለጸብ ነው ብዙ ምክንያት እየፈጠሩ እንዲዘገይ ማድረግና ዕድሉን ማጥበብ። ደግሞም ነገሩን ማኅበረሰባዊ ከፍ ብለንም አገራዊ ስናደርገው፤ «አገሬን እወዳለሁ» ስንል እንዲሁ እንጂ በጥቅም ምክንያት አይደለም። እንደውም ምንም የማያገኝ ለፍቶ አዳሪ ነው አገሩን የሚወደው።
አብዛኛው ባለሀብት አገሩን እንዲወድ «ኑ! ኑ!» የሚል ዘፈን ካልተዘፈነና የእጣን ጪስ፣ የዶሮ ወጥ ካልታየ አገሬን አይልም እየተባለ ይታማል። እውነት ከሆነ እንጠይቃለን፤ ብቻ ግን መውደድን መግለጽ ዋጋ አለው። እና ይህን ስብከት የመሰለ ነገር የነገርኳችሁ በምስሉ ላይ የምታዩት ጽሑፍ ጎትጉቶኝ ነው። የአብነት አዲስ ከተማ ወጣቶች…ይመቻችሁ! ይሄ የጽሑፍ መልዕክት የተለየ ምክንያት የለውም፤ ልክ እኔና እናንተ ለምናውቃቸውና ለሚቀርቡን እስልምና እምነት ተከታዮች እህት ወንድሞቻችን በሞባይል እንደላክነው መልዕክት ነው። ግን ይገዝፋል፤ ይተልቃል።
መውደድን «ከመሬት ተነስቶ» እንደመግለጽ ነው። የትውውቅና የቅርበት ጉዳይ አይደለም፤ የሁሉ ነገር መግቢያና መቋጫ የሆነው ፖለቲካ ጋር አይደርስም፣ አይመጥኑትም! ይርቃቸዋል። ቀናትን የመጋራትና እውነታን የመካፈል ጥበብ ነው። የሃይማኖት እኩልነትና መቻቻል አይደለም፤ ተቻቻል እኩል ነህ የሚለውማ ሕግና ሕገ መንግሥት ነው። ይህኛው ግን ሰው መሆንን ማግዘፍ ነው። ጥፋትና ክፋታችን «ዝም ብሎ ደስ አይለኝም… በቃ! ዝም ብዬ እጠላዋለሁ» ማለት ይቀናናል። እንዲህ ዝም ብለን ብንዋደድ ግን ከፍ እንል ነበር። ነገሩን እያካበድኩት ይሆን? እንግዲህ በጾም ሰሞን ቂም አይያዝምና ካጋነንኩትም አትቀየሙኝ። ብቻ ቢለምድብን ስለወደድኩ ነው። በዛም ላይ የአብነት አዲስ ከተማ ወጣቶችን «ይመቻችሁ!» ለማለት ስለፈለግሁም ነው።
የእነዚህ ወጣቶች መልዕክት «እንኳን አደረሳችሁ- ረመዳን ከሪም» የሚለው ብቻ አይደለም። በበኩሌ መልዕክት እንዳለው ይሰማኛል። ባልታሰበ ሰዓት እንደሚገለጽ መውደድ፤ ሊወርሰን የሚታገለንን የጎሰኝነት ጥላ ላይ ብርሃን ሆኖ ለአፍታ የሚሰውርልን ነው። መገናኛ ብዙኅኑ ለመደመጥና ለመታየት ሲሉ መርጠው የጥፋትን ዜና ሲያሰሙ፤ ከእነዚህ ወጣቶች ሰፈር አንዱ የግንብ ጥግ ላይ የተለጠፈው ከልብ የመነጨ መልዕክት «ፍቅር አለች!» የሚል ነው። አገርና የአገር ፍቅር ላይ አብዝቶ በሙዚቃው የሠራው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/፤ «ጃ ያስተሰርያል» በተሰኘ ሙዚቃው «ጃ ማለት ፈጣሪ…’ሚሰረይ ይቅርታ፤ እኛ ስንዋደድ ይሰማናል ጌታ» እንዲል፤ መዋደድ ዋጋው ከምናውቀው ነገር ሁሉ ውድ ነው።
ደግሞ እኛ ስንዋደድ ፈጣሪ እንደየ ጸሎታችን መስማቱ ብቻ አይምሰላችሁ። የሚጠላን ሊደናገርና ግራ ሊጋባ እንደሚችልም ልብ ይሏል! ሲደናበር ይዞ መሸኘት ነው። እና ብቻ! የአብነት አዲስ ከተማ ወጣቶች መውደዳችሁን፣ መልካም ምኞታችሁንና ፍቅራችሁን ስለገለጻችሁ እናመሰግናለን። ስሜቱን ስላጋባችሁብን ዋጋችሁ ቀላል አይሆንም። መጠላላትና መጣላት በበዛበት ወቅት በተስፈኞች ልብ ውስጥ ላለች ቅንጣት እምነት «መንገድ አለ» እንዳላችሁ ስለሚቆጠር እጅ እንነሳለን። እንዲህ ነው የአራዳ ልጅ! ረመዳን ከሪም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
ሊድያ ተስፋዬ