ጤና ይስጥልን አንባቢዎቻችን እንደምን ከረማችሁ? መንትዮቹ የዘመን ሀኪሞች ነን። ለዛሬ በአዲስ ዘመን ቅዳሜ ያዘጋጀነውን የጤና መረጃ እናካፍላችኋለን። ላለፉት ሦስት እትሞች ስለ ጤና ምንነት እና የጤና ዓይነቶች ለሦስት(3) አበይት ክፍሎች በመክፈል እያንዳንዳቸውን ምን ዓይነት የጤና ዓይነቶች እንደሆኑ ለመግለጽ ሞክረናል።
ለዛሬ የደም ማነስን ምንነት፣ ምልክቶች እንዲሁም ህክምናውና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከአንባቢዎቻችን በርከት ያሉ ጥያቄዎች ደርሰውናል። በመሆኑም የደም ማነስን በሚመለከት ዘርዘር ያለ መረጃ እናካፍላችኋልን።
መግቢያ፡-
ማንኛውም ህይወት ያለው ነገር የተፈጥሮ እና የሰውነት ግዴታውን ለማከናወን መመገብን፤ መጠጣትን እንዲሁም መተንፈስን የግድ ይለዋል፡፡ ታዲያ ይህን ሲያደርግ የተለያዩ መንገዶችን እና ስርአቶችን አልፎ ለጥቃቅን ህዋሳት(ሴል) መድረስ ይኖርበታል፡፡ የተመገብነው ፣የጠጣነው እንዲሁም የተነፈስነው ከዛም ከሰውነታችን ሴሎች የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለማጓጓዝ የሚጠቅመን ደማችን ነው ፡፡
በደማችን ውስጥ የተለያዩ ኬሚካሎች፣የተለያዩ የሴል አይነቶች የሚኖሩ ሲሆን ምግብን ፣ኦክስጅንን ለማመላለስ እና ከዛም ከሴሎቻችን የሚወጣውን የተለያዩ ተረፈ ምርቶች ለምሳሌ እንደ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (CO2 ) የሚያመላልስልን በደማችን የሚገኘው የቀይ የደም ሴል ነው፡፡ ከነዚህም መካከል አይረን፣ ቫይታሚን B12፣ፍሌት እንዲሁም የተለያዩ የፕሮቲን ዘሮች ይገኛሉ ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ንጥረ ነገሮች በማዋሀድ የቀይ ደም ሴል ይገነባል ፡፡ በቀይ የደም ሴል ውስጥ ኦክስጅን ለማመላለስ የሚጠቅም ሄሞግሎቢን የሚባል ንጥረ ነገርይገኛል ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የቀይ የደም ሴል እንዲሁም በደም ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ የደም ሴል የሚያመርተው በዋናነት መቅኔያችን ነው፡፡ እንግዲህ የደም ማነስ ተብሎ የሚጠራው የህመም አይነት በተለያየ ምክንያት እነዚህን የቀይ ደም ሴል ማነስ ለመጥራት የምንጠቀምበት ስያሜ ነው፡፡ በህክምናው አጠራር ‹‹አኒሚያ›› የሚባለው ነው፡፡
የደም ማነስ ወይም አኒሚያ እራሱን ችሎ ወይም ያለ ሌላ ምክንያት የማይከሰት የህመም አይነት ነው ፡፡ ይህ ማለት አኒሚያ ስንል አብረን የደም ማነስ ያመጣውን ምክንያት ማወቅ መመርመር እንዲሁም ማከም ያስፈልጋል፡፡
መንስኤዎች
1.የአይረን ማነስ
የቀይ የደም ሴል ለመገንባት፣ ከሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች አንዱ አይረን ይገኝበታል፡፡ስለዚህ ይህ አይረን የተባለው ንጥረ ነገር ከሌለ በሚፈለገው መጠን የቀይ ደም ሴሎችን ማምረት አይቻልም ፡፡ ለአይረን መጠን መቀነስ ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው በበቂ መጠን የአይረን በደም ውስጥ አለመኖር ነው፡፡ ለዚህም በበቂ አይረንን አለመመገብ ዋነኛው ነው፡፡
2.የቫይታሚን እና ፎሌት እጥረት
ልክ እንደ አይረን ቫይታሚን እና ፎሌት የተሰኘው ንጥረ ነገሮች የቀይ የደም ሴልን በመገንባት ዋነኛ ግብአቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በበቂ ሁኔታ አለመኖር የቀይ ደም ሴሎችን እንዳይኖሩ ያደርጋሉ፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሰው የእነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነታች አለመኖር ቢሆን ለዚህም እነዚህ ንጥረ ነገሮች የያዙ ምግቦችን አለመውሰድ እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል፡፡
3. ከህመም ጋር የተያያዘ
አንዳንድ የህመም አይነቶች እንደ ካንሰር፤ የኤች አይቪ (HIV/AIDS) የኩላሊት ህመም፤ከሆድ እቃ እና አንጀት ህመም የመሳሰሉት ከቀይ የደም ሴል መመረት ጋር በተያያዘ የቀይ ደም ሴል መጠንን ይቀንሳሉ፡፡
4. ከመቅኔ ህመም ጋር የተያያዘ
የቀይ የደም ሴል የሚመረተው መቅኔያችን ውስጥ ነው፡፡ የተለያዩ የህመም አይነቶች ለምሳሌ፡-ሉኬሚያ (Leukemia) እና የተለያዩ ተያያዥ እና ተመሳሳይ የካንሰር አይነቶች የቀይ የደም ሴሎችን ምርት ይቀንሳሉ፡፡
5. ከቀይ የደም ሴሎች መሰባበር የተያያዘ (Hemolytic)
አንድ አንድ የህመም አይነቶች የቀይ የደም ሴሎችን ያለግዜያቸው እንዲሰባበሩ እና ጥቅም እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ። በተጨማሪም መድሀኒቶች መርዛማ ኬሚካሎች ይህን የሚያደርጉ ይኖራሉ፡፡
6. ሌሎች የደም ማነስ የሚያመጡ ፡-
የወባ በሽታ፤ እርግዝና፤ ከቀይ የደም ሴል አፈጣጠር ችግር ጋር የሚያያዙ እንደ ( ሲክል ሴል አኒሚያ ) ከፍተኛ የደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ወ.ዘ.ተ. ናቸው፡፡
የደም ማነስ ምልክቶች
የደም ማነስ ያመጣው ህመም ወይም ሁኔታ ተጨማሪ ምልክቶችን ሊያመጣ ቢችልም በአጠቃላይ ግን የደም ማነስ ምልክት ይህንን ይመስላል፡፡
- የድካም ስሜት
- የተዛባ የልብ ምት
- ትንፋሽ ማጠር
- የሰውነት መዛል
- የራስ ምታት
- የሰውነት ነጭ መሆን
- የእግር እና የእጅ መቀዝቀዝ
- የደረት ውጋት ወይንም ህመም ወ.ዘ.ተ
አጋላጭ ሁኔታዎች
አጋላጭ ሁኔታዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ
- ያልተመጣጠኑ ምግብ መብላት
- የምግብ እጥረት
- የደም መፍሰስ
- ለተለያዩ ኬሚካች መጋለጥ
- እርግዝና
- በዘር የደም ማነስ ያለ ከሆነ
- እድሜ
ህክምናው
የደም ማነስ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ የደም ማነሱን ያመጣው ምክንያት ተለይቶ እሱን ማከም ያስፈልጋል፡፡ህክምናው የደም ማነሱን መጠኑ (አነስተኛ፤መካከለኛ ወይንም ከፍተኛ) በማለት እንደ ደረጃው የህክምናውን አይነት እና አማራጭ ይወስዳል፡፡ለምሳሌ ከፍተኛ የሆነ የደም ማነስ ከተገኘ እንደ አስፈላጊነቱ ደም ሊሰጥ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የደም ማነሱን የመጣውን ምክንያት ጎን ለጎን ይታከማል።ለምሳሌ የአይረን፤ የቪታሚን፤ የፎሌት እጥረት ሆኖ ቢገኝ እንደ አስፈላጊነቱ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ሊሰጥ ይችላል፡፡
መከላከያው
የደም ማነስ ለመከላከል የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል እጅግ አስፈላጊ ነው፡ ፡ይህም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ የደም ማነስ ምልክቶችን በሚመለከቱበት ግዜ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ቦታ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ እና ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ከሌሎች ህመም ጋር ተያይዘው የሚመጡ የደም ማነስ ሲኖረው የቅርብ የሆነ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ምንጭ፡- ዶክተር አለ 8809:
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011