የሀገራችን ሰዎች ስለዝንጀሮም ሆነ ጦጣ ብልጠት መተረክ፤ መዝፈንና መጫወት ይወድዳሉ፤ ስለ ሁለቱም
«ገዳይ ገዳይ አለች የቆለኛ ልጅ፤
አባቷ ምን ገድሏል? ዝንጀሮ ነው እንጂ» ተብሎ ይዘፈናል።
«ዝንጀሮ በዳገት ጦጣ በዛፍ ላይ፤
የማይበላ እህል ይጠበቃል ወይ» ይባላል። ይህ ዘፈን ተፈልጋ በቀላሉ የማትገኝን ፍቅረኛ ተስፋ ማድረግ ከንቱ እንደሆነ ይመክራል።
«የዝንጀሮ ባልቴት አትባልም አንቱ፤
ላርግሽ በደረቴ እንዳበደ ሴቱ ።
ዝንጀሮ ጠባቂ ላያድር ያመሻል፤
ፈርቼሽ ነው እንጂ ልቤ ከጅሎሻል» የሚል ዘፈንም አለ።
አበደ ሴቱ የተባለው ሴቶች ሁሉ የወደዱትና ያበዱለት የአንገት ጌጥ (ግማዴ) ሊሆን ይችላል። የዝንጀሮ ባልቴት በአንቱታ እንደማትጠራ አንቺም እኩያየ ነሽና በደረቴ ላይ ላርግሽ፤ ልለጥፍሽ እንደማለት ነው።
«ዝንጀሮ እንኳን ባቅሙ ያውቃታል ወዳጁን፤
የፈለፈለውን ይሰጣታል የጁን» ተብሎም ተዘፍኗል።
የባለሥልጣኖች የሙስናና የዘረፋ ነገር ሕዝቡን ስለአማረረው
«የጅብ ሊቀ መንበር፤ የዝንጀሮ ዳኛ፣ የጦጣ ጸሐፊ፤
ሁሉም ሌቦች ናቸው አታላይ ቀጣፊ» ተብሎ መዘፈኑም ይታወሳል። በተረትም ዝንጀሮ ሲጠግብ ያባቱን ዋሻ ይረሳል ይባላል። ጦጣን አስመልክቶ
«ጦጣ ባለቤቷን ታስወጣ» ሲባልም መስማት የተለመደ ነው።
በዝንጀሮና ጦጣ ላይ ለመንደርደር የፈለግሁት በቦኩ መካነ ጸበል ቆይታየ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ ፈልጌ ነው። ቦኩ ከአዳማ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል በግምት አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ስፍራ ነው።
ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለበት፣ የተፈጥሮ እንፋሎት የሚፈልቅበትና ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጅብና ሌሎች የዱር እንስሳት የሚፈነጩበት ድንግል የተፈጥሮ አካባቢ ነው። ከቦኩ ገደላማ ቦታ ላይ ሆኖ ቁልቁል ሸለቆውን፣ ገጸ ምድሩን፣ ልዩ ልዩ የዛፍ ዓይነቱን ሲመለከቱት መንፈስን ያድሳል። በአጭር ርቀት አረንጓዴ የሆነውን የወንጂን የሸንኮራ አገዳ ተክል በሠፊው ሜዳ ላይ ተዘርግቶ ሲያዩት ልብን በተስፋ ያለመልማል።
ቀደም ባለው ጊዜ ታላላቅ ሰዎች ሳይቀሩ በቦኩ የተፈጥሮ ደን ውስጥ በመገኘት የአደን ሥነ ሥርዓት ያካሂዱበት ነበር። በጤና እክል ምክንያት ወደ ቦታው ሄጄ በነበረበት ሰዓት መምህሬ ጀንበሬ ብዙ ወርቅ የተባሉ የእንፋሎቱ ደንበኛና ቋሚ ተጠቃሚ እንዲሁም የመቂ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አዛውንት እንዳጫወቱኝ፤ የቀድሞው ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በደጃዝማችነታቸው ዘመን ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ጋር ወደ ሥፍራው በፈረስ እየሄዱ ድኩላና ሌሎች የዱር እንስሳትን ያድኑ ነበር።
ደጃዝማቹ አደን በሚያድኑበት ሰዓት ከቦኩ ገደል ሥር እንደ ጭስ እየተነነ የሚወጣውን የተፈጥሮ እንፋሎት ይመለከታሉ። ይህ እንፋሎት የሕዝብ መታከሚያ እንዲሆን በማሰብ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እንዲጠና ካደረጉ በኋላ እንዲመሠረት ያደርጋሉ። መምህሬ ጀንበሬ እንዳጫወቱኝ ያኔ የ27 ዓመት ወጣት ነበሩ። በተፈጥሮ እንፋሎቱ ለመጠቀም በ1947 ዓ.ም
ወደ ቦኩ ሲሄዱ ለጸበልተኞች ማረፊያ ትንሽዬ ሣር ቤት በመሠራት ላይ ነበረች።
የሣር ቤቷ ግድግዳ ቆሞ ሣር ከዳኝ ይጠፋል። እርሳቸውም ዕውቀቱ ስለአላቸው “እኔ ልክደነው” ብለው በቀን 1.50 ሳንቲም እየተከፈላቸው ቤትዋን አሳምረው በሣር ክፍክፍ ይከድኑዋታል። በወቅቱም በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ጠላ፣ ቆሎ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ለጸበልተኛው ያቀርቡ ነበር። ያኔ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች ራቅ ብለው ድርጊቱን በጨዋነት ከመመልከት በስተቀር እንዲህ እንደዛሬው ዓይን ያወጡ ዋና ተዋናዮች አልነበሩም።
በወቅቱ የተፈጥሮ እንፋሎቱ የቦኩ ሚካኤል ጸበል እየተባለ ከመጠራቱም ባሻገር ሰው በተለምዶ የእንፋሎት መታከሚያ ክፍሎችን ገብርኤል፣ አቦ፣ ማርያም እያለ ይጠራቸው ነበር። በኋላ ላይ የተፈጥሮ እንፋሎቱ ከእምነት በተላቀቀ መልኩ ለሁሉም የእምነት ተከታዮች መታከሚያ እንዲሆን ስለታሰበ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይገለገልበታል።
የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች በቆርቆሮ እንዲሠሩ ተደርጐ አገልግሎት ሲሰጥ በነበረበት ሰዓት አንድ ባለሥልጣን ታክመው ስለዳኑበት መብራት እንዲገባለት እንዳደረጉ መምህሬ ጀምበሬ አውግተውኛል። የቦኩ ሚካኤልም ከአካባቢው ተነሥቶ ከዋናው አዳማ ከተማ መግቢያ በር ላይ በዘመናዊ ፕላን ቤተክርስቲያኑ በካቴድራል መልክ እንዲገነባ ተደርጓል።
ከአንዳንድ ሰዎች እንደተረዳሁት የተፈጥሮ ሀብቱን መንግሥትም፣ ግለሰብም ሲያስተዳድረው የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዲንሾ የተባለ ድርጅት ተረክቦ፣ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶችን፣ የአልጋ ክፍሎችን ካፊቴሪያዎችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት ከመስጠቱ ባሻገር እንግዶች እንዳይጉላሉ ከአዳማ ቦኩ አድርሶ የሚመልስና በየቀኑ የሚመላለስ ተሽከርካሪ መድቦ የሕዝቡን ችግር አቃልሏል።
በተለይ ለ1ኛ ደረጃ የእንፋሎት ክፍሎች ተጠቃሚዎች የዘመናዊ ሻወር አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል። የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከርም አዘጋጅቷል። ዘመናዊ የእንፋሎት መገልገያ ክፍሎች ኃይለኛ የሙቀት መጠን በማመንጨታቸው ምክንያት ተጠቃሚዎች በተለምዶ “ጥቁር አንበሳ”፣ “ፌዴራል ፖሊስ”፣ “መከላከያ”፣ “ጤና ጥበቃ”፣ ትምህርት ሚኒስትር” ብለው ይጠሯቸዋል። በዚህ ዓይነት በጣም የሚጋረፈው እንፋሎት በአሁኑ ጊዜ ፌዴራል ተብሏል። ፌዴራል ገብቼ ወጣሁ ይባላል።በደረጃ በተከፋፈሉት የተፈጥሮ እንፋሎት መገልገያ ቦታዎችም ሰው ደስ ብሎትና በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ወደመጣበት ይመለሳል።
በተለይ የመታጠቢያ ውኃ በባልዲ የሚያቀርቡና ክፍሎቹን ሰው ተጠቅሞ በወጣ ቁጥር አጽድተው ለአገልግሎት የሚያዘጋጁ ወጣቶች ታታሪነት በእጅጉ ያስደንቃል። ነገር ግን በቦኩ የእንፋሎት መገልገያ ቦታ ጧት፣ ሌሊትና ማታ አካባቢውን መድፍ የተተኮሰ ያህል የሚያናውጠው የጅብ ጩኸት፣ ስልት ያለው የዝንጀሮዎችና የጦጣዎች ቅሚያና ዘረፋ አያድርስ ያሰኛል።
መንገደኛ ገና ከመኪና ሲወርድ የቦኩ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች እጅብ ብለው ወደ ሰው ሲመጡ መልካም አቀባበል ለማድረግ ያሰቡ ይመስላሉ። መንገደኛው አገልግል፣ ፌስታል፣ ሻንጣ፣ ሊያንጠለጥል ይችላል። እነ አጅሬ ያዩትን ነገር ከመቅጽበት ላፍ አድርገው ይሮጣሉ። በየመኝታ ክፍሉም እየገቡ ይዘርፋሉ። ምግብ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሞባይል፣ ልብስ በፌስታል… የተያዘ ነገር ነጥቀው ይሮጣሉ። አልጎረስ፤ አልነከስ ያላቸውን ሞባይል ወደ ገደል ይወረውሩታል።
እነዚህ ማጅራት መቺዎች የካፊቴሪያና የአልጋ መስተዋቶችን ሰባብረው ጥለዋቸዋል። በተለይም ካፊቴሪያዎች ኮርኒስ ስለሌላቸው ጦጣዎች ተንጠልጥለው ይገቡና ከወራጁ ላይ ይሠፍራሉ። ምግብ በሚቀርብበት ሰዓት ከላይ ሆነው ሽንታቸውን በምግቡ ላይ ይለቁታል። ሊበላ ያሰፈሰፈ ሁሉ፤ “አይ አይ አይ” በማለት ምግቡን ወደ ውጭ ሲደፋው ተንደርድረው በመውረድ እየተሻሙና እየተጣሉ ይበላሉ።
የዝንጀሮ መንጋው ሰላማዊ መስሎ እየተጐማለለ በካፊቴሪያ ዙሪያ ይሠፍራል። ያላወቀ ሰው ምግብ አዝዞ ሊበላ ሲል መስተዋቱ በረገፈው ግድግዳ በኩል እጁን ልኮ ከመቅጽበት ምግቡን ይዞት ይሮጣል። አንዲት ሴትዮ ከመኪና እንደወረዱ እንጀራ በአገልግል ታቅፈው ሲራመዱ፣ አንድ ትልቅ ግመሬ ዝንጀሮ ትልቁን አገልግል በቅጽበት ላፍ አደረገና ወደ ላይ ወደ ገደሉ ይዞት ወጣ።
ወዲያው አገልግሉን ፈታታና ለሳምንት የተያዘውን ስንቅ በደቂቃ ውስጥ ብቻውን ጠብ አደረገው። ከዚያ ቆየና አገልግሉን ወደታች ሲወረውረው አገልግሉ ተንከባልሎ በእልህና በንዴት ሲንጨረጨሩ ወደነበሩት አሮጊት ዘንድ ደረሰ። “ተመስጌን እንኳን አገልግሌን ሰጠኸኝ” ብለው ዝንጀሮውን አመሰገኑት። የዱር እንስሳቱን ብልጠት ሰው ሁሉ እንደ መዝናኛ ከመመልከት ውጪ የሚጨክንባቸው የለም።
የዝንጀሮ እና የጦጣ መዛለያ የሆኑት የጣሪያ ቆርቆሮዎች ተጣመዋል፣ ረግበዋል። በቦኩ አካባቢ ያሉ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች ከሰው ጋር ማኅበራዊ ኑሮ ስለመሠረቱ የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት ወደ ጫካ ከመሠማራት ይልቅ እየቀሙ መኖርን ተለማምደውታል። ሰው መፍራትም ማፈርም ትተዋል።
የሶደሬ ጦጣዎችም ልክ የቦኩ ዘመዶቻቸው እንደሚያደርጉት ኑሯቸው የተመሠረተው በንጥቂያ ላይ ነው። የቦኩ ጦጣዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ይርመሰመሳሉ። ዝንጀሮዎች ግን በአብዛኛው 4 እና 5 ሰዓት ላይ በብዛት ከወጡ በኋላ በ11 ሰዓት ወደ ሠፈራቸው ይከትታሉ። የመንገደኛ ዳቦና አምባሻ የለመዱትና በዓባይ በረሃና ጊቤ በረሃ ውስጥ የሚኖሩት ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች ግን ጨዋነት ይታይባቸዋል። መኪና ባለፈ ቁጥር እጃቸውን እያውለበለቡ ከመለመን መኪናውን አላሳልፍ ከማለት ውጪ ከሰው አይቀሙም ።
በነገራችን ላይ ዝንጀሮም ሆነ ጦጣ ከሰው የሚሻሉበት መንገድ አለ። ቆየት ያለ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው፤ ዝንጀሮ ከሕጋዊ ሚስቱ ውጪ ወደ ሌላ ሄዶ አይወሰልትም። ሚስቱ ብትሞትበትም ወይንም ሚስት ባል ቢሞትባት “ይመነኩሳሉ” እንጂ ሁለተኛ ጋብቻ አይፈጽሙም። ጦጣዎችም እንዲሁ ናቸው። ነውረኝነታቸው ግን በዚያ ሁሉ ሕዝብ መኻል የወንድና የሴት ግንኙነት መፈጸማቸው ነው። ሌላው ወንድ ዝንጀሮ ሽንቱን ከሸና በኋላ ብልቱን በእጁ ይዞ ሽንቱን ማራገፉ ለንጽሕናው ያለውን ትኩረት ያመለክታል።
በቦኩ ቆይታዬ አንድ ጅብ ከጧቱ 3 ሰዓት ገደማ አጠገባችን ጩኸቱን እንደ መድፍ ለቅቆ ቢያስደነግጠንም ግቢው በታጣቂዎች በሚገባ ስለሚጠበቅና አጥሩም የተጠናከረ በመሆኑ የፈራ ሰው አልነበረም። ይልቁንም ጸበልተኛው ሁሉ እየሣቀ “አይ አጅሬ ጠብቶበት ሳይሆን ረፍዶበትኮ ነው ምድሩን በጩኸት የሚያናውጠው» እያለ ተዘባበተበት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በታደለ ገድሌ ጸጋየ