የዓለም አትሌቲክስ በታሪኩ ያነገሳቸው ከዋክብት

ቀነኒሳ በርሊን ላይ ጥሩነሽ ደግሞ ሄልሲንኪ ላይ ያሳዩት ብቃት
 በዓለም አትሌቲክስ ከምርጥ 20 ውስጥ መካተት ችሏል፣

ከበቆጂ አፈር ከተገኙት ወርቆች መካከል እንደነሱ በኦሊምፒክ እና በዓለም ቻምፒዮና የውድድር መድረኮች የደመቀ አትሌት የለም።የሀገራቸውን ባንዲራ በክብር ያላነሱበት የአትሌቲክስ መድረክ የለም። ኢትዮጵያ የከዋክብት ሯጮች ሀገር መሆኗን ደጋግመው ካስመሰከሩ እልፍ ሯጮች ሁለቱ የተለዩ ናቸው። በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ትዝታ ታትሞ ሊፋቅ የማይችል የራሳቸው የሆነ የአሯሯጥ ስልት አላቸው።ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የአንጋፎቻቸውን እግር ተተክተው የዓለም ቁጥር አንድ አትሌት በመሆን ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ለተቀናቃኞቻቸው የራስ ምታት ሆነው የዘለቁት እነዚህ ሁለት አትሌቶች ለሚሳተፉባቸው ውድድሮች ልዩ ጣዕምና ድምቀት ናቸው። ለሀገራቸው ልጆችም የአሸናፊነትና የፅናት ምልክቶች ናቸው።በአንድ ዘመን ገነው ለመታየት በቅተዋልና የበርካታ ወጣትና ታዳጊ አትሌቶች እንደነሱ አላማ አላቸው።ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ።የበርካታ ገድሎች ባለቤት የሆኑት ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ከነገሱባቸው የውድድር መድረኮች መካከል የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቀዳሚው ነው።እአአ በ2003 ፓሪስ የሚጀምረው የቻምፒዮናው ተሳትፎ ታሪካቸው በበርካታ ሜዳሊያዎች የታጀበ ሲሆን፤ በየግላቸው ያስቆጠሯቸው ሜዳሊያዎች ብዛትም ከበርካታ ሀገራት የተሻሉ ያደርጋቸዋል።

የረጅም ርቀት ሩጫ ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ በፓሪስ፣ ሄልሲንኪ፣ ኦሳካ እና በርሊን በተካሄዱ የዓለም  ቻምፒዮናዎች ላይ ኢትዮጵያ ስሟ በስፋት በተጠቀሰባቸው ርቀቶች ተሳትፏል።በዚህም 5 የወርቅ እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ በቻምፒዮናው የግል የደረጃ ሰንጠረዥ 8ኛ ላይ ተቀምጧል።ጠይሟ ወርቅ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በፓሪስ፣ ሄልሲንኪ፣ ኦሳካ፣ ሞስኮ እና ለንደን በተካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎዎቿ 5 የወርቅ እና 1 የብር በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር በደረጃ ሰንጠረዡ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሁለቱ አትሌቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በቀዳሚነት የሚመሩ ሲሆን፤ ሀገር ቢሆኑ በዓለም የደረጃ ሰንጠረዡ 23ኛን ይይዙ ነበር።

የሁለቱ ድንቅ አትሌቶች ጀብድ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ሲታወሱ የሚኖሩ ቢሆኑም፤ ከተሳትፎዎቻቸው መካከል ግን የተወሰኑት ታሪካዊ ናቸው።አንድ ወር ብቻ የቀረውን የቡዳፔስቱን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተከትሎ በስፖርት ቤተሰቡ ድምጽ ከተሰጠባቸው 40

 ውድድሮች ደረጃ ውስጥም ሁለቱ አትሌቶች በተከታታይነት ተቀምጠዋል።በዚህም መሰረት 18ኛውን ደረጃ የያዘው የቀነኒሳ በቀለ የ2009 በርሊን ቻምፒዮና ሲሆን፤ የጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የ2005ቱ የሄልሲንኪ ቻምፒዮና ተሳትፎዋ ነው። ሁለቱ አትሌቶች በእነዚህ ውድድሮች የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ጥንድ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ባለድል መሆናቸው አይዘነጋም፡፡

የአስደናቂው አትሌት ለመጨረሻ ጊዜ ስኬታማ በሆነበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አስደማሚ ብቃቱን ለዓለም ማሳየት የቻለው በቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለት ወርቅ በማስመዝገብ ነው። የበርሊኑ ተሳትፎ ከአመት በፊት በቤጂንግ ኦሊምፒክ ጥምር ወርቅ ባጠለቀባቸው ርቀቶች ተደግሟል። የብቃቱ ጫፍ ላይ የደረሰው ቀነኒሳ አሸናፊነቱ ባያጠራጥርም ሁለት ወርቆችን አንድ ክብረወሰን ጋር መቀዳጀቱ ለብዙዎች ትንግርት ነበር። በወቅቱ 5ሺ ሜትርን

 13:17.09 በሆነ ሰዓት የሮጠው ይህ ጀግና አትሌት በ10ሺ ሜትር ደግሞ 26:46.31 የሆነ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በቻምፒዮናው የመም አትሌቶች ታሪክ ብቸኛው መሆን ችሎ ነበር። ይህንን ተከትሎም የዓለም አትሌቲክስ ‹‹ይህ ሰው በረጅም ርቀት ከታዩ እና ወደፊትም ከሚታዩ አትሌቶች ምርጡ ነው›› ሲል አወድሶታል።

በውድድር ወቅት በአስደናቂ ትኩረቷ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ዙሮች ተፎካካሪዎቿን በረጅም ርቀት ልዩነት ማንበረከኳ መልከ መልካሟን አትሌት ጥሩነሽ ከሌሎች የተለየች ያደርጋታል። ጥሩነሽ ኢትዮጵያን ካኮራችባቸው ተደጋጋሚ ድሎች መካከል አንዱ የሄልሲንኪው የዓለም ቻምፒዮና ነው።በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ሁለት ወርቆችን ባጠለቀች በጥቂት ወራት ልዩነት ሄልሲንኪ ላይ የታየችው ምርጧ አትሌት 5ሺ ሜትርን የሮጠችው 14:32.93 በሆነ ሰዓት ነው። ይኸውም ቀድመው ከተመዘገቡ ሰዓቶች 6.36 ሰከንዶች የፈጠነ በመሆኑ በሀገሯ ልጅ ብርሃኔ አደሬ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ከእጇ ለማስገባት አስችሏታል። ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ በምትታወቅበት የ10ሺ ሜትር በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያውን ማጥለቅ ችላለች።ይኸውም በዓለም ቻምፒዮና መድረክ በእነዚህ ርቀቶች ሁለት ሜዳሊያዎችን ያጠለቀች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት አድርጓታል።የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት ላይ የተለየ ብቃት በማሳየት ተሸላሚ የሆነችውም በዚያ ውድድር ነበር። ያም አስደናቂ ብቃቷ ዛሬ ላይ በዓለም አትሌቲክስ የአርባ አመታት ታሪክ ውስጥ ከማይረሱ ሃያ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ሊመረጥ በቅቷል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *