የአመላችን ነገር አመላም ያበቅላል፤ አይጣል ነው። አሁን አሁንማ ከሰው (ከመሰሎቻችን) ጋር አላስኖር ሊለን ደርሷል፡፡ መሬት ጠበበችኝ ሊልም ይዳዳው ይዟል፡፡ አመል ሆኖብን ምን ቢዋብ፣ ቢሽቀረቀር፣ ቢለፋ፣ ቢታትር በዓይናችን አይሞላም፡ ፡ ፈጣሪ ይቅር ይበለኝ እንጂ ከአመል ጎዶሎነት የአካል መጉደል በስንት ጣዕሙ ይሻላል እቴ፡፡ እንደውም እኮ «የእኔ ብቻ ሸጋ» በሚያሰኝ ልክፍት የአመል በሽታ ታማሚዎች ሆንን እንጂ የዚችን አገር ጸጋ በልኩ ላይቋደስ የመጣ ያለ አይምሰላችሁ። ሆሆይ በል ጥናትክን አቅርብ እንዳትሉኝ፤ ተጠንቶ ተጀምሮ፤ በጥናቱ የሚጠናቀቅ ለውርርድ አታገኙም፤ አትሰቡት፡፡
«ላያስችል አይሰጥም» ነው ወይስ ላያስችል አይፈጥርም፡፡ አሁን ለመሬት የሚባለው፡፡ አዎ! ቻይማ ባትሆን የእኛ አመል ገመና ለስቅላት ይዳርገን ነበር። ይች ቻይ መሬትማ ሁልጊዜም የምትሆነው በልኳ ነው፡፡ በልካችን ያልተቃኘው የእኛ አመል፣ ልካችንን ያልተረዳነው እኛ ምስቅልቅል እያደረግናት እንጂ እሷማ የምትሆነውን አሳምራ ታውቃለች፡፡ ከልኳ በላይ የሆንባት የእኛው ጉድ ነው፡፡ አልክ አትበሉኝ እንጂ፤ እንደ እውነታው ከሆነ ካለ ልኩ የተፈጠረ የለም፡፡ ያለ ልኩ የሚኖርም ማንም የለም። ልኩን ማጤን ግን ተስኖታል፡፡ አመላችንን መዛኝ፣ ልካችንን ነጋሪ መስሪያ ቤት ባለመኖሩ እንጂ እኛማ ለጉድ የበቃን ነን፡፡
የሰው አመላችንን ክደን በውሻ (ለዚያውም በእብድ ውሻ) አመል ተክተናል፡፡ ውሾች ሆነናል ብል በስድብ ናዳ መዝገብ ላይ አታስፍሩት፡፡ እንደ ውሽልሽል የድንጋይ ካብ አመላችን ሊንደን መቃረቡን መፈተሽ ግን ደግ ነው፡፡ አዎ! ጥርጥር የለውም ማንነታችን ሊናድ ዘሟል። ኧረ እንደውም ሰውነታችንን የካድን «እባቦች» ሆነናል የሚል በአጽንኦት የታዘበ አይጠፋም። በሚያመዝነው ባህሪያችን ተሰልቶ እንስሳነታችን ይመደባል፤ ይፈረጃል፤ ቢባል ጉዳችን እስከ አናታችን ድረስ ነው፡፡ ፍርጃ ነው። ግንቦት 7 እና ኦነግ የተሟሹበትን ፈርጀ ብዙውን አፈራረጅ አላልኩም፡፡
«በፕሮፌሰር እከሌ፣ በዶክተር እከሌ ጥናት እንደተረጋገጠው» ብለህ ምንጭ ጥቀስ የሚል ስለራሱ አመል ነጋሪ የሚናፍቅ አይጠፋም፡፡ ኧረ የተጸውኦ ስማቸውን ባታነሳም በወል ስማቸው እንኳን «የዘርፉ አጥኚዎች» እንዳሉት ብለህ በእነሱ የብዕር አንደበት የእኛን አመል ንገረን የሚልም ይኖራል። ብዙ ነገር እኮ ተዛንፎብናል ጎበዝ!፡፡ በዓይናችን የምናየውንና በየዕለቱ የምንሆነውን ተግባር መዝነን ቆም ብለን በሰውኛ አስተሳሰብ ከማጤን ይልቅ በጆሮ በኩል የመጣን ወሬ ያለአንዳች ልኬት ፍጹም እውነት አድርጎ ማሽሞንሞን የምንወድ አመላሞች ብዙ ነን፡፡
አመላችን የደረሰበትን የክፋት ጥግ መርምሮ ለመረዳት የተሻለ የአመል ሊቅነት አይጠይቅም። ወደ ሰውነት መመለስ በቂ ነው፡፡ ሰው ስንሆን ሰው ይታየናል። (ታላቁ ሙፍቲ እንዳሉት) አጃኢብ የሚያሰኘው ደግሞ በሕዝብ አገልጋይነት ካባ ውስጥ ተጠቅልለን የምንጦር የመንግሥት ሠራተኞች ሺ አመለኛ መሆን ነው፡፡ በእኛ የአመል ክፋት ስንቱ ግዑዝ የመስሪያ ቤት ሕንፃ ጭምር አመላም ሆኗል፤ በአመላምነቱ ታውቋል፡፡ ሠራተኛው በአመላምነቱ እስከ «አንቱ» ክብር ሾልኮ የተቆናጠጠ ብዙ ነው፡፡ የበርካታው ሺህ አመላምነት ግን «አይ አመል እቴ!» ተብሎ የሚታዘንለትና መሳለቂያነትን ያተረፈ ነው፡፡ ክፉ አመላምነት፡፡ በተከፈተችው ጉሮሮው የሚወረውርባት ቁራሽ ያጣ እስኪመስለው ድረስ በፍርኃት ተንጦ ነፍሱን ማሸነፍ ተስኖት አመል ያበቀለ ቀዥቃዣ አመላም፡፡
የዚህ ዓይነቶቹ «ሰው መሳይ በሸንጎ» የአመል ምድብተኞች ተርታ ውስጥ ይሰለፋሉ፤ ይካተታሉ፡፡ ባልታወቀው ደረጃ መዳቢ እንደተገለጸው ተብሎ ይታወቅልኝ፤ ይዘገብልኝ፡፡ በእርግጥ ለሌሎች የነፍስ ከፍታ የራስን ነፍስ ከማሳነስና ከማሸነፍ በላይ መስዋዕትነት የለም፡፡ ያኔ ሚዛኑ ሰውነት ይሆናል፡፡ ሰው መሆን እንልመድ፡፡ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል ከመንግሥት ሥራ ተጣብቶ የኖረ አንድ «ሞዴል አገልጋይ» የሲቪል ሰርቪስ ተሸላሚ ባልደረባዬ ሹክ ያለኝን ሀሜት አስታወሰኝ፡፡ «በሞቴ ንገረን የሚል ከመካከላችሁ አንድ ሰው እንኳን አይታየኝም?» ተውት፡፡
እኔም «ከዓይን ይልቅ የጆሮ አመላም» ስለሆንኩ የተሰማችሁን ስሜት ነገ እሰማዋለሁ፡፡ ወሬ ዬን ግን ቀጠልኩ፤ ደግሞ ለማውራት ማን አህሎኝ፡፡ ሰውዬው ምን አለኝ መሰላችሁ ‹‹ ከሺ ባለ ማዕረግ ፤ ሺ አመለኛ ሰው ሥጋውና ጎጆው የደነደነ ነው›› አትሞኝ። ብሎ የራስ ጸጉሬን አሸት አሸት አደረገኝ፡፡ አዎ! ሺ አመልን ተላብሶ ከአመለኞች ጋር መራመድ ይቻ ላል፤ተችሏልም፡፡ ግን ሰው መሆን አያስች ልም፤ ሰው መሆንንም አይሰጥም፡፡ ሥጋ ሰውነትን ያስክዳል። ሰውዬው ይሄን የታዘበ በት ያ ወቅት ብዙ ዲግ ሪዎች ለመደርደር መማሰን አለበለዚያም በበርካታ ዘርፎች መመረቅ ገንዘብ አያስገኝም፡፡
ይልቁንስ የበርካታ አመሎች ባለቤት መሆን ተሽሏል ነው ነገሩ፡፡ አዎ! አመላችን ሰውነታችንን አስክዶናል። ያባይሆንም እንዲህ እርስ በእርስ መናከሳችን፣ መተማማታችን፣ መቋሰላችን እና መጋደላችን እየበረታ ባልሄደ ነበር፡፡ የሰው ሕይወት መጥፋት ኖሮበት አይሳቅም እንጂ እኮ የአመላችን ጣጣ በሰላሳ ሁለት ጥርስ የሚያንከተክት ነው። እንጂማ ሰው እንሁን፤ ሰውነትን እንላበስ ብለው ሆነው የተገኙ መሪ ከዶክተሩ በላይ ሰውነት ላሳር ነው።
ነገሩ ‹‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም›› ነው፡፡ ‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› ነውና የአበው ብሂል የተከበሩት ታላቁ የእስልምና እምነት መሪ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ከተናገሩት አስገራሚ ነጥብ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ‹‹የሕዝብ መሪዎች ያለወቅታቸው፣ያለ ጊዜያ ቸው፣ያለሰው ብቻቸውን ምጡቅ ሆነው ይፈጠራሉ። የዚህ አይነት ክስተት ሲገጥም ምርጫቸው መምከር፣ ተው ማለት፣ መለመን፣ መታገስ፣ መቻልና ብቻቸውን ማልቀስ ይሆናል እጣቸው›› ይላሉ፡፡
በእሳቸው እምነት ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የእሳቸው አይነት ሰው የሆነ መሪ ከዚህ በፊት አላየሁም፤ ከዚህ በኋላም ይመጣል ብዬ አላስብም። ከሁሉም በፊት ‹‹ሰውነት ይቀድማል፤እስኪ ሰው እንሁን›› ብለው ከንግግራቸው እኩል እንባቸው በጉንጫቸው ኮለለለለለ…ልል ብሎ ሲወርድ በአይኔ በብረቱ የተመለከትኩት መቼም አይረሳኝም፡፡ እናም ሰው እንሁን፡፡ የማያሳፍር ሰውነት ይኑረን፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በሙሐመድ ሁሴን