እግር ጥሎዎት ጠብ የተጫረበት አካባቢ ይደርሱ ይሆናል፤ አጠገብዎ ያሉ ሰዎች በነገር አንድ አንድ ሲሉ ቆይተው ጠብ ውስጥ ገብተው አይተውም ሊሆን ይችላል፡፡ በቅርብ ርቀት ጠብ ተነስቶም ሊያዩ ይችላሉ፡፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የእርሶዎ አቋም ምንድን ነው?
አንዳንዶች ጠብ ሲያዩ እግሬ እውጪኝ ብለው ይፈተለካሉ፡፡‹‹ማምለጥ ነው ለጫማው በሁዋላ ይታስበበታል›› ነው ያለው ማስታወቂያው፤ ‹‹እስከሚጣራ›› እንዳለችው እንስሳም እንደማለት ነው፡፡
ከዚህ አልፈው ሲገላግሉ የሞቱትን፣ የተመቱትን፣ ወይም ስለእነዚህ ተጎጂዎች የሰሙትን እያስታወሱም ወራጅ አለ ብለው እግሬ አውጪኝ የሚሉ በቅርብ ርቀት ሆነው ወሬውን ተቀብለው አቀነባብረው የሚናገሩም ጥቂት አይደሉም፡፡
እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች ሲሸሹ መልስ ብለው እንኳ የሚመለከቱ አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች አንዳንዴ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአካል እና የህሊና ጉዳት ሊከሰት ይችላል፤ ጠበኞቹ ደንጋይ መወራወር ቢጀምሩ የማን ያለህ ይላሉ፡፡ ቢታኮሱስ፤ አይጣል ነው፡፡
ምስክርነት መጠራትም አለ፤ ለዚያውም ምን ቅብጥ አርጎ እዚያ ውስጥ አስገባኝ የሚያሰኝ፡፡ የኛ ሀገር ምስክርነት ስራ ያስፈታልና እሱም ሌላው ዳፋ ነው፤ በተከሳሽ በኩል ቅሬታ ካስከተለ ደግሞ ባለጋራ መፍጠር ይከተላል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ትንሽ ቀረብ ብለው ሁኔታውን ይከታተላሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወገኖች በግርግሩ ላለመጎዳት በሚል ነው ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚጥሩት፡፡ እነዚህም ልክ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተጣሉ እናገላግላለን ያሉ የቀመሱት ቡጢ ሊታሰባቸው ይችላል፤ አንተን ማን ገላጋይ አደረገህ? አስደበደብከኝ ብለው ሊማቱ የሚጋበዙ ጠበኞች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ እስኪዋጣላቸው ድረስ ወይም ገላጋይ እስከሚገባ ድረስ ቆመው መመልከታቸው ጥፋት አይኖረውም፡፡
እነዚህም እንደ ፈርጣጮቹ ገላጋይ ለመሆን ገብተው የተመቱ፣ የተሰደቡ፣ የሞቱም እንዳሉ አስበው ዳር ቆመው መመልከትን ይመርጣሉ፡፤ ምንም እንኳ ሰዎች ሲጋደሉ ቆሞ መመልከት ተገቢ ባይሆንም፣ የእነዚህ ወገኖች ዳር ሆኖ መመልከት ስህተት ነው ብሎ ለመደምደም አያበቃም፡፡
ሌሎች ግን የተከፈለው ዋጋ ይከፈል ብለው ሰው ሲጎዳ እና ሲጋደል ቆመው አይመለከቱም፤ ዘለው ጠበኞቹ መሀል ገብተው ይገላግላሉ፡፤ እኔም አንድ ቀን ተመሳሳይ ችግር ቢገጥመኝ ማን ይደርስልኛል ብለው አስበው ሳይሆን በቃ ሰዎችን መታደግ እንዳለባቸው አምነው ላይሆን ይችላል፡፤ ብቻ ይገላግላሉ ያስታርቃሉ፡፡ በእዚህ አይነት መልኩ ሰዎችን ከአስከፊ አደጋ የታደጉም ጥቂት አይደሉም፡፡ የሚገላግሉት ደግሞ የሚያውቁት ሰው ስለሆነ ብለው ሳይሆን በቃ ሰዎች ተጣልተው የከፋ ጉዳት እንዳይከተል ለማድረግ ነው፡፡
አንዳንዴ ቆሞ መመልከትም ሆነ መገላገል የሚያስከፍለው ዋጋም ይኖራል፡፡ ጠቡ የከፋ እና የሰፋ ሊሆን ይችላል፤ ፓሊስ ተሳክቶለት ይደርስና ለማናቸውም ብሎ በአካባቢው ያለውን ሰው ሁሉ አፍሶ ወደ ማረፊያ ቤት ሊወስድ ይችላል፡፡ መረጃ እስከሚገኝም እስር ላይ መቆየት ይከሰታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህ ሊሆን እንደሚችል አውቀውም ሳይውቁም ሊሆን ይችላል እርምጃውን የወሰዱት፡፡
ከማገላገሉ ጋር በተያያዘ ምንም ይፈጠር ምን እርምጃቸው ትክክል ነው፡፡ ከእዚህ የከፋም ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቅሻለሁ፡፡ በቦክስ መመታት፣ በስለት መወጋት፣ በድንጋይ መመታት፣ መሰደብ፣ ለዛቻ መዳረግ ወዘተ ሊከተል ይችላል፡፡ በምስክርነት መጉላላት ደርሶም ይሆናል፡፡ በግልግል ወቅት ከደረሰ ጉዳት ጋር ተያይዞ መከሰሰም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይሄ ይሄ ሁሉ ሁለተኛ ኮሽ ባለበት ቦታ አልገኝም የሚሉ ሰዎች እንዲፈጠሩ ያደርግ ይሆናል፡፡
በመሰረቱ ሰው ሲጣላ እያዩ መሄድ ወይም ዝም ብሎ መመልከት ሰውኛ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ሃላፊነትን አለመወጣትም ይሆናል፡፡ በህግ መነጽርም ቢሆን የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ አካል ሲጎድል ሲጋደሉ ቆሞ ማየት ወይም መሸሽ በህግም የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፤
ቤተሰብ፣ ጎረቤት ቀዬ ወዘተ ሰላም እንዲሆን ሃላፊነቱ የፖሊስና የመሳሳሉት የፀጥታ ሀይሎች ብቻ አይደለም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፈነትም ጭምር ነው፡፡ በማገላገል ወቅት ቆሞ በመመልከት ወቅትም ሆነ በሽሽት ወቅት ካጋጠመ ችግር ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን የነግ በኔ አመለካከት ለጊዜው እናቆየውና ሰዎች ማህበራዊ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ግን እናስብ፡፡
እያንዳንዱ ሰው ጠብ ሲመለከት መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፤ ጠብ እየሰፋ ሄዶ ዳር የቆመውንም መንደር ያለውንም ላይምር ስለሚችል በጊዜ እንዲበርድ ማድረግ ይገባል፡፡ ሲሆን ሲሆን ደግሞ አስታርቆ መሸኘት ወይም ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ትክክለኛው አካሄድ ነው፡፡ ችግር እንዳይሰፋ የሚያደርግ በመሆኑም ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት ነው፡፡
የጠቡን ደረጃ መመዝንም ያስፈልጋል፡፡ እነማን ተጣሉ የሚለውን መመልከት ይገባል፡፡ የልጆችን ጸብ መገላገል አያዳግትም፡፡ አስቸጋሪ የሚሆነው ድንጋይ ፣ ስለትና የመሳሰሉትን ጭምር ይዘው የሚጣሉትን መገላገል ይሆናል፡፡ እሱም ቢሆን መላ ይኖረዋል፡፡ መገላገል አለመቻሎን ካወቁም ሊገላግሉ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡት መንገርም አንድ መላ ነው፡፡ መሸሽ ወይም ቆሞ መመልከት ግን ትክክል አይደለም፡፡
ቢያንስ ነግ በእኔን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ሲደባደቡ መሸሽ፣ ቆሞ መመልከት፣ አለመገላገልና አለማስታረቅ ማህበራዊ ሃላፊነትን መሸሽም ነው፡፡ ለችግር መላ ፋላጊ እንጂ ችግር እንዲሰፋ እና እንዲፋፋ መፍቀድ አይገባም፡፡ ጸብ እያዩ እዚያው በጸባላችሁ ማለቱ ሜዳ ሲቃጠል ተራራ ይስቃል እንደሚባለውም ሊሆን ይችላልና ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል