ጥቂት የማንባል ሰዎች አሁን አሁን ከዕለት ሩጫችን የምትተርፍ ጊዜ ብትኖር የቅርብ ዘመዶቻችንን አሊያም ወዳጆቻችንን ለመጠየቅ ማዋል ትተናል፤ የእኛን ጊዜ ከሚፈልጉ ቤተሰቦቻችንም ሆነ ጎረቤቶቻችን ጎን ከመገኘት ይልቅ በተለያዩ ድረ ገፆች በተለይ በተለይ ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ማፍጠጥን እንመርጣለን፡፡
ስራችንን ወደጎን በመተውም በየአምስትና አስር ደቂቃ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን አሊያም ደግሞ ኮምፒውተሮቻችንን መነካካት ከተጠናወተን ቆይቷል፡፡ የቱ መቅደም አለበት የሚለው ውሉ ጠፍቶናል፡፡
ለራሳችን ስለራሳችን ጊዜ በመስጠት በጥሞና የምናሳልፋት ፍርፋሪ ጊዜ ብንፈተሸ አይገኝብንም፡፡ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ስለተለጠፈው እያንዳንዱ ነገር ስንመራመር፣ በሚሰጡ አስተያየቶች ሆዳችን እስኪቆስል ድረስ ስንስቅ፤ አለፍ ሲልም በመልዕክቶቹ ዙሪያ በተቃርኖ ወይም በድጋፍ የመሰለንን አስተያየት ስናሰፍር አቻ የማይገኝልን ትጉህ ሰራተኞች እንመስላለን፡፡
በማንባቡ፣ በመፃፉና በመሳቁ አንዳንዴም በምናነበው አሊያም በምናየው ተንቀሳቃሽ ምስልም (እውነትም ሐሰትም ሊሆን መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ) ለማልቀስ ስለሚዳዳን የሚታይብን የፊት ገፅታ ምንም ይምሰል ምን አጠገባችን ያለው ማንም ይሁን ማን ግድ አይሰጠንም፡፡ በጣም ስስ ሆነናል፡፡
ይህን ጉዳይ ለማንሳት ምክንያት የሆነኝ ነገር ወዲህ ነው፡፡ አንድ ጎረቤታችን አባወራ ባለቤቱ ስራዋ አንድ ሳምንት ቀን ሲሆን፣ አንድ ሳምንት ደግሞ ሌሊት በመሆኑ የምትሰራው በፈረቃ ነው፡፡ የማታ የማታ ስትሆን አንድ ዓመት ያልሞላውን ህፃን ልጇን ያው ለአባት ትታ ትሄዳለች፡፡ ይሁንና ስጋት ስለሚያድርባት እስከሚተኙ ድረስ በየ20 እና 30 ደቂቃ ልዩነት መደወሏም የተለመደ ነው፡፡
አባወራው ግን ህፃኑን ከመከታተል ይልቅ አይኖቹንም ሆነ እጆቹን ከተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ ለአፍታም ቢሆን አያነሳም፡፡ ይህም ‹‹እውነት ይህ ህጻን የእርሱ ነውን›› ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል፡፡ እንዲያው ልጁ አጠገብ ሆኖ ስልኩን መነካካቱና በማህበራዊ ድረ ገፁ ላይ በተለጠፉ መልዕክቶች ምላሽ ለመስጠት አለመቦዘኑ አይደለም ዋናው ጭንቅ፣ አንድ የሆነ መረጃ (የውሸት ይሁን የእውነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) ሲያነብ ካለበት ቤት ወጥቶ ፊት ለፊት ካለው ቤት የሚገኘውን ሌላውን አባወራ በመጥራት ‹‹እንትና የፃፈው አልገረመህም?! እኔማ ጥሩ አድርጌ መልሼለታለሁ…፡፡›› ሲል ብጤውን በመጥራት የባጡ የቆጡን ሲቀበጣጥር ህፃኑን እስከማስለቀስ ይደርሳል፡፡ ይህ እንግዲህ የተለመደ ተግባሩ ከመሆኑም በላይ መድኃኒት ያልተገኘለት ሱስ ሆኖበታል፡፡
እንደተለመደው አንድ ምሽት ላይ የልጇን ወተት ራሷ አፍልታ ትሄድ የነበረች እናት በስራ ከመዋከቧ የተነሳ እንዲያፈላለትና አቀዝቅዞ እንዲሰጠው ከአደራ ጭምር አስጠንቅቃው ወደስራዋ እብስ ትላለች፡ ፡ አባወራው ከስራ እንደተመለሰ ሱሱን ጋብ ሊያደርግ የፈረደበት ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ መጣድ እንጂ ወተቱን መጣዱን ጭርሱኑ አላሰበውም፡፡
ህፃኑ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ከተጣደበት ማህበራዊ ትስስር ገፅ ሁለንተናውን ያነሳና ወደ ህፃኑ ማፍጠጥ፤ ከዛም መደንገጥ ይሆንበታል፡ ፡ ፈጥኖም ህፃኑን ለማባበል ከእቅፉ ያስገባዋል፡፡ በሐሳቡ ህፃኑ ዝም ካለለት በኋላ ወተቱን ለመጣድ ነበር፡፡
ቤት ውስጥ ወዲህ ወዲያ እያለ ህጻኑን ሲያባብል ደቂቃዎች ተቆጠሩ፤ በውስጡም ስላነበባቸውና ስለሰጠው አስተያየት ማሰላሰል ያዘ፤ አፍታም ሳይቆይ ደግሞ ህፃኑን በእቅፉ እንደያዘ ወደ ውጭ ወጣ አለ፡፡ ያንኑ ሰው ይጠራውና ‹‹እኔ የምልህ? ምን ብሎ አፉን እንዳስያዘው አየህ አይደል?! እሱ እኮ ማለት ድሮም ቢሆን አንበሳ ነው፤ እንትናስ ዛሬ ምንም አላለ ይሆን?…›› እያለ ሌላ የወሬ ምዕራፍ በሰፊው ሊጀምር ሲል በአባቱ እቅፍ ውስጥ በብዙ ውዝወዛ ለመረጋጋት የሞከረው ህፃን ርቦት ስለነበር በድጋሜ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ወተቱን አለመጣዱ ትውስ ብሎት ዘሎ ወደቤት ይገባል፡፡
በዚህ መሃል በለቅሶ ብዛት የተዳከመው እንቦቀቅላ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ስለወሰደው ወተቱን ይጥዳል፡፡ ሱስ መቼም ቢሆን እስካልተቆረጠ ድረስ ሱስ ነውና ወተቱ እስኪፈላ በማለት ያንኑ የፈረደበትን ስልኩን መነካካት ይጀምራል፤ በሚያየውና በሚያነበው ጉዳይ መመሰጡን ይቀጥላል፡ ፡ ከነጎደበት ዓለም የተመለሰው የህፃኑ ወተት አንዲት ጠብታ እንኳ ሳይቀር ሙሉ ለሙሉ ምድጃው ላይ ገንፍሎ ካበቃ በኋላ ነበር፡፡
ወጥቶ ወተት አይፈልግ ነገር ምሽቱም ነጉዷል፤ ህፃኑም ምርር ብሎ ሲያለቅስ ቆይቶ የተኛው ባዶ ሆዱን ነው፡፡ ግራ ተጋባ፤ ባለቤቱ ዘንድ አይደውል ነገር ይብሱኑ እሷን ማናደድና እንድትጨነቅ ከማድረግ ዉጭ አንዳች ፋይዳ የለውም፡፡
የፈራው አልቀረም፤ ህፃኑ ነቃ፤ ለቅሶው እንደ አመሻሹ አይነት አልነበረም፡፡ ሆድ የሚያባባ አይነት እንጂ፡፡ አባትም የፀፀት እንባ ተናነቀው፡፡ የህፃኑን አይን የአዋቂ አይን እስኪመስለው ድረስ ሸሸው፡፡ አይኖቹን ከአይኖቹ አራቀው፡፡ ይህን ድክም እያለ የመጣውን የህፃን ድምፅ የሰሙ ጎረቤት ውድቅት ቢሆንም ‹‹አሞበት ይሆናል፤ እናቲቱም የለች…›› ሲሉ ወደእርሱ ይመጡና ህፃኑን ይቀበሉታል፡፡
መራቡንና ወተቱ ገንፍሎ ማለቁን ሲረዱም በማቀዝቀዣ ውስጥ የነበራቸውን ወተት አስታውሰው ‹‹ቆይ…›› ሲሉ ሮጠው ወደቤታቸው በመግባት እና ወተቱን በማምጣት የጋዝ ምድጃው ላይ እንዲያው ለስሙ ያህል ብቻ ሞቅ አድርገው ለህፃኑ በመስጠታቸው ለጊዜው ህፃኑ እፎይታን አግኝቶ ያሰማ የነበረውም የሲቃ ድምፅ ጠፍቶ ጡጦውን ብቻ በስስት ይምግ ጀመረ፡፡
ምናለ የህፃኑ ወተት እስኪፈላ ለአፍታ ያህል እንኳ ቢታገስ ማለታችሁ አይቀርም፡ ፡ ስንቶቻችን ነን በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ተጥደን በምንሰጠው አስተያየትና በምንለጥፈው መልዕክት የብዙዎችን ህይወት ያበላሸነው፤ ምናለ ቢቀርስ፡፡ ስንቶቻችን ነን ከተንቀሳቃሽ ስልካችን ጋር ተጣብቀን መትረፍ የሚችለውን ሰው በሰዓቱ ተገኝተን ካለማከማችን የተነሳ ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት የሆነው፡፡ ስንቶቻችን ነን ባለጉዳይ ፊት ለፊታችን ቆሞ ሲማፀነን እያየንና እየሰማን በማህበራዊ ድረ ገፅ በመጣዳችን ብቻ ምላሽ ሳንሰጠው ወደቤቱ በምሬት እንዲመለስ ያደረግነው፡፡
ምናለ በልኩ ብንሆን፡፡ በማያገባንስ ነገር ገብተን ያልሆነ አስተያየት በመሰንዘር አንዱን ከሌላው ያፋጀነው ስንቶቻችን እንሆን፤ ምናለ አስተያየትስ ሳንሰጥ ማለፍ ብንችል፡፡ አገርም ከነውጥ፣ የቅርብ የምንላቸውም ሰዎች ከስጋት እንዲሁም ከፅሁፉ እንደተረዳነው ደግሞ ህፃናት ከረሃብ መትረፍ ይችላሉና ብናስብበትስ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
አስቴር ኤልያስ