ዕለታዊው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወርሃ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዕትም አፍሪካ እንዴት አንድነቷን መስርታ ኃያል ሆና ለመውጣት ጥረት እንደጀመረች ያስነብባል።ጋዜጣው ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም በፊት ገፁ ‹‹ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች የተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፤ ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ›› ሲል አስነብቧል።
በግንቦት 19 ቀን 1955 ዓ.ም እትሙ ደግሞ በርእሰ አንቀጹ፣ ‹‹የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎችንም ብሎኮችና ቻርተሮች ሠርዞ የአፍሪካ አንድነትን የሚመሠርተው ‹ የአፍሪካና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተር › ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ተፈርሟል›› ሲል አስፍሯል።ቀጥሎም ‹‹በአራቱ ቀን ጉባኤ ፍጻሜ አዲስ የአፍሪካ ታሪክ፣ አዲስ የዓለም ታሪክ ተጽፏል፤ ተመዝግቧል›› በሚል የትናንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እንዴት እንደተመሰረተ ገልጿል።
ይህ ጉዳይ ዛሬ ማንሳት የተፈለገው ካለምክንያት አይደለም።የአፍሪካ ህብረትን መነሻ በማድረግ ስለተመሰረተው ሌላኛው የአፍሪካ ህብረት ለማውጋት ነው። ‹‹የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት›› አፍሪካዊያን አንድ ሲሆኑ ብዙ ነገሮች መለምለም እንደሚችሉ ያሳየና እያሳየም የሚገኝ ህብረት ነው። ለአህጉሪቱ ተማሪዎች ትልቅ ተስፋ የሰጠው ይህ የተማሪዎች ህብረት ከሁሉም በላይ አፍሪካዊያን በጋራ በተለያየ መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ያስተማረ ነው።
የህብረቱ አመሰራረትና ታሪክን በተመለከተ የጽሁፍ መረጃዎች የሚያመለክቱት ለህብረቱ ምስረታ ምክንያት የሆነው ነጻነትን የመፈለግ ሂደት ነው።እ.ኤ.አ. በ 1972 ‹‹የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ህብረት የመጀመሪያ ኮንግረስ›› (AASU) የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ሲመሰረት የመመስረቻ ስብሰባው የጀመረው በጋና ኩማሲ በሚገኘው ክዋሜ ንክሩማህ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነበር።
የስብሰባው ምክንያት የነበረው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበረው የግንኙነት ሁኔታ፣ የትራንስፖርት እና የፋይናንስ ችግር ነበር።ይህ እንዳለ ሆኖ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ቅኝ ገዥዎች በርካታ ግፎችን ፈጽመዋል።ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ የህዝብ አመጽ ተማሪዎች ተጨፍጭፈዋል፤ የአካልና የስነልቦና ጉዳትም ደርሶባቸዋል፤ ተፈናቅለዋልም።ይህንን ያደርግ የነበረው ደግሞ የአፓርታይድ ሥርዓት እንደነበር ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በዚህ አመፅ የተጎዱ አፍሪካውያን ተማሪዎችን ለመታደግና ይህንንና መሰል ችግሮችን ለማስቆም መፍትሄው በአንድነት ተሰባስቦ መታገል እንደነበር ታመነበት።እናም የወቅቱ ተማሪዎች ይህንን ሃሳባቸውን እውን የሚያደርግላቸው እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ።ይህም መሰባሰብና ህብረት ያለው ኃይል መፍጠር ሲሆን፤ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ከአስር ያላነሱ ሀገራት ተወካዮችን በመያዝ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ አከናወኑ።
ስብስባቸው ኃይል እንደሆናቸው ሲመለከቱ ደግሞ እንደነዚህ አይነት መደራጀቶችና ውይይቶቻቸውን ይበልጥ ገፉበት።በዚህም ስብሰባቸው ቀጣይነት ያለው ሆነና ሁለተኛው ስብሰባቸው በታንዛንያ ዳሬሰላም በ1973 ተደረገ።ሦስተኛው ደግሞ በዓመቱ በግብጽ አሌክሳንዴርያ ውስጥ ተከናወነ።እንዲህ እንዲህ እያሉም አራተኛውንና በአይነቱ ልዩ የሆነውን ጉባኤያቸውን ጋና አክራ ላይ አካሄዱ።
በእርግጥ ይህ ጊዜ በዓመቱ የተከናወነ አልነበረም።ሁለት ዓመታትን አስጠብቋቸዋል።ይሁን እንጂ ፍሬያማ ያደረጋቸው ስለነበር አልተቆጩበትም።ምክንያቱም በጣም በርካታ ተማሪዎች ተሳትፈውበታልና ስኬታማ ያደረጋቸው አዳዲስ ነገሮች ተፈጥረዋል። አንዱ በወቅቱ የተለያዩ ድርጅቶች ህብረቱን እንዲቀላቀሉት መሆኑ ነው።ለአብነት የወቅቱ የብሔራዊ ነፃ አውጪ ንቅናቄዎች የዚህ አካል መሆን መቻሉ ነው።በተለይም በደቡብ አፍሪካ ያሉት እንደ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እና የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ህዝቦች ድርጅት (ኤስዋፖ) አይነቶች ተቀላቅለውታል።ይህ ደግሞ ለህብረቱ መጠናከርና ወደ ፊት መጓዝ ጥሩ እድልን ያቀዳጀ ነበር።
ይህ እድል በተለይም ማንነትን ከማስከበርና በደቡብ አፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ ጉልህ ሚናን ለመጫወት አስችሏቸዋልም።በዚህም ህብረቱ ከቅኝ አገዛዝ ጋር በተደረገው ትግል ላይ ትልቅ ሚና እንዲኖረውና የአፓርታይድ ሥርዓትን ታግሎ መገርሰሱ ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ አድርጎታል።
የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም እኤአ በ1982 ጉባኤውን አሂዷል።ይህ ጉባኤው እንደ አራተኛው ጉባኤ ሁሉ ልዩ ተስፋን የጫረና የማይገረሰስ ታሪክን የተከለ ነበር።ጉባኤው የተካሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ሲሆን፤ አንድ ጠንካራ መሰረት የተጣለበት እንደነበር በህብረቱ ታሪክ ላይ የተፃፈ ሰነድ ያትታል።
ሰነዱ እንደሚያስረዳው፤ ስድስተኛው ጉባኤ ልዩ መልዕክት ያለው ነበር።የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት ተቋቁሞ ሰኔ 16 ‹‹የአፍሪካ ተማሪዎች ቀን›› ተብሎ እንዲከበር ታሪካዊ ውሳኔ ተላልፏል።ስለዚህም እኤአ 1982 ለአፍሪካ ተማሪዎች አዲስ ምዕራፍ ሆኗል።የህብረቱ መቋቋምና የቀኑ መከበር ደግሞ የሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ነበር።አንዱ አፍሪካዊያን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ሰብሰብ ብለው እንዲመካከሩ እድል መስጠቱ ሲሆን ሌላው ደግሞ በመረዳዳት በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች አይቶ መፍትሄ መስጠት ነው።በተለይም ለተማሪዎች የትምህርት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እንዲሰራበት ያደርገዋል።
ህብረቱ እንደ አህጉር ጥሩ የሚባል ሥራ በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ እየሰራ እንደሆነ ከሰነዱ ባሻገር በተግባር ማረጋገጥ ይቻላል።ሰሞኑን ‹‹የአፍሪካ ተማሪዎች ቀን›› “Back to Addis” በሚል መሪ ሀሳብ ከ41 ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ተከብሯል።ቀኑ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የተከበረ ሲሆን፤ አንዱ የህብረቱ አመሰራረትና ይዞት የመጣው ለውጥን የሚያስቃኝ ነበር።ሌላው ደግሞ ለሀገራችን ይዞት የመጣው የድጋፍ ጥሪ ነው።ይህም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙት ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ነው።
የህብረቱ ፕሬዚዳንት ኦሲሲጉ ኦስኬኚ በክብረ በአሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹የአፍሪካ የተማሪዎች ህብረት በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ እንቅስቃሴ የነበረው ኃይል ነው፤ በአህጉሪቱ ላይ ለአፍሪካ ተማሪዎች ጥላ ሆኖ የዘለቀ።ምክንያቱም ሁሉም የተማሩና በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ችግሮችን በመፍትሄ ይቃኛሉ።የመተጋገዝን ጥቅም በሚገባ አውቀዋልና እንደአህጉር በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ይተባበራሉ።ማንነታቸውን አክብረው በየዘርፉ ልቀው እንዲወጡ ይደጋገፋሉ፡፡›› ብለዋል።
ህብረቱ የአህጉሪቱን 54 ሀገራት ይዞ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ያሳትፋል።ይህ ደግሞ ለአንዱ ሸክም የሆነው ለብዙ ሲሆን ጌጥ ተደርጎ በመፍትሄ ያሸበርቃል።እናም አሁን የአፍሪካ ተማሪዎች ችግር በህብረቱ በየአቅጣጫው መፈታት ይኖርባቸዋል።በተለይ አሁን ላይ በትምህርት ጥራትና ፍታዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ህብረቱ በስፋት እየሰራ ነውና ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።
ህብረቱ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ የጥራት ማረጋገጫ፣ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓቶችን ማጣጣም ላይም በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ፤ በተለይ ደግሞ በትምህርት እንቅስቃሴ ውስጥ ብቃት ትልቁ ማንጸሪያ እንዲሆን እየሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲኖር ፣ የተማሪዎች መብት እንዲጠበቅ፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥና የአፍሪካ ባህል እንዲያድግ በስፋት ይሰራልም ይላሉ።
እንደ ፕሬዚዳንት ኦሲሲጉ ኦስኬኚ ገለጻ፤ ህብረቱ እንደ አፍሪካ ዘላቂ ልማት፣ ሥራ ፈጣሪነትና የአካዳሚክ ነፃነት እንዲኖር የሚሰራ ነው።ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አላማቸውን የምርምር ነፃነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም የሰላምና የዴሞክራሲ እሴቶችን ማሳደግ ላይ አድርገው እንዲሰሩ ይደግፋል።ለዚህ ማሳያው ደግሞ የተማሪዎችን መብት በማሳደግ እና በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የትምህርት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን ብርቱ ጥረት አድርጓል በሚል እ.ኤ.አ. በ2000 የተባበሩት መንግሥታት እውቅና የሰጠው ነው።ስለዚህም ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
አሁን እንደ አህጉር ተደጋግፎ ነገሮችን ማለፍ ያስፈልጋል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በጦርነቱ ከወደሙ ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ የህብረቱ ፕሬዚዳንት ኦሲሲጉ ሲናገሩ ‹‹በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ ናቸው።በዚህም በሠላማዊ መንገድ መፍታት ካልተቻለ የተማሪዎችን እንግልት ማስቀረት ከባድ ይሆናል።እናም ግጭቶቹ በርከት ያሉ ተማሪዎችን ለችግር እየዳረገ ስለሆነ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ከግጭት ወጥተው ተማሪዎች የፈለጉትን እንዲያገኙ ማድረግ ላይ መሥራት ይገባል።እነርሱም ከዚህ ድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው››።
በግጭቱ የፈረሱትን ትምህርት ቤቶች ደግሞ አሁን ላይ የሁሉንም አካል ትኩረት ይሻሉ።እናም ሁሉም ለግንባታው መረባረብ ይገባዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ግጭት አሁን ቀንሷል።ሆኖም ብዙ የተጎዱ አካባቢዎች አሉ።ስለዚህም እርሱን በመደጋገፍ መጠገን ያስፈልጋል።ለዚህ ደግሞ በመላው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ርብርብ ማድረግ አለባቸው።ህብረቱም ይህንን በማድረግ በኩል የበኩሉን እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ ከነበረችበት ግጭት ወጥታ ይህን መሠል አህጉራዊ ሁነት ማዘጋጀቷ እንዳስገረማቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ሀገሪቱ ምንም አይነት ችግር ቢገጥማት የማትበገር መሆኗን አሳይታለች ይላሉ።ሆኖም በግጭቱ የመጡ ችግሮች በራስ አቅም ብቻ የሚፈቱ ስላልሆኑ የፈረሡ የትምህርት ተቋማትን መልሶ የመገንባትና ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ መተጋገዝ ይጠይቃል ባይ ናቸው።እናም የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት ይህንን ሥራ በማከናወኑ በኩል ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል።
የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ህብረት የዓለም አቀፍ ህዝብ ግንኙነት ተወካይ አቶ ኦሊ በዳኔ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ተማሪዎች ቀን የሚከበረው ዝም ብሎ ለይስሙላ ሳይሆን ቀደም ሲል ዋጋ የከፈሉ ተማሪዎችን ለማሰብና በአህጉራችን አፍሪካ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች እንዲቆሙ ድምጽ ለመሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።ስለዚህም ሁሌም ይህንን ቀን ስናስብ እንደ አፍሪካ እጅና ጓንት በመሆን በመስራት ሊሆን ይገባል። የተቸገሩትን በመርዳት፣ የፈረሱትን በመጠገንና በመገንባቱ ላይ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።
ሌላው በመርሃ ግብሩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አብዱ ናስር እንደሚሉት፤ የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ቀን በሀገራችን መከበሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። የመጀመሪያው ለምናስበው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ትልቅ አቅም ይፈጥራል። በህብረት መስራትንም ያጠነክርልናል። በተለይም አሁን የትምህርት ቤት መሻሻል ላይ ለምናደርገው የተለየ ጥረት ብዙ አጋዥ ነገሮችን ያመቻችልናል።
ኢትዮጵያ ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።በተለይም የጥራት ጉዳይ ዋና አጀንዳዋ አድርጋ መንቀሳቀስ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። ይህንን በማገዙ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን።ስለዚህም ይህ ቀን ልዩ ስንቅ የምንሰንቅበት በመሆኑ እንደትምህርት ሚኒስቴር እጅግ ደስተኛ ነን ሲሉም የቀኑ መከበር ይዞት የመጣውን ተስፋ ያስረዳሉ።
የአፍሪካ ወጣት ተማሪዎች ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ያሉት ደግሞ በመርሃ ግብሩ በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ ሲሆኑ፤ እርሳቸውም ስለ ህብረቱና ይዞት ስለመጣው ተስፋ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል።‹‹ ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነትና ኅብረት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንን ወሳኝና ተቀዳሚ ተግባር ነው።ይህንን ከምናሳይበት መንገድ ደግሞ አንዱ እንዲህ በህብረት የምናከብራቸው ቀናት ናቸው።ስለዚህም ይህንን ማስቀጠልና መተጋገዛችንን ማጠናከር አለብን››
ዶክተር ሀብታሙ አፍሪካዊያን ህብረታቸውን ካጠናከሩ በብዙ መልኩ መተጋገዝ ይችላሉ።አንዱ በውጪ ትምህርት እድል ሲሆን፤ በዚህ ብዙዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ ማንም ይረደዋል።ከዚያም ባሻገር አፍሪካ ተማሪዎች እርስ በእርስ መገናኘት ሲችሉ የባህል ልውውጥና የመማማሪያ መድረክ ያገኛሉ።ይህ ደግሞ በተማሪዎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ይቀንሳል።የምርምር ሥራን ያሰፋል፤ የልምድ ልውውጥና ተጨባጭ ጥናቶችን እንደሀገር ያመጣል ባይም ናቸው።
የዘንድሮው የአፍሪካ ተማሪዎች ቀን ለወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ትልቅ ተስፋ የሰጠና ቃል የተገባበት ነበር።አፍሪካውያን ተማሪዎች ልምድ ተጋርተውበት ፣ የቀጣይ የትምህርት ዘርፉ አቅጣጫና ሥራዎች ምን እንደሚሆኑ ተወያይተውበትም ተጠናቋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም