ውልደቱ እ.ኤ.አ 1971 ኢራቅ ውስጥ ነው። ሙሉ ስሙ አቡባክር አል-ባግዳዲ ይባላል። የአሸባሪ ድርጅት የኢራቅና ሌቫንት እስላማዊ መንግሥት (ISIL) አንጋፋ መሪ ነው። ከ2011 ጀምሮ ለበርካታ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ፍንዳታዎችና የተቀነባበሩ ጥቃቶች ኃላፊነት ወስዶአል። በሺዎች ለሚቆጠሩት ንፁሐን ሞትም ተጠያቂ ነው ።
አል-ባግዳዲ በአሜሪካ መንግሥት የሽብር ተኞች መዝገብ ዓለም አቀፍ አሸባሪ እንደሆነ የተወሰነበት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ 2014 ሞሱል ላይ በአልኑሪ መስጊድ ሆኖ በሶሪያና በኢራቅ ውስጥ ያለው እስላማዊ ግዛት መሪ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ታይቶ አያውቅም።
የአል-ባግዳዲ ቡድን ከዓመታት በፊት ሰፊ የምዕራብና ሰሜን ኢራቆችን እንዲሁም የሶሪያ ከተሞችን መቆጣጠሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ይሁንና አሜሪካ መራሹ ዓለም አቀፍ የፀረ አይ.ኤስ ጥምረት ለዓመታት ባካሄደው ዘመቻ ሙሉ በሙሉ ሊባል በተቃረበ መልኩ ይዞታዎቹን መመለስ ግድ ብሎታል።
አሜሪካም፣‹‹የምድራችንን ቁጥር አንድ ተፈላጊ ወንጀለኛ አሳልፎ ለሰጠኝ 25 ሚሊዮን ዶላር አሊያም 19 ሚሊዮን ፓውንድ ወሮታን እክፍላለው›› ስትል ያሳወቀች ቢሆንም፤ ተፈላጊውን ወንጀለኛ ‹‹ይዘነዋል›› አሊያም ‹‹አይተነዋል›› የሚል ማግኘት ግን አልቻለችም።
ከሰውየው አደገኛነት አንፃር፤ አሜሪካና አጋሮቿስ ከተደራጁበት እጅግ ረቂቅና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም አንፃር ለምን ግለሰቡን ያለበትን ማወቅና፣ አድነው በቁጥጥራቸው ስር ማዋል አቃታቸው ሲሉ የሚጠይቁም አል ጠፉም።
ለዚህ መልስ አለን የሚሉት በሌላ በኩል፤ ሰውየው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያ ድርጋቸው እንቅስቃሴዎችም እጅግ ውስብስብ በሆነ ጥንቃቄዎች የታጀቡ ዘመናዊ የቴኖሎጂ የግንኙነት መስመሮችን የማይጠቀም መሆኑን እርሱን የማደኑን ዘመቻ ከባድ እንዳደረገው ያመላክታሉ። በእርግጥም ሰውየው ያለፉትን አምስት ዓመታት እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ከዓለም ተሰውሮ ቆይቷል።
ይሁንና ከቀናት በፊት ሰውየው ከአምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ታይቷል። የሽብር ቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ልሳን ባሰራጨው ቪዲዮ መሪው የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል። የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ ውን ትክክለኛነት የተረጋገጠና መቼ የተቀረጸ ስለመሆኑ ግልፅ ባይሆንም አይ.ኤስ ግን በያዝነው የሚያዝያ ወር የተቀዳ መሆኑን ጠቅሷል።
በእርግጥ ሰውየውም በርካታ ወቅታዊ ሁነቶችን በንግግሩ አካቷል። በሶሪያ የመጨ ረሻዋ ግዛት የሆነችው ባጉዝ፣ ራቃና ቤንጋዚ እንዲሁም በሞሱል ስለገጠመው ሽንፈት በተለይም በቅርቡ በስሪላንካ ስለተፈጸመው ጥቃት ሲናገር ተደምጧል።
እ.ኤ.አ በ2017 ሩሲያ ሰውየው ከሚገኝበት አቅራቢያ በፈፀመችው የአየር ድብደባ አካሉ ላይ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት የተለቀቀው ምስል ግን ጉዳት እንደደረሰበት በቀላሉ ማሳየት አልቻልም።
ቆሞ አለመታየቱም ምናልባት ጉዳቱን ለመደበቅ የተቀመረ ሰለመሆኑና ሰውየውም በመልዕክቱ ስለ ራሱ ጤንነት ይህ ነው ብሎ የተናገረው አንዳችም ባይኖርም፤ ‹‹ገፅታው በጠባብ ምሽግ ውስጥ አስቸጋሪ ጊዜያትን ያሳለፈ ሰው አይመሰልም›› ተብሏል።
መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች በአንፃሩ ከምስል ቀረፃው በኋላ የሽብር ቡድኑ መሪ ዳግም መታየት ለምን? ሲሉ በስፋት አንስተዋል። በዚህ ረገድ የቻይናው ግዙፍ የዜና አውታር ዥንዋ የፀጥታና ደህንነት ተንታኞችን ዋቢ በማድረግ እንዳስነበበው፤ የአል-ባገዳዲ ዳግም መከሰት በመካከለኛው ምስራቅ ቡድኑ እየደረሰበት ያለው አስከፊ ውድቅትና መንኮታኮት ምክንያት የውስጥ ጫና ግፊትና የመሸነፍ ፍርሃት ውጤት ስለመሆኑ አትቷል።
በኢራቅ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ሃሺም አል ሃሺም ለዥንዋ በሰጠው አስተያየትም፤ ‹‹የሰውየው ዳግም መከሰት ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉና ቀሪ አባላቱን የቀደመ መንፈስ ለመመለስ ሳይሆን በአሽባሪ ቡድኑ አባላት ዘንድ የተፈጠረና እያደር የጠነከረ ውስጣዊ ጫና ግኝት ነው።›› ብሏል።
የሽብር ቡድኑ መሪ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ላይ የሚገኙት የቡድኑ አባላት መከፋፋል እንዳሳሰበው ያመላከተው ፀሐፊው፤ ይህም በተለይ ቡድኑ በሶሪያ አል ባጉዝ ከተማ ከደረሰበት አስከፊ ሽንፈት በኋላ ይበልጥ ማየሉን አትቷል።
አባሎቹ በየቀኑ በሶሪያና በኢራቅ አስከፊ ሽንፈትና የሞት ፅዋን ሲጋቱ፤ እርሱ በአንፃሩ ለደህንነቱ ዋስትና በሚሰጠው ሁኔታ ተደላድሎ መቀመጡን በርካቶችን ማስቆጣቱን የጠቆመው ፀሐፊው፤ የቪዲዮ መልዕክቱም መሰል ተቃውሞዎችን ለማብረድና በተከታዮቹ መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ማርገብን ዓላማው ያደረገ ስለመሆኑ አብራርቷል።
ኩርዳዊው የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኝ ሞሐመድ አል ካራዳጂ በሌላ በኩል፤ የመሪው ዳግም መከሰትና ከቀናት በፊት የተፈፀመውን 250 ንፁሃን ህልፈት ምክንያት የሆነው አሰቃቂ የስሪላንካ የሽብር ጥቃት ዋቢ ማድረጉ ነገም ቢሆን አስከፊው ስለመምጣቱ የሚጠቁም ነው ብሏል።
በኢራቅ የሚገኙ ሽብርተኞች ግብዓተ መሬት አለመፈፀሙንና የመሪው መልዕክትም ለአባሎቹ ተጨማሪ ጥቃት መፈፀም አረንጓዴ መብራትን ያመላክተ መሆኑን የጠቆመው ተንታኙ፤ ይህ እስከሆነም ኢራቅም ሆነ መላው ዓለም ከመዘናጋት ይልቅ አሁን ላይ የሚካሄዱ የፀጥታ ጥበቃዎች ጥብቅ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝቧል።
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው፤ የመሪው መመለስ በአገራቸው ያለውን የመቀየር አቅሙ ማክተሙንና ፋይዳ ቢስ መሆኑን በማስገ ንዘብ፤ ‹‹ይልቅስ እኛ በቀጣይም እነዚህን ካንሰሮችን ዳግም እንዳያንሰራሩ ለመቅበር ህብረትና ትብብራችን እናጠናክራልን» ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩሮ ኤሲያ የሰራው ሰፊ ትንታኔ፤ ‹‹አይ. ኤስ በሶሪያ የመጨረሻዋ ግዛት የሆነችው ባጉዝ ከቡድኑ ቁጥጥር መላቀቅ፤ በሽንፈቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹ ማፈግፈግ፤ በርካቶች መፈናፈኛ አጥተው መከበብና አብዛኞቹም በቁጥጥር ስር መዋል መሪው ላይ ብርቱ ጭንቀት ስልፈጠረበት ነው ሲል›› አትቷል።
በእርግጥም የአይ.ኤስ በሶሪያ የመጨረሻዋ ግዛት የሆነችው ባጉዝ ነፃ መውጣት በኋላ፤ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ ተዋጊዎች በተደረገላችው ቃለ ምልልስ፤ በርካቶች ለካ ሊፌቱ የነበራቸውን ድጋፍ መጥፋቱና ስለምን እንደሚፋለሙም ቅጡ እንደጠፋባችው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የባጉዝ ነፃ መውጣት ከፈጠረው ጭንቀት በተጓዳኝ፤ የመሪው ዳግም መከሰት በተለይ 250 ንፁሃን ህልፈት ምክንያት የሆነው አሰቃቂ የስሪላንካ የሽብር ጥቃት ዋቢ ማድረጉ አሁንም ‹‹አልሞትንም መሪውም እኔ ነኝ» የሚል እንድምታን እንዲያዝለትና ከሞት የተረፉት አባላቱ ጥቃታቸው እንዳያቋርጥ የተቀመረ ሰለመሆኑ ተመላክቷል። ይህ ማለት ግን ቡድኑና አባላቱ አሁንም ቢሆን ሥጋት አይደሉም ማለት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባልም ተብሏል።
እንደ ቮክስ ኒውስ ዘገቢዋ ጄኔፌር ዊሊያም ከሆነ ደግሞ፤ ባለፉት ዓመታት ቡድኑ ሰፊ ግዛቶችን በስሩ ማድረግ ቢችልም፤ አሜሪካ መራሹ ጥምር ጠንካራ ጥቃት በርካታ ይዞታዎቹን ለማስረከብ መገደዱን ታስ ታውሳለች።
ምንም እንኳን የቀደመ ሃይሉ ዛሬ ላይ ቢንኮታኮትም፤ አልፎ አልፎ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሳቸው የሽብር ጥቃቶች ግን እንዳልቆሙ የምታመላክተው ፀሐፊዋ፤ ምንም እንኳን ቡድኑ ቢፈረካከስም፤ አሁንም ቢሆን ግብዓተ መሬቱ አለመፈፀሙን ጠቅሳ፤ ሆኖም ግን ሁሉም ነገ ላይ የሚታይ ነው ብላለች።
የዘ ሂንዱ ድህረ ገፅ ፀሐፊው ሳታንሊ ጆኒ ዘገባ በበኩሉ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት አይ.ኤስ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ይዞታዎቹን ቢነጠቅም ዳግም የመመለሱ ትርጉም «ካሊፌቱ ቢንኮታኮትም፤ አይ.ኤስ አሁንም አላበቃላትም›› የሚል ነው ሲል አስነ ብቧል።
በአጠቃላይ የሽብር ቡድኑ መሪ ዳግም መታየት በሚመለከት የሚሰነዱ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችና የባለሙያ አስተያየቶች ሁለት አይነት እንድምታን ይዘዋል። ለአንዳንዶች የመሪውን ዳግም መታየት የሽብር ቡድኑ ግብዓተ መሬት ሊፈፀም በመቃረቡ ለይስሙላ አለን የሚል ምክንያትን ያነገበ ሆኗል።
አብዛኞቹ በአንፃሩ፤ የሰውየው ዳግም መከሰት መጪው አሳሳቢ ስለመሆኑ አስምረው በታል። እናም ቡድኑ ተዳክሟል በሚል ከመዘናጋት ይልቅ ከእንቅልፍ መንቃትና የተጀመሩ ዓለም ዓቀፍ የሽብር ዘመቻዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተውታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
በታምራት ተስፋዬ